ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የምንጠቀምባቸው የዓለም ካርታዎች የተሳሳቱ ናቸው? ለምንስ አወዛጋቢ ሆኑ?
የአፍሪካን ትክክለኛ የቆዳ ስፋት የሚያሳይ አዲስ ካርታ በተባበሩት መንግሥታት ጸድቋል።
የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ያጸደቀው "ትክክለኛ ካርታ" በ16ኛው ክፍለ ዘመን በተሠራው የመርኬተር ካርታ ላይ ያለውን የተዛባ የቆዳ ስፋት እንደሚያስተካክል ተገልጿል።
በዚህ ካርታ ላይ የአፍሪካ አገራት የቆዳ ስፋት ከግሪንላንድ ጋር የተስተካከለ ሆኖ ቀርቧል። ሆኖም ግን የአፍሪካ አገራት የቆዳ ስፋት 14 እጥፍ ይበልጣል።
አዲሱ ካርታ አገራት ካላቸው የቆዳ ስፋት ጋር በሚመጣጠን ሁኔታ በካርታ ላይ እንዲወከሉ ያስችላል።
'ኢኳል ኧርዝ' ወይም እኩል መሬት የተባለው አዲሱ ካርታ የራሱ ችግሮች አሉበት።
ዝርግ በሆነ ካርታ ላይ የአገራትን ትክክለኛ የቆዳ ስፋት በሚወክል መንገድ ማስቀመጥ ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ለዓመታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ይህም የራሱ አወንታዊም አሉታዊም ጎኖች አሉት።
አሁን ላይ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው መርኬተር ካርታ በአውሮፓውያኑ 1569 የተሠራ ሲሆን፤ በቤልጂየም የካርታ ባለሙያ ጄራርዱስ መርኬተር የተዘጋጀ ነው።
በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለንደን የካርታ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ጄምስ ቻሺር እንደሚናገሩት፤ የካርታው ዋነኛ ዓላማ አውሮፓውያን ባሕረተኞች ውቅያኖስ ላይ በሚያደርጉት ጉዞ አቅጣጫ ማመላከት ነበር።
"ካርታው ላይ ቀጥተኛ መስመር የዘረጋው በኮምፓስ የታገዘ ጉዞ ሲደረግ መሬት ላይም ቀጥተኛ መስመር ተደርጎ እንዲወሰድ ነው። ይሄንንም ድንቅ በሆነ መንገድ ተግብሯል" ይላሉ።
ዝርግ በሆነው ካርታ ላይ ትክክለኛውን መስመር ለመጠበቅ የመርኬተር ካርታ ከምድር ወገብ ወደ ሰሜን እና ደቡብ ዋልታዎች ያለውን ምጣኔ አስፍቶታል።
ምድር ድቡልቡል በመሆኗ የሚፈጠረውን እጥፋት በካርታው ለመወከል በሚል በምድር ወገብ አቅራቢያ ያሉ አገራት መጠናቸው አነስተኛ እንዲሆን ተደርጓል። ይህም ከቆዳ ስፋታቸው አንጻር ያነሰ ነው።
በሰሜን እና ደቡብ ዋልታዎች የሚገኙ አገራት በአንጻሩ መጠነ ሰፊ ሆነው በካርታው ላይ ይታያሉ።
ዝርግ ወይም ሁለት አውታር (2ዲ) በሆነ ካርታ ላይ የምድርን ትክክለኛ የቆዳ ስፋት በሚያሳይ መንገድ ማስቀመጥ አይቻልም። በዚህም ምክንያት ከቆዳ ስፋት ጋር የማይመጣጠን ውክልና በካርታዎች ላይ ተቀምጧል።
መርኬተር ካርታ ከተሠራ ከ450 ዓመታት በላይ ይሆናል።
በካርታው ላይ ባለው የአገራት አቀማመጥ ምክንያት የተለያዩ አገሮችን ከትክክለኛ የቆዳ ስፋታቸው አሳንሶ መመልከት መፈጠሩን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህም ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዳለው ያስረዳሉ።
ጉግል ማፕስን ጨምሮ በየትምህርት ቤቱ እና በቴሌቭዥን ላይ የሚታየው ካርታ መነሻቸው የመርኬተር ካርታ አከላለል ነው።
በመርኬተር ካርታ ምክንያት አንዳንድ አገራት ከትክክለኛ የቆዳ ስፋታቸው የበለጡ ሆነው ይታያሉ። ትልቅ መሆናቸው ከፍ ያሉ ተደርገው እንዲወሰዱ ማድረጉን ባለሙያዎች ያብራራሉ።
ኬንያዊው የሥነ ምድር ተመራማሪ ኪዎኮ ሙንዱ እንደሚሉት፤ የአፍሪካ መጠነ ሰፊ ሃብት እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮች እና ሕዝቦቿ አነስተኛ ቦታ እንዲሰጣቸው ምክንያት ሆኗል።
"ካርታ ለተጓዦች ጥቆማ ከመስጠት በላይ ጥቅም አለው። ቀጣናዎች በፖለቲካ እና በምጣኔ ሃብት የሚታዩበትን መንገድም ይወስናል" ይላሉ።
'ኢኳል ኧርዝ' ካርታ ይሄንን የተዛባ አካሄድ ለማረም ይሞክራል።
በአውሮፓውያኑ 2018 በካርታ ባለሙያዎች የተረቀቀው ካርታው፤ ከአገራት ትክክለኛ የቆዳ ስፋት ጋር የሚመጣጠን እንደሆነ ተገልጿል።
በ1963 የተሠራው የሮቢንሰን ካርታን መነሻ ያደረገ ነው። ይህ ካርታ ዓለምን በአንድ ዕይታ ያሳያል።
'ኢኳል ኧርዝ' ካርታ ያለፈው ጥር በአፍሪካ ኅብረት ተቀባይነት አግኝቷል።
ይህ ካርታ በመርኬተር ካርታ ያለውን ቀጥተኛ መስመር ያጠፋል። ይህ ቀጥተኛ መስመር አቅጣጫን በትክክል ለማወቅ የሚረዳ ነበር።
አዲሱ ካርታ በተለያዩ ሥፍራዎች መካከል ያለውን ትክክለኛ ርቀት ለመለካት ጥቅም ላይ መዋል አይችልም።
ፕሮፌሰር ጄምስ "አንድን አካባቢ መወከል ወይም ቅርጹን ማሳየት አልያም ደግሞ ርቀትን ወይም አቅጣጫን ማሳየት ነው የሚቻለው። ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ በትክክል ማድረግ አይቻልም" ይላሉ።
ፒተርስ የዓለም ካርታ የተሠራው በጀርመናዊው የታሪክ ተመራማሪ አርኖ ፒተርስ በ1970ዎቹ ነው።
ስኮትላንዳዊው የካርታ ባለሙያ ጄምስ ጋል በ1855 የሠራውን ካርታ መነሻ ያደረገ አራት መዓዘን ያለው ካርታ ነው።
ትኩረቱ የቅርጽ ትክክለኛነት ሳይሆን የምጣኔ ትክክለኛነት ላይ ነው። ስለዚህም የሰሜን እና ደቡብ ዋልታ አካባቢዎች መጠናቸው አንሶ፤ የምድር ወገብ ተለጥጧል።
ይህም የአፍሪካ እና የግሪንላንድን ትክክለኛ የቆዳ ስፋት ያላመጣጠነውን ካርታ ችግር ይቀርፋል። አገራቱ ያላቸውን የቆዳ ስፋት ለመገመትም ይረዳል።
ካርታው ቀጥተኛ እና አግድም መስመርን የተከተለም ነው።
ሆኖም ግን የምድርን ትክክለኛ መጠን የሚወክል አይደለም። ለምሳሌ ሩሲያ የተሳለችው ከትክክለኛ የቆዳ ስፋቷ ባነሰ መጠን ነው።
ፒተርስ ካርታ ኮምፓስን ተከትሎ ለሚደረግ ጉዞ ጥቅም አይሰጥም።
ከአንድ የተመረጠ ማዕከላዊ ቦታ አንጻር የዓለም ክፍሎችን በእኩል ርቀት ላይ ያስቀምጣል።