የነዳጅ ዋጋ በሳምንት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ
አሜሪካ በኢራን ላይ ዳግም ጥቃት በመክፈቷ ያገረሸውን የጥቃት ምልልስ ተከትሎ እየጨመረ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ዛሬ ሰኞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ባለፉት ቀናት አሜሪካ እና ኢራን በፋርስ ባሕረ ሰላጤ በሚተላለፉ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን፣ ይህም በወሳኙ የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ቁጥርን በከፍተኛ መጠን ቀንሷል።
ዛሬ ጠዋት በምሥራቅ እስያ በዋለው የነዳጅ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የአሜሪካ ጥቃት ከመጀመሩ በፊት ከነበረበት ወደ 10 ዶላር ያህል ጭማሪ አሳይቷል።
የነዳጅ ዋጋ መተመኛ በሆነው ብሬንት የነዳጅ ዓይነት በሰኞ ጠዋት አንድ በርሜል ዋጋው ወደ 97 ዶላር ተጠግቷል።
በኢራን እና አሜሪካ መካከል እየተካሄደ ያለው አዲሱ የወታደራዊ ግጭት ባለፈው ሳምንት ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎ በነበሩት ቀናት በተመሳሳይ አንድ በርሜል ነዳጅ 86 ዶላር ገደማ ነበር።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከፍተው ጦርነቱ በቀጠለበት ባለፉት ስድስት ወራት የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ መጥቷል።
ለዚህም ምክንያቱ ኢራን የተከፈተባትን ጥቃት ተከትሎ የዓለም 20 በመቶ የነዳጅ ፍጆታ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷ ነው።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ እንደተናገሩት አሜሪካ እና እስራኤል በአገራቸው ላይ "ወረራ ከመክፈታቸው በፊት ሆርሙዝ ሙሉ በሙሉ ክፍት ነበር። አሜሪካ ሕገ ወጥ እና ጨካኝ ጦርነት በመክፈቷ መደበኛው የባሕር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል" ብለዋል።
በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ በሚፈጸመው ጥቃት ምክንያት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ለመቆም የተገደዱ ሲሆን በዚህም ምክንያት የነዳጅ እና ሌሎች ምርቶች ዋጋ ዋጋ በእጅጉ አሻቅቧል።