ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እስከ መጋቢት ሊቀጥል እንደሚችል ዜሌኒስኪ ከአሜሪካ ልዑካን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ገለፁ
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ልዑካን ጋር በኪዬቭ ካደረጉት ውይይት በኋላ፣ ከሩሲያ ጋር የሚካሄደው ጦርነት ከታህሳስ እስከ መጋቢት ወራት በሚቆየው የአውሮፓውያኑ ክረምትም ሊቀጥል ይችላል ብለው እንደሚጠብቁ ተናገሩ።
ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር፣ ሩሲያ ሙሉ ወረራ ከጀመረች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩክሬን ተጉዘው ከአገሪቱ መሪ ጋር ያደረጉት ውይይት ስላስገኘው ጉልህ ውጤት መግለጫ አልወጣም።
ሁለቱ የአሜሪካ ልዑካን፣ ወደ ኪዬቭ ከማቅናታቸው አንድ ቀን አስቀድሞ በሞስኮ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተወያይተው ነበር።
ዊትኮፍ "ጠቃሚ" እና "ሰፊ ይዘት ያለው" ባሉት የኪዬቭ ውይይት እንደተበረታቱ ተናግረዋል።
ዜሌንስኪ በበኩላቸው ሩሲያ በድጋሚ ወረራ እንዳትፈፅም የሚያስችል ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንደሚፈልጉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
እሁድ እለት ለሰዓታት በዝግ የተካሔዱትን ውይይቶች ተከትሎ፣ የዩክሬን፣ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ውይይቶችን ለመቀጠል በቅርቡ እንደሚገናኙ ዜሌንስኪ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል። ከሩሲያ እና ከአሜሪካ ጋር የሦስትዮሽ ውይይት እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።
"ጥሩ ውጤት ይኖራል ብለን እናምናለን" ሲሉ ዊትኮፍ ተናግረዋል። ተደራዳሪዎቹ ቅዳሜ ዕለት በሞስኮ ባደረጉት ውይይት "ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል" ሲሉም አክለዋል።
ስለ ሞስኮው ውይይት የተጠየቁት ኩሽነር ደግሞ፣ የአሜሪካው ቡድን "እስካሁን ድረስ ውጤት ያላመጡ ብዙ ሀሳቦችን መመርመሩን" እና "ዘላቂ ሰላም" ለማምጣት በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር መሞከሩን ገልፀዋል።
"በጣም ጥሩ ውይይት ነበረ። ፑቲን ብዙ ጥያቄዎችን አንስተዋል፤ እኛም እንደዚያው።"
ዊትኮፍ ልዑካኑ ወደ ኪዬቭ ከመጓዛቸው በፊት ከሩሲያው መሪ ጋር የተገናኙት ሩሲያ ያላትን አቋም ለማወቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
ዜሌንስኪ ጦርነቱ እስከ ክረምቱ ወራት ድረስ ከቀጠለ፣ ዩክሬን ተጨማሪ የአየር መከላከያ እና የኃይል አቅርቦት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት በአጽንዖት ገልፀዋል።
ዩክሬን የሩሲያን ባሊስቲክ ሚሳዔሎች ለመከላከል የአሜሪካ የ"ፓትሪዮት" መከላከያዎችን በስፋት ስትጠቀም ቆይታለች። ሆኖም አሜሪካ ከኢራን ጋር በነበራት ጦርነት ወቅት ከፓትሪዮት ክምችቷ ብዙውን ተጠቅማለች።
ባለፉት ዓመታት ሩሲያ በክረምት ወራት በተለይ የኃይል መሠረተ ልማቶችን ዒላማ በማድረግ ጥቃቶችን ስትፈጽም ነበር።
ዜሌንስኪ ዩክሬን የራሷን የፀረ-ባሊስቲክ መከላከያ ስርዓት ማልማት እንዳለባት ገልጸው፣ አሜሪካ ግን በሚቀጥለው ዓመት ምርቷን እንደምታሳድግ እና ዩክሬንም "ተስፋ ያደረገችው" ይህንኑ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
የአሜሪካ ልዑካን የሁለቱን አገራት መሪዎች ያነጋገሩት ሩሲያ እና ዩክሬን በቅርብ ወራት ውስጥ የአየር ጥቃቶቻቸውን ማፋፋማቸውን ተከትሎ ነው።
የአሜሪካ ልዑካን ከሩሲያ መልስ ወደ ኪዬቭ የገቡት በማቆራረጥ ሲሆን፣ ወደ ፖላንድ በአውሮፕላን ከዚያ በደግሞ በባቡር ነው። ዜሌንስኪ ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለፁት ሁሉም ዝግጅቶች ቢደረጉም አውሮፕላናቸው እንዲያርፍ ማድረግ ግን አልተቻለም።
ፑቲን እና ዜሌንስኪ፣ ተደራዳሪዎቹ ጉዟቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት በዋና ከተሞቻቸው ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለሦስት ቀናት ለማቆም ተስማምተው ነበር።
ዜሌንስኪ፣ ስቲቭ ዊትኮፍን እና ጃሬድ ኩሽነርን በኪየቭ በሚገኘው የቅዱስ ሶፊያ ካቴድራል ነበር የተቀበሏቸው። ይህ ቦታ የሚገኘው ሩሲያ ባለፈው አርብ በድሮን ከመታችው የዩክሬን የደህንነት አገልግሎቶች ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ ነው።
ከአሜሪካውያን አደራዳሪዎች ጋር በተናጠል የተካሔዱት ውይይቶች መጠናቀቃቸውን ተከትሎ የሩሲያ እና የዩክሬን ኃይሎች ሌሊቱን ጥቃት መሰነዛዘር ሲቀጥሉ፣ ዩክሬን የሩሲያን አንድ የነዳጅ ማጣሪያ፣ አንድ የአየር ማረፊያ እና ሁለት የአየር መከላከያ ስርዓቶች መምታቷን ገልፃለች።
ሩሲያ ደግሞ 108 ረጅም ርቀት የሚጓዙ ድሮኖችን እና ትናንሽ ክሩዝ ሚሳዔሎችን በመጠቀም ጥቃት መፈጸሟን የዩክሬን አየር ኃይል አስታውቋል።
የአገሪቱ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች፣ 82 ድሮኖችን እና 6 ሚሳዔሎችን ማውደማቸው ቢገለጽም፣ 11 ቦታዎች በቀጥታ ተመተዋል።