በትግራይ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች "የጦር ቁስለኞች እና ታጣቂዎች" ካልወጡ ተማሪ እንደማይመደብ ትምህርት ሚኒስቴር አስጠነቀቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ትምህርት ሚኒስቴር በትግራይ ክልል የሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ግቢዎቻቸውን "ከማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ" እንዲያደርጉ አስጠነቀቀ። የዩኒቨርሲቲዎቹ ካምፓሶች ውስጥ የሚገኙ "የጦር ቁስለኞች እና ታጣቂዎች" እስካልወጡ ድረስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ተማሪዎችን እንደማይመድብ አስታውቋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጠው ዛሬ ሰኞ ጷጉሜን 2/2018 ዓ.ም. ለመቀለ፣ ለአክሱም፣ ለአዲግራት እና ለራያ ዩኒቨርሲቲዎች በጻፈው ደብዳቤ ነው።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ በትግራይ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ አመራር በትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተጻፈው ደብዳቤ ዛሬ እንደደረሳቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፌስቡክ ገጹ ላይ ደብዳቤውን ጋር አጋርቶ የነበረ ቢሆንም ከደቂቃዎች በኋላ አጥፍቶታል።

"የዩኒቨርሲቲ ግቢዎችን ከማንኛውም ወታደራዊና የትጥቅ እንቅስቃሴ ነፃ ስለማድረግ" በሚል የተጻፈው ደብዳቤ፣ ከዚህ ቀደም በመቀለ ዩኒቨርሲቲ ኩሓ ካምፓስ እንዲሁም በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምውፃእ ወርቂ ካምፓስ "የጦር ቁስለኞች መቀመጣቸውን" ይገልጻል።

"በቅርቡ ደግሞ በአክሱም እና አዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ዋና ግቢዎች ውስጥ የጦር ቁስለኞች እንዲቀመጡ [ተረጋግጧል]" ሲል ይከስሳል።

ይህ ሁኔታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ "ከሲቪል እና ትምህርታዊ ተልዕኳቸው ውጭ ለወታደራዊ ዓላማ እየዋሉ" መሆኑን እንደሚያመለክት ገልጿል። ይህ ዓይነቱ ድርጊት "የተማሪዎችን ሕይወት እና ደኅንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ" መሆኑንም በደብዳቤው አስፍሯል።

ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በጽሑፍ ጥያቄ አቅርቧል። በስልክ ጥሪ እና በጽሑፍ መልዕክት ከአራቱ ዩኒቨርሲቲዎች አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

አንድ የዩኒቨርሲቲ አመራር ደብዳቤው እንደደረሳቸው ቢገልጹም፤ በጉዳዩ "ስሱነት" (sensitive) የተነሳ አስተያየት ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ተናግረዋል። የመቀለ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዱልቃድር ከድር በበኩላቸው "ደብዳቤው እንዳልደረሳቸው" ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች "የወታደራዊ ኃይል ማረፊያ፣ ማከማቻ፣ ማደራጃ ወይም ማንኛውንም ተያያዥ ወታደራዊ ተግባር ማካሄጃ" መሆን እንደሌለባቸው የጠቀሰው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ መወሰድ አለባቸው ያላቸውን ሦስት እርምጃዎች ዘርዝሯል።

በቀዳሚነት ያስቀመጠው ዩኒቨርሲቲዎቹ በግቢዎቻቸው ውስጥ "የሚገኙትን የጦር ቁስለኞች በአስቸኳይ እንድታስወጡ" የሚል ትዕዛዝ ነው። "ሁሉም ግቢዎች ከማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴ ፈጽሞ ነፃ መሆናቸውን እንድታረጋግጡ" ሲልም ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

በተጨማሪም እንደ ካምፓሶች፣ የተማሪዎች መኖሪያ፣ የሕክምና ማዕከል፣ ሕንፃ፣ መጋዘን እና ተሽከርካሪ ያሉ የዩኒቨርሲቲዎቹ ሀብቶች "ለማንኛውም ወታደራዊ እና ተያያዥ ተግባር እንዳይውሉ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ" በማለትም አዝዟል።

የዩኒቨርሲቲዎቹ አመራሮች እና ቦርድ ለእነዚህ ትዕዛዛት "ልዩ ትኩረት ሰጥተው አፈጻጸሙን በቅርበት እንዲከታተሉ" አሳስቧል።

ትምህርት ሚኒስቴር፣ የዩኒቨርሲቲ ምደባ ወቅት "ለተማሪዎችን ሕይወት፣ ደኅንነት፣ ሰላማዊ የመማር ሁኔታ እና የትምህርት ቀጣይነት ቅድሚያ" እንደሰሚጥ በደብዳቤው ጠቅሷል።

አክሎም "የዩኒቨርሲቲ ግቢዎች ከማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ መሆናቸው በአግባቡ ካልተረጋገጠ ወደ ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎችን የማንመድብ መሆኑን ማስታወቅ እንፈልጋለን" ሲል የሚወስደውን እርምጃ አሳውቋል። በዩኒቨርሲቲዎቹ ካምፓሶች ይገኛሉ የተባሉት "የጦር ቁስለኞቹ እና ታጣቂዎችም ከዩኒቨርሲቲው ግቢ" መነሳት እንዳለባቸው አሳስቧል።

"ይህ ውሳኔ የተማሪዎች ደኅንነት እና ሰላማዊ የመማር ሁኔታ መሟላቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ተፈጻሚ ይሆናል" ያለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ "ከዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ ውጭ" የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን "ሪፖርት አለማድረግ ከፍተኛ ተጠያቂነት" እንደሚያስከትል አስጠንቅቋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ማስጠንቀቂያ የሰጠው በፌደራል መንግሥት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል ያለው ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ነው። የትግራይ ክልል አመራሮች ባለፈው ሐምሌ ላይ የ12ተኛ ክፍል ፈተናን በተመለከተ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የፌደራሉ መሥሪያ ቤት አገር አቀፉን ፈተና በተመለከተ "እርስ በራሳቸው የሚጣረሱ፣ ግልፅነት የጎደላቸው፣ በየጊዜው የሚቀያየሩ" ውሳኔዎች እንዳሳለፈ በመግለጽ ከስሶ ነበር። የራሱን ፈተና አዘጋጅቶ በክልሉ ለሚገኙ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች እንደሚሰጥ መግለጹም በተማሪዎች ዘንድ ግራ መጋባትን ፈጥሮ ነበር።

ይሁን እንጂ ኋላ ላይ ተማሪዎቹ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው ቀን በክልሉ በመቀለ እና አዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ፈተናውን ወስደዋል። ከትግራይ ክልል ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ተማሪዎችም በዚያው ዕለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፈተናውን እንደወሰዱ ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።