ከኢራን ጋር ባልተቋጨ ጦርነት ውስጥ ያሉት ትራምፕ “ኢራን ተሸንፋለች” አሉ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሠራዊታቸው ባለፉት ወራት በኢራን ላይ በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ኢራን መሸነፏ ግልጽ ነው ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጻፉ።
ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ መድረካቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ በጦርነቱ ኢራን የነበራትን ሁሉንም ነገሮች አጥታ ለሽንፈት ተዳርጋለች ብለዋል።
“ኢራን በይፋ የተሸነፈች ሀገር ናት። አብቅቶላታል። የባሕር ኃይል የላትም፣ የአየር ኃይል የላትም፣ ብሔራዊ ገንዘቧ ዋጋ አጥቷል፣ ለወታደሮቿ እና ለፖሊሶቿ መክፈል አትችልም፣ የዋጋ ንረቱ 300 በመቶ ደርሷል፣ አመራሩም ተበታትኖ አገሪቱን መወከል አይችልም” ብለዋል።
ጨምረውም “ያላቸው ነገር ከአሜሪካ የሚወጣ የሐሰት ዜና እና የራሳቸውን ተቃዋሚዎች የመግደል ፍላጎት ብቻ ነው። ከ100,000 በላይ ሰዎችን ገድለዋል፤ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ የጦር ወንጀል በመፈጸማቸውም ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል” ሲሉ ጽፈዋል።
ትራምፕ ይህንን ይበሉ እንጂ ኢራን ባለፉት ስድስት ወራት ከእስራኤል እና ከአሜሪካ የተፈጸመባትን ጥቃት ተቋቁማ በቀጣናው ባሉ የአሜሪካ ተቋማት ላይ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን እየፈጸመች ነው።
በተጨማሪም ከፍተኛ የነዳጅ ምርት ለዓለም ገበያ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት በዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ጫና ማሳደር ችላለች።
በእርግጥም ኢራን በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ቢሆንም አሁንም ከኃያሏ አሜሪካ ጋር ተፋጥጣ ትገናለች። ጦርነቱን ለማብቃት ድርድሮች እየተደረጉ ቢሆንም ከውጤት ላይ አልደረሱም።
በወታደራዊ እርምጃ የምትፈልገውን ውጤት ያላገኘችው ኢራንን በምጣኔ ሀብት ጫና ለማንበርከክ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር አዳዲስ ማዕቀቦች እና ዕገዳዎችን በኢራን እና በአጋሮቿ ላይ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል።