ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ በህወሓት መሪዎች ለቀረበባቸው ቅሬታ ምላሽ ሰጡ
የትግራይ ጦርነትን ያበቃው የፕሪቶሪያ ስምምነት አሸማጋይ የሆኑት የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መሪዎች ገለልተኛ አይደሉም በሚል ለቀረበባቸው ክስ ምላሽ ሰጡ።
የትግራይ ክልል አስተዳደርን ተቆጣጥረው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ፍጥጫ ውስጥ የገቡት የህወሓት መሪዎች እሁድ ዕለት ባወጡት መግለጫ የቀድሞውን የናይጄሪያ መሪ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የገለልተኛ አደራዳሪነት መርኅ አልታየባቸውም በማለት ወቅሷል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየተባባሰ በነበረበት ጊዜ ኦባሳንጆ ባለፈው ነሐሴ አጋማሽ በድንገት ወደ መቀለ ሄደው ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር ንግግር አድርገው እንደነበር ይታወሳል።
ይህንንም በማስመለክት የትግራይ ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ ላይ "በቅርቡ... በኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኩል የማደራደሩ ሂደት እንደገና ሊጀመር መሆኑን የሚያመለክት የይምሰል ድራማዎች ለመፍጠር የተደረገ ጥረት ታይቷል" በማለት እንቅስቃሴው "በራሳቸው ተነሳሽነት ወይስ በብልፅግና ትዕዛዝ ነው የሚል ከባድ ጥያቄን እያስነሳ ይገኛል" ብሏል።
ኦባሳንጆ ለቀረበባቸው ወቀሳ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ ላይ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ባለሥልጣናት መካከል የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ የፕሪቶሪያን ስምምነት የሚጥሱ ሙከራዎች እንዲሁም "ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጠብ ጫሪ" ሁኔታዎች መታየታቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲጀምሩ ምክንያት እንደሆናቸው ጠቅሰዋል።
ነገር ግን ህወሓት ባወጣው መግለጫ የፕሪቶሪያው ስምምነት በአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የመልዕክተኞች ኮሚቴ እና በቁልፍ ዓለም አቀፍ አጋሮች የአፈጻጸም ሂደቱን ሳይተገበር መተዉን እና የስምምነቱን ዕጣ ፈንታ በአብዛኛው በፌዴራል መንግሥቱ ውሳኔ ላይ ጥገኛ እንዲሆን ተደርጓል በማለት አሸማጋዩ ኦባሳንጆ ላይ ጥያቄ አንስቷል።
ኦባሳንጆ የጀመሩት የማሸማገል ጥረት የትግራይ ባለሥልጣናት በሂደቱ ገለልተኝነት፣ ነጻነት እና አደራዳሪው ጉዳዩን ከምር በመያዛዘቸው ላይ ጥያቄ እስካነሱበት የባለፈው እሁድ መግለጫ ድረስ በተሳካ ሁኔታ ሲካሄድ እንደነበር ጠቅሰዋል።
የትግራይ ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ ኦባሳንጆ ሰኔ ወር ላይ ንግግር እንደገና ስለማስጀመር ጥልቅ ውይይት አድርገው እንደነበር እና ከሁለት ሳምንታት በኋላ እንደሚመለሱ ቃል ቢገቡም ሁለት ወራት ዘይግይተዋል ብለዋል።
ለዚህም ምክንያታቸው "የብልፅግና አገዛዝ ባለሥልጣናት ብሔራዊ የውይይት ጉባኤውን እስኪጨርሱ ድረስ እንዲጠብቁ ያዘዟዋቸው መሆኑን ተናግሯል" በማለት "ይህንን መመሪያ ተቀብሎ የሽምግልና ሂደቱን ለማራመድ ምንም ዓይነት ግልጽ ተነሳሽነት አላሳዩም" በማለት ወቅሰዋል።
ኦባሳንጆ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ ላይ ለቀረቡባቸው ወቀሳዎች በሰጡት ምላሽ በማሸማገል ሂደታቸው ከፌደራል መንግሥቱ ትዕዛዝ እንደማይቀበሉ እና "ትኩረትን ለማግኘት ጥንቃቄ የሚፈልጉ እና ምሥጢራዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ኃላፊነት የጎደለው ነው" ብለዋል።
በተጨማሪም አንዳንድ የህወሓት አመራሮች ለራሳቸውን አጀንዳ እንዲመች የኦባሳንጆን ጥረት ለማጣጣል ሲሞክሩ የአሁኑ የመጀመሪያው እንዳልሆነ በመጥቀስ በፕሪቶሪያው ድርድር ወቅትም ተመሳሳይ ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል ብለዋል።
በህወሓት መሪዎች በኩል የቀረበባቸው ኦባሳንጆ ለአንድ ወገን ያደላሉ የሚለው ክስ እስካሁን ያከናወኑትን ጥረት እና ውክልናቸውን የሚያዛባ መሆኑን በመግለጽ፣ ኦባሳንጆ በድርድር ሂደት የአንድ ወገን ፍላጎትን በሌላው ላይ መጫን ውጤት እንደማያስገኝ የሚገነዘቡ መሆናቸውን አስምረውበታል።
"በአንድ ግጭት ውስጥ የቀረቡ ፍላጎቶች ተቀባይነት ካላገኙ ወይም አንድ ወገን የሚጠብቀውን ካልተሳካ መፍትሄው አደራዳሪውን ማጥቃት ወይም አቋሙን ጥያቄ ውስጥ መክተት ሳይሆን፣ አስማሚ ነጥብ ላይ እስኪደረስ ንግግርን መቀጠል ነው" በማለት መክረዋል።
ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የሰላም ጥረት ቁርጠኛ አቋም እንዳቸው እንዲሁም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራው የሰላም ጥረት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አመለክተው፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ሌላ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ የሁሉንም ወገኖች እርምጃ በቅርበት እንዲከታትል ጥሪ አቅርበዋል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ተፈርሞ የሁለት ዓመቱን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት አራተኛ ዓመቱን ይይዛል።
ድርድሩን በአፍሪካ ኅብረት ተሰይመው ለወራት ሲያካሂዱ የነበሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ሲሆኑ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮችም ተሳታፊ ነበሩ።
ጦርነቱ ከቆመ በኋላ በፌደራል መንግሥቱ አማካይነት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ የነበረ ሲሆን ባለፉት አራት ዓመታት በስምምነቱ መሠረት መፈጸም የነበረባቸው በርካታ ጉዳዮች ተግባራዊ አለመሆናቸውን ሁለቱም ወገኖች ሲያነሱ ቆይተዋል።
ነገር ግን በሚያዚያ ወር መጨረሻ ላይ የህወሓት መሪዎች የክልሉን ጊዘያዊ አስተዳደር ሥልጣን በመቆጣጠር ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ውዝግብ ውስጥ ከመግባታቸው በተጨማሪ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ማድረጋቸው ውጥረቱን አባብሶት ቆይቷል።
ከዚያም በኋላ በሁለቱም ወገን ወታደራዊ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸው ከመዘገቡ በተጨማሪ በተወሰኑ ስፍራዎች ላይ ግጭቶች እና በርካታ የድሮን ጥቃቶች ተካሂደዋል።
ይህም በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሮ ምዕራባውያን አገራት፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ስጋታቸውን በመግለጽ ሁለቱም ወገኖች አለመግባባታቸውን በንግግር እንዲፈቱ እየጠየቁ ነው።