ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ በግዛት ደረጃ ምርጫ አሸነፈ
የጀርመኑ 'አልተርናቲቭ ፎር ጀርመኒ' (ኤኤፍዲ) ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በክልል ደረጃ ወደ ሥልጣን የወጣ የመጀመሪያው ቀኝ አክራሪ የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆን ተቃረበ።
ቀኝ አክራሪው ፓርቲ በምሥራቃዊ ጀርመን ሳክሶኒ አንሃልት ግዛት ከሚገኙ ተቀናቃኞቹ እጅግ የበለጠ ድምፅ በማግኘት ወደ አስገራሚ አሸናፊነት እያመራ ነው።
አብዛኞቹ የምርጫ ጊዜያዊ ውጤቶች እንደሚያመለክቱት ፓርቲው 44 በመቶ ድምፅ በማግኘት 17 በመቶ ድምፅ በማግኘት ተከታይ ከሆነው 'ሲዲዩ' የተሰኘው ወግ አጥባቂ ፓርቲ ቀዳሚነቱን ይዟል።
ፓርቲ ያገኘው ድምፅ በክልሉ አብላጫውን ለመቆጣጠር እንደማያስችለው ትንበያዎች ያሳያሉ፤ ይሁን እንጂ ፓርቲው የአስተዳዳሪነት ሥልጣኑን ማሸነፉን አስታውቋል።
በግዛቱ የፓርቲው መሪ የሆኑት ኡልሪች ሲግመንድ ውጤቱን "አስደናቂ" ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ በተቻለ ፍጥነት አካባቢውን ማስተዳደር መጀመር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የትኛውም የቀኝ አክራሪ ፓርቲ የአንድን የጀርመን ግዛት መንግሥት ተቆጣጥሮ አያውቅም። በግዛት ደረጃ የሚመሠረት አስተዳደር በፖሊስ፣ በአካባቢው ትምህርት እና በባህል ጉዳዮች ላይ ሥልጣን ይሰጣል።
'ኤኤፍዲ' ቀዳሚ ድምፅ ያገኘበት ሳክሶኒ አንሃልት ግዛት 2.1 ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች ያሉበት ባለ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ግዛት ነው።
በግዛቱ የሚገኘው የፓርቲው ቅርንጫፍ "ቀኝ አክራሪ ጽንፈኛ" በሚል በጀርመን የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ግምገማ ተደርጎበታል። በግዛቱ የፓርቲ አመራር የሆኑት የ35 ዓመቱ ሲግመን ይህንን ፍረጃ ውድቅ አድርገውታል።
ተንታኞች እና ተቃዋሚዊ ፖለቲከኞች የምርጫ ውጤቱን እጥፋት እና ካለፈው ታሪክ መነጠል የተፈጠረበት ነጥብ ሲሉ ገልጸውታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጀርመን ቴሌቪዥን የተላለፈውን የውጤት ግምት 'ስክሪሻት' ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አጋርተዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት መልዕክተኛ ኪሪል ዲሚትሪቭ ደግሞ የትራምፕን ልጥፍ በድጋሚ በማጋራት "ተራማጅ የሆነው ኤኤፍዲ ያገኘው ታሪካዊ ድል" በማለት አድንቀዋል።
ዲሚትሪቭ ከዚህ ቀደም ዲሚትሪየቭ ለሩሲያ የወዳጅነት ስሜት ያለውን ኤኤፍዲ "የተስፋ እና የምክንያታዊነት፣ የትብብር፣ የእውነት እና የጀርመን ተስፋ ፓርቲ" በማለት አሞካሽተውት ነበር።
ባለፈው ዓመት የጀርመን የፌዴራል ምርጫ ከመደረጉ አስቀድሞ ደግሞ፣ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ለፓርቲው ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ይህ የጄዲ ቫንስ እርምጃ እንደ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በመቆጠሩ ጀርመን ውስጥ ወቀሳ አስነስቶ ነበር።
ኤኤፍዲ 83 መቀመጫ ካለው የግዛቱ ፓርላማ ውስጥ ያሸነፈው 39 ወንበር ነው። መንግሥት ለመመሥረት ደግሞ 42 መቀመጫዎችን ማሸነፍ ያስፈልጋል።
ፓርቲው በግዛቱ አብላጫ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል በቂ መቀመጫ ባያገኝም፣ የፓርቲው አመራር የሆኑት ኡልሪች ሲግመንድ ግን ጥምር መንግሥት የመመሥረት ፍላጎት የላቸውም።
በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙት የፓርቲው መሪዎች በበኩላቸው አናሳ ድምፅ ካገኙ ሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን መንግሥት መመሥረቱን አንደ አማራጭ ይመለከቱታል።
ሲግመንድ በግል ከተወዳደሩ የፓርላማ አባላት ወይም ከአንድ ፓርቲ ጋር አብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ "አስፈላጊ ከሆነ አዲስ ምርጫ ይካሄዳል፤ ያኔ ደግሞ 50 ወይም 55 በመቶ እናገኛለን" ብለዋል።