የአሜሪካ ጦር ከሐምሌ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ
በኢራን በፈጸመው ጥቃት ላራክ ደሴት ላይ የሚገኙ ማስወንጨፊያዎችን መምታቱን አንድ የዋሽንግተን ባለሥልጣን ተናገሩ።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ቲም ሃውኪንስ
“የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ኃይሎች የባህር ውስጥ ፈንጂዎችን የያዙ ሮኬቶችን ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ለመተኮስ ሲዘጋጁ ታይተዋል” ሲሉ
በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እሁድ ምሽት
በተፈጸመው ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል። ለዚህ ጥቃት “ምላሽ እና ቅጣት” እንደሚሰጥም
ዝቷል።
አብዮታዊ ዘቡ ቆየት ብሎ ባወጣው መግለጫ፣ በዮርዳኖስ
በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እንደገለጸ የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ቢቢሲ ስለ ጥቃቱ አስተያየት ለማግኘት
ለአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ጥያቄ አቅርቧል።
የዮርዳኖስ ጦር ከአብዮታዊ ዘቡ መግለጫ ከአጭር
ጊዜ በኋላ በሰጠው ገለጻ፣ ወደ አገሪቱ የተወነጨፉ ስምንት ሚሳዔሎችን ማክሸፉን አስታውቋል።
የዮርዳኖስ ጦር በመግለጫው “ዛሬ ሰኞ ንጋት
ላይ የአገሪቱን የአየር ክልል ጥሰው የገቡ ስምንት ሚሳዔሎች በአየር መከላከያ ስርዓቶች ተጠልፈዋል” ማለቱን ‘ፔትራ' የተሰኘው የመንግሥት
ዜና ወኪል ዘግቧል፥።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም አስጀምረውት
የነበረውን ወታደራዊ ዘመቻ ሐምሌ ላይ ካስቆሙ ወዲህ በሚታወቅ ደረጃ ኢራን ላይ ጥቃት ሲፈጸም የትናንት ምሽቱ የመጀመሪያው ነው።
ላራክ ደሴት ቁልፍ ወደብ ከሆነው ‘ባንዳር አባስ’ ፊት ለፊት የሚገኝ ደሴት ነው። ስፍራው ለዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞ ወሳኝ
በሆነው ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ይገኛል።
በአሁኑ ሰዓት ኢራን በወሽመጡ እንዲያልፉ የምትፈቅድላቸው
ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ለፍተሻ በዚህ ደሴት በኩል እንዲጓዙ ታደርጋለች። መርከቦቹ ወሽመጡን ለማለፍ 2 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ እያስገደደች
መሆኑም ተዘግቧል።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይ ሆሴን
ሞሄቢ ጥቃቱን “በትራምፕ አገዛዝ የተፈጸመ ስልታዊ እና ገዳይ ስህተት” ሲሉ ጠርተውታል። “ጠላት በኢኮኖሚያዊም ሆነ በወታደራዊ
መስኮች የዚህን የተሳሳተ ስሌት መዘዝ ዋጋ ይከፍላል” ሲሉም ተናግረዋል።
ደሴቱ ላይ የተካሄደው ጥቃት የተፈጸመው በድሮን
መሆኑን ከአብዮታዊ ዘቡ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ቀጥሎ ባወጣው መግለጫ፣
በላራክ ደሴት ለደረሰው ምት በተወሰደ የአጸፋ እርምጃ፣ በዮርዳኖስ በሚገኙት ‘ኪንግ ሁሴን’ እና ‘አል አዝራቅ’ የአሜሪካ ጦር
ሰፈሮች ላይ የባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።
በዚህ ጥቃት “ከፍተኛ ጉዳት” ማድረሱን እና
“ቴክኒካዊ መሠረተ ልማቶች፣ የጥገና ተቋማት እና የጠላት ተዋጊ ጄቶች የሚገኙባቸው ስፍራዎችን” ዒላማ ማድረጉን ገልጿል።
አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት ኢራን ላይ በፈጸሙት
ጥቃት የተጀመረው ይህ ጦርነት አድማሱን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አስፍቷል።
ኢራን በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ እስራኤልን፣
የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን እንዲሁም በባሕረ ሰላጤው የሚገኑ የአጋር አገራትን መትታለች። የሆርሙዝ ወሽመጥም ለመርከብ ጉዞ ዝግ ሆኗል።
ጦርነቱ አሁን ስድስተኛ ወሩን አልፏል።