ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ80 በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገው 'የወንዶች ብልት ስርቆት' ክስ
በአውሮፓውያኑ 2025 ከጥቅምት እስከ ሐምሌ ባሉት ወራት ከ80 በላይ ሰዎች "ብልት ሰርቀዋል" በሚል ሐሰተኛ ክስ ምክንያት መገደላቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል።
የቢቢሲ ዓለም አቀፍ የሐሰተኛ ዜና ክትትል ክፍል በስድስት የአፍሪካ አገራት ውስጥ እነዚህ ሰዎች መገደላቸውን ለማወቅ ችሏል።
የአንድን ግለሰብ ትከሻ በመንካት ብቻ የብልቱ መጠን ሊቀንስ ወይም ሊጠፋ ይችላል የሚል ሐሰተኛ ወሬ በማኅበራዊ ሚዲያ ተሠራጭቷል።
ታንዛኒያዊው የመኪና መካኒክ ቦኒፌስ ምጋላ "የአንድን ሰው ብልት ሰርቃችኋል ብለው እየጮሁብን ነበር። በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ስለነበር ማምለጫ መንገድ አልነበረንም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ የብልት ሌባ ነህ ባሉት ሰዎች የከፋ ድብደባ ተፈጽሞበታል።
ሌሎችም ቢቢሲ የተመለከታቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እንደ ቦኒፌስ ዓይነት ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች ያሳያሉ።
ሰዎች በተሰበሰቡበት ሥፍራ ሳሉ ከማያውቁት ግለሰብ ጋር በተፈጠረ ንክኪ ምክንያት ብልታቸው እንዲሁም የዘር ፍሬ ቋታቸው መጥፋቱን አልያም መጠኑ መቀነሱን የተናገሩ አሉ።
እነዚህ ሰዎች ከሌሎች ጋር በደቦ በመሆን ብልት ሰርቀዋል የተባሉት ግለሰቦች የሰረቁትን እንዲመልሱ በሚል ጥቃት አድርሰዋል።
እንዲህ ያለ አጉል እምነት እና ፍርሃት ለአፍሪካ አዲስ ነገር አይደለም።
በተለይም በጥንቆላ በሚያምኑ ማኅበረሰቦች ዘንድ እንዲህ ያሉ ዕሳቤዎች የተለመዱ ናቸው። ማኅበራዊ ሚዲያ ይሄንን ፍርሃት አጉልቶታል።
አሁን ላይ እየተሠራጨ ያለው ወሬ መነሻው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነው። ይህ ወሬ አምና መሠራጨ ቢጀምርም ከዚህ ቀደምም በአውሮፓውያኑ 2008 ተመሳሳይ ክስተት ነበር።
ወሬው ቀስ በቀስ ወደ ቡሩንዲ፣ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ፣ ሞዛምቢክ፣ አንጎላ፣ ማላዊ እና ኬንያ ተስፋፍቷል።
ታንዛኒያን ከዛምቢያ የምታዋስነው የንግድ ከተማ ምፔምባ የሚኖረው ቦኒፌስ ፊቱ ላይ ያለውን ጠባሳ ይዳብሳል። የገጠመውን አሰቃቂ ጥቃት ያስታውሳል።
"በዚያ ቀን ምን ያህል ለሞት እንደምቃረብ ባውቅ ኖሮ ምግብ ለመብላት ወደ እዚያ ሬስቶራንት አልሄድም ነበር። ሞት ምን ያህል ቅርብ እንደሆነ የምናውቀው ሲደርስብን ነው።"
ከጓደኛው ጋር ምግብ ለመብላት እና ከመኪና ገዢ ጋር ለመገናኘት ነበር ወደ አካባቢው ያመራው።
ምግብ ቤት ውስጥ ተቀምጠው ብዙም ሳይቆዩ ሰዎች ተሰብስበው ከበቧቸው። በደቦ ከምግብ ቤቱ አስወጧቸው።
ጉንጩ ላይ ሁለት ጠባሳ ይታያል፤ ጥርሱም ወልቋል። ድብደባው ሲፈጸምበት ራሱን ስቶ ነበር።
ከሁለት ቀናት በኋላ ራሱን ሆስፒታል ውስጥ አገኘው። ጓደኛው እንደተገደለም ተነገረው።
ቦኒፌስ ከባለቤቱ እና ከአራት ልጆቹ ጋር ይኖራል። ቤቱ ውስጥ እያነከሰ ይሄዳል፤ የማያቋርጥ ራስ ምታት ያሰቃየዋል።
ወደ መካኒክነት ሥራው መመለስ ስላልቻለ ጎረቤቶቹ እና ጓደኞቹ ተባብረው የሕክምና ወጪውን ሸፍነውለታል።
ቦኒፌስ እና ጓደኛው ድብደባ በተፈጸመባቸው ቀን የ23 ዓመቱ ፎቶግራፈር እና ነጋዴ ማይክል ሲላቭዌ ሌሎች ሰዎች ላይም ጥቃት ሲደርስ መመልከቱን ይናገራል።
ቲክቶክ ላይ የተሰረቀ ብልት ቪድዮ መሠራጨቱን ተከትሎ በከተማው ከፍተኛ ውጥረት ነበር።
አንድ ሰው ብልት ሰርቋል መባሉን ተከትሎ በሱቁ አቅራቢያ ሰዎች ሲሯሯጡ አይቷል። ብልት ሰርቋል የተባለው ሰው ተደብድቦ በእሳት ተቃጥሏል።
"ሰውነቱን በእሳት ካቃጠሉት በኋላ ፖሊስ በቦታው ሲደርስ ሰዎቹ ተበተኑ" ይላል።
የቢቢሲ ዓለም አቀፍ የሐሰተኛ ዜና ክትትል ክፍል ያረጋገጠው ተንቀሳቃሽ ምሥል በቲክቶክ እና በፌስቡክ ከ100 ሺህ ጊዜ በላይ ታይቷል።
ሰዎች ተሰብስበው አንድ ግለሰብ የሰረቀውን ብልት ይመልስ ብለው ሲደበድቡት ይታያል።
ማይክል "ነገሩ እየተባባሰ ሄዶ ሰዎችን መደብደብ ቀጠሉ" ይላል።
እንደ እሱ ያሉ ወጣቶች ፈርተው እንደነበር ይናገራል። ወሬው ሐሰተኛ መሆኑንም ማወቅ ችሏል።
የ50 ዓመቷ አሻ ስቲቨን ምዋኪላሳ በቱንዱማ ከተማ ልብስ ትሰፋለች። "ውሸት መሆኑን አውቄያለሁ" ትላለች።
ይህ ግን ፍርሃቷን አይቀንሰውም። ባለቤቷ እና ወንድ ልጆቿ ከቤት ሲወጡ ትጨነቃለች።
አሁን ላይ ፖሊስ ጥበቃውን በማጠናከሩ እፎይታ ተሰምቷታል።
የሞምባ ግዛት ኮሚሽንር ኤልያስ ዳንኤል ምዋንዶቦ ለቢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከአንዳንዶቹ ክስተቶች ጀርባ ሆነ ተብሎ የተቀነባበረ የወንጀል ድርጊት አለ።
"ግለሰቦች ወንጀል ለመፈጸም ተመሳጥረው የሕዝብን ቁጣ ለጥቅማቸው አውለዋል" ይላሉ።
በታንዛኒያ፣ ዳሬ ሰላም የተሠራጨ ተንቀሳቃሽ ምሥል ሰዎች ተሰባስበው አንድን ግለሰብ ሲያባርሩት ይታያል።
ግለሰቡን እየገፈተሩ በመምታት የሰረቀውን ብልት እንዲመልስ ይነግሩታል። ግለሰቡ ምንም ጥፋት እንደሌለበት እየተናገረ ይለምናቸዋል።
ተመሳሳይ ቪድዮዎች በሞዛምቢክ እና ኬንያም መሠራጨታቸውን የቢቢሲ ዓለም አቀፍ የሐሰተኛ ዜና ክትትል ክፍል አረጋግጧል።
በርካታ የደቦ ጥቃት የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ተለቅቀዋል።
ግለሰቦች የግል ተሞክሯቸውን በመጥቀስ በደቦ የሚፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ በቲክቶክ እና በፌስቡክ ቪድዮ አስተላልፈዋል።
ቢቢሲ ከተመለከታቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች አብዛኞቹ አሁንም ድረስ በበይነ መረብ ይገኛሉ።
የሜታ ቃል አቀባይ "የተላኩልንን ይዘቶች እየመረመርን ነው፤ ፖሊሲያችንን የሚጻረሩት ላይ እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቲክቶክ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች ተመልካቾች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳስባሉ። ሐሰተኛውን ወሬ ያምኑበት እንደሆነ ግን ግልጽ አይደለም።
የተመልካች ቁጥር ለመጨመር የሚያደርጉትም ሊሆን ይችላል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የብልት ስርቆትን የሚከላከል ድግምት ሲተዋወቅም ታይቷል። በሌላ በኩል ይሄንን የቀልድ ይዘት አድርገው ቪድዮ የሠሩም አሉ።
ማኅበራዊ ሚዲያ እና ተንቀሳቃሽ ስልክ ሐሰተኛ ወሬ በፍጥነት እንዲሠራጭ እያደረጉ ነው። ሥርጭቱ ከተጀመረ በኋላ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከባድ እንደሆነ ደራሲ ጁልያን ቦንሆም ይናገራል።
'ዘ ሴክስ ቲቭስ፡ ዘ አንቶሎጂ ኦፍ ኤ ሩመር' የተባለው መጽሐፉ 'የወሲብ ሌቦች' የሚለው ወሬ እንዴት እንደተሠራጨ ያትታል።
ሰዎች ብልታቸው ተሰርቋል የሚለው ወሬ ብቻ አይደለም የሚሠራጨው። ብልታችን ተሰርቋል ብለው የተጨነቁ ወንዶች የደረሰባቸውን ሲናገሩም ይደመጣል።
ደራሲው እንደሚለው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ ያልተረጋገጡ ወሬዎች በፍጥነት ስለሚሠራጩ ተዓማኒት ያገኛሉ።
ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁኔታ አንጻር ዲጂታል ዓለም እንዴት ነገሮችን እንደለወጠ ማሳያ ነው ይላል።
ሰዎች በብዛት የተገደሉት በሞዛምቢክ ነው። ፖሊስ እንዳለው ከግንቦት ጀምሮ በስድስት ሳምንታት ውስጥ የፖሊስ ኃላፊ፣ የጤና ባለሙያ እና የመንግሥት ሠራተኞችን ጨምሮ 55 ሰዎች ተገድለዋል።
የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዳንኤል ቻፖ በስፋት እየሠታጨ ያለውን ወሬ እና ግድያ አውግዘዋል።
ወሬው ሐሰተኛ እንደሆነ እና መንግሥት ሰዎች የሰውነት ክፍላቸውን ስለማጣታቸው የሚያረጋግጥ የሕክምና ማስረጃ እንዳላገኘ አስታውቀዋል።
ሁለት የጤና ባለሙያዎች በታንዛኒያ ድንበር በሚገኘው በካቦ ዴልጋዶ ግዛት በቤታቸው እና በሥራ ቦታቸው ሳሉ ጥቃት ደርሶባቸዋል።
አካባቢው የኢስላሚስት ታጣቂዎችም ይፈተናል።
ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማት ለሳምንታት ተዘግረው መንግሥት ሐሰተኛውን ወሬ ለማጥፋት የሕዝብ ግንዛቤ መስጫ ንቅናቄዎች አካሂዷል።
ብልትን የማጣት ፍርሃት የሚፈጥረው የአእምሮ ሕመም (ኮዶ ሲንድረም) አንደኛው የቀውሱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መንግሥት ይፋ አድርጓል።
በቅርቡ በኬንያ በክዋሌ እና ሞምባሳ ግዛት በተፈጸሙ የደቦ ጥቃቶች አምስት ሰዎች ተገድለዋል።
ሐምሌ ላይ የመጀመሪያው ጥቃት ከደረሰ በኋላ የሞምባሳ ከንቲባ መሐመድ ኑር የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች "ተመልካች እና ትኩረት ለማግኘት ሲሉ ብቻ" ወሬውን በማራገብ ኮንነዋል።
"እንዲህ ያለ ሐሰተኛ ወሬ በቀላሉ የሰዎችን ሕይወት ያሳጣል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፖሊስ ነውጡን መቆጣጠር እንደቻለ እና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋለ አክለዋል።
የወንዶችን ብልት ታጠፋለች የተባለች ሴት ላይ ጥቃት ያደረሱ አባት እና ልጅ የአንድ ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።
በማላዊ በዚሁ ሐሰተኛ ወሬ ምክንያት በደቦ በተፈጸሙ ጥቃቶች ስምንት ሰዎች ተገድለዋል።
በታንዛኒያ፣ ቱንዱማ ግዛት ቦኒፌስ ከአካላዊ ጉዳቱ እያገገመ ቢሆንም የሥነ ልቦና ጠባሳው ገና አልሻረም።
"ጓደኛዬ የተገደለበትን ትርጉም አልባ ክስተት ሳስታውስ አሁንም ድረስ ጥልቅ ሕመም ይሰማኛል። ምን እየሆነ እንደነበረ እንኳን አላወቅኩም። ድንገት ያለ ምክንያት በድንጋይ ተወግረህ ሕይወትህን ማጣት ምንድን ነው?"