ሩሲያ በዩክሬን የደኅንነት ኃላፊ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሟን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ማዕከል ላይ ሩሲያ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት የዩክሬን የደኅንነት አገልግሎት ዋና መሥሪያ ቤትን መምታቱን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ አስታወቁ።

አርብ ከሰዓት ላይ ከደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሕንጻ ጋር የተጋጨው ሰው አልባ አውሮፕላን፣ የደኅንነት ኃላፊው ኦሌክሳንደር ፖክላድ ቢሮን ዒላማ እንዳደረገ ተገልጿል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰዓት ፖክላንድ ሕንጻው ውስጥ ስለመኖራቸው እስካሁን አልታወቀም። ነገር ግን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የደኅንነት ኃላፊውን እንዳነጋገሯቸው እና "ተገቢው፣ ተጨባጭ የአጸፋ ምላሽ" እንዲሰጥ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ "ድሮኑ ሕንፃው ውስጥ ባለው የደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ ቢሮ ላይ በቀጥታ ያነጣጠረ ነበር" ሲሉ አረጋግጠዋል።

ይህ ጥቃት፣ የሩሲያ አዳዲስ ድሮኖች ዒላማቸውን በትክክል የመምታት አቅም እየጨመረ መምጣቱን የሚያመለክት ነው። በተጨማሪም ሩሲያ ቅዳሜ እና እሁድ ሊካሄድ ከታቀደው የአሜሪካ የአሸማጋይነት ንግግር አስቀድሞ ሞስኮ ጥቃቶቿን ልታጠናክር እንደምትችል ጠቁሟል።

ዜሌንስኪ በቴሌግራም ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት "ሁሉም የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ሠራተኞች ቦታው ላይ ናቸው። ጉዳት የደረሰበት ሰው በሙሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያገኛል" ብለዋል።

"ሁሉም ነገር ዝግጁ ሲሆን ለሩሲያውያን ተመጣጣኝ፣ ተጨባጭ እና ከተቻለም ይህንን ጥቃት የሚያንጸባርቅ እርምጃ እንዲወሰድ ለፖክላድ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ። ጦራችንም ለዚህ ምላሽ ድጋፍ ያደርጋል" ሲሉም የአጸፋ እርምጃ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት በተሠራጩ ምሥሎች ላይ በሕንፃው ፊት ለፊት ከሚገኙ ሁለት መስኮቶች ጥቁር ጭስ ሲወጣ ታይቷል።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪይ ሲቢሃ ጥቃቱን "ጠንካራ ምላሽ የሚሻ ትልቅ የውጥረት መባባስ" ሲሉ ገልጸውታል።

አክለውም "ሞስኮ ይህንን ጥቃት የፈጸመችው አዲስ የሰላም ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው፤ ለዲፕሎማሲ ያላትን እውነተኛ ተቃውሞ በግልፅ ያሳያል" ሲሉም ወቅሰዋል።

የኪዬቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ እንደገለጹት በደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ላይ በተፈጸመው ጥቃት አምስት ሰዎች ቆስለዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቢሮዎቹ ውስጥ የነበሩ ስለመሆናቸውን ግን አላብራሩም።

በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ካፌ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፣ አንድ ደንበኛም ከጥቃቱ በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ አርብ ዕለት በዩክሬን ቾርኖሞርስክ ወደብ በሚገኝ የጭነት መርከብ እና ኦዴሳ አቅራቢያ የነበረ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሩሲያ በዩክሬን ዒላማዎች ላይ በቀን የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች ጨምራለች።

በብዙዎቹ ጥቃቶች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉት ፈጣን እና ለመጥለፍ አስቸጋሪ የሆኑትን በጄት ሞተር የሚሰሩ ድሮኖችን ነው። የትናንቱ ጥቃት የተፈጸመው በምን ዓይነት መሣሪያ እንደሆነ አልታወቀም።