ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተካረረው የአሜሪካ እና የካናዳ የንግድ እና የታሪፍ ጦርነት
የአሜሪካንን እርምጃ ተከትሎ ካናዳ በበርካታ የአሜሪካ ምርቶች ላይ የጣለችው የአጸፋ ታሪፍ ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ ሥራ ላይ መዋል ጀመረ።
ይህ ካናዳ በአሜሪካ ላይ የጣለቸው የአጸፋ ታሪፍ ወደ 28 ቢሊዮን የካናዳ ዶላር (20 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር) የሚጠጉ ከአሜሪካ ወደ ካናዳ የሚገቡ ምርቶችን ይመለከታል።
ይህም ከብረት እስከ የቤት እቃዎች፣ ጥጥ እና የተለያዩ አልባሳትን የሚያካትት ሲሆን፣ የታሪፉ መጠን እስከ 50 በመቶ ይደርሳል።
የአሜሪካ እና የካናዳ ባለሥልጣናት አዲስ ስምምነት ለመፈራረም ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም፣ በነሐሴ መጨረሻ የተቋረጡትን ውይይቶች ለመቀጠል የሚደረግ ምንም እርምጃ አልታየም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ ካናዳ አሁንም ከአሜሪካ ጋር ዘላቂ እና ለሁለቱም አገራት ጥቅም የሚያመጣ ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።
የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ጄሚሰን ግሪር በበኩላቸው ሐሙስ ዕለት "ኳሱ አሁን በካናዳ ሜዳ ላይ ነው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት የካናዳው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦምባርዲየር የምርት ሂደቱን ወደ አሜሪካ ካላዘዋወረ ከኩባንያው ጋር የሚደረጉ ሁሉንም የአሜሪካ የንግድ ግንኙቶች ሊያቋርጡ እንደሚችሉ ዝተዋል።
ቦምባርዲየር በካናዳ ካሉ ትልልቅ ኩባንያዎች አንዱ ሲሆን፣ በታዋቂ የሂሳብ ተቋም ባስደረገው ጥናት በ2024 ብቻ ለካናዳ ኢኮኖሚ ከ7 ቢሊዮን የካናዳ ዶላር በላይ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ትራምፕ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ባወጧቸው በርካታ ጽሁፎች ካናዳን በድጋሚ ዒላማ አድርገዋል።
በአንዱ ጽሁፍ የካናዳ እና የአሜሪካ የገንዘብ ምንዛሪ ተመን "ተቀባይነት የለውም" ሲሉ፣ በሌላው ደግሞ ሰሜን አሜሪካን፣ ካናዳን እና ሜክሲኮን እንዲሁም ግሪንላንድን ያካተተ ካርታ በአሜሪካ ባንዲራ ተሸፍኖ ቀርቧል።
ካናዳ እና አሜሪካ በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነቶች አንዱን ይጋራሉ። የሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ በ2025 ወደ 900 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ተገምቷል።
በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ በካናዳ በሚመረቱ መኪኖች እና የጭነት ተሽከርካሪዎች 25 በመቶ ታሪፍ ጥላለች። በተጨማሪም በካናዳ ብረት፣ አሉሚኒየም እና የእንጨት ምርቶች ላይም ተጨማሪ ቀረጥ ተጥሏል።
በነሐሴ መጨረሻ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሌሎች የካናዳ ምርቶች ላይም አዲስ 50 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል። ከእነዚህ ውስጥ የወተት ተዋጽኦዎች፣ የአልኮል መጠጦች፣ ሽቶዎች እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ "ዶላርን በዶላር" ብለው የገለጹት የካናዳ የአጸፋ ታሪፍ ደግሞ ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ ከአሜሪካ በሚገቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምርቶች ላይ ተፈጻሚ ሆኗል።
እነዚህ አዳዲስ የአጸፋ ታሪፎች ቀደም ሲል ካናዳ በአሜሪካ ተጠናቀቁ መኪኖች እና የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ከጣለችው የአጸፋ ቀረጥ ተጨማሪ ናቸው። እነዚህ ተሽከርካሪዎች በካናዳ፣ በአሜሪካ እና በሜክሲኮ መካከል በሚገኘው የነጻ ንግድ ስምምነት መስፈርቶችን ያላሟሉ ናቸው።
የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች አብዛኞቹ የካናዳ ዜጎች አገራቸው በአሜሪካ ላይ የአጸፋ ታሪፍ መጣሏን እንደሚደግፉ አመለክተዋል።