የፕሪቶሪያ አደራዳሪው ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በትግራይ ክልል "ድንገተኛ ጉብኝት" ማድረጋቸው ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ከፕሪቶሪያ ስምምነት አደራዳሪዎች አንዱ የሆኑት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ትናንት ሰኞ በትግራይ "በድንገተኛ ጉብኝት" ማድረጋቸውን ህወሓት የሚመራው የክልሉ አስተዳደር አስታወቀ።

ህወሓት መሩ አስተዳደር ከፌደራል መንግሥት ጋር ውይይት ለመጀመር "መሠረታዊ እና ቁልፍ" ናቸው ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል።

ሰኞ ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም. የተደረገው የኦባሳንጆ ጉብኝት "አስቀድሞ በመደበኛ መርሃ ግብር እና በቀጠሮ የተያዘ" እንዳልነበረ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው አስተዳደር ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና በዶ/ር ደብረጽዮን መካከል የተደረገው ውይይት በህወሓት እና በፌደራል መንግሥት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ማርገብ ላይ ያተኮረ እንደነበር መግለጫው ያመለክታል።

የህወሓት መሩ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረጽዮ፣ ባለፈው ሰኔ ኦባሳንጆ ወደ መቀለ በተጓዙበት ወቅት በተደረገው "ውይይት መሠረት ትርጉም ያለው ክትትል እና ቁጥጥር ባለመደረጉ ደስተኛ እንዳልሆኑ" እንደገለጹላቸው ተጠቅሷል። "ሁኔታውም ወደ የከፋ ውጥረት" ማምራቱንም አንስተዋል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም ከተደረገው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት የትግራይ ክልል ጉብኝት በኋላ፣ ነሐሴ ላይ የፌደራል እና የትግራይ ኃይሎች "ሸረሪና" በተባለ የሱዳን አዋሳኝ ሥፍራ ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።

በዚህ ወርም ትናንትን ሰኞ ነሐሴ 18 ቀንን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶች እንደተፈጸሙ የትግራይ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የፌደራል መንግሥት ግጭቱንም ሆነ የድሮን ጥቃቶቹን በተመለከተ እስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጠም። ይሁን እንጂ የህወሓት አመራሮች በአገር ውስጥ ካሉ ታጣቂዎች እና የውጭ አካላት ጋር 'ፅምዶ' የተባለ ጥምረት እንደመሠረቱ በመግለጽ ከስሷል።

የህወሓት አመራሮችም ባደረጓቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ፌደራል መንግሥትን "ስለማስወገድ" ያንጸባረቁን አቋም ውጥረቱን ያባባሰ ሆኗል።

የህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል አስተዳደር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ የፌደራል መንግሥት "በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ እና እውነተኛ ማሻሻያዎች" አለማድረጉን በመጥቀስ ከስሷል።

"ላለፉት አራት ዓመታት" የታየውን "የማይፈጸሙ ቃል ኪዳኖችን" ያሉበት እንዲሁም "መሬት ላይ ሁኔታው ከመጥፎ ወደ የባሰ እየተለወጠ የሚሄድበትን አካሄድ እንደገና ለመድገም ምንም ዓይነት ፖለቲካ ፍላጎት እንደሌለው" ገልጿል።

ዶ/ር ደብረፅዮን፣ ከፌደራል መንግሥት ጋር ውይይት የሚጀመር ከሆነ መመለስ ስላለባቸው "መሠረታዊ እና ቁልፍ" ጉዳዮች ለኦባሳንጆ ገልጸዋል ተብሏል።

ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል "የኢኮኖሚ ማዕቀብና እገዳ መነሳት" እንዲሁም "ወታደራዊ ከበባን ማቆም እና የተፈጠረውን ውጥረት ማርገብ" የሚሉት ይገኙበታል።

"የትግራይ ሉዓላዊ ግዛት ወደ ነበረበት መመለስ"፣ "የተፈናቃዮች ደኅንነታቸው እና ክብራቸው በተጠበቀ መንገድ መመለስ" እንዲሁም የህወሓት "ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ ማንነት መመለስም" በቅድመ ሁኔታነት ተቀምጠዋል።

አስተዳደሩ ከፌደራል መንግሥት ጋር የሚደረግ ውይይት "የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት" እንዲሁም "ግፊት መፍጠር የሚችሉ ዋነኛ ዓለም አቀፍ አጋሮች" የሚሳተፉበት መሆን እንዳለበት ገልጿል።

መግለጫው፣ "የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆ 'ከፌደራል መንግሥት ጋር ተወያይቼ በሚቀጥሉት አንድና ሁለት ሳምንታት እመለሳለሁ'" ማለታቸውን ጠቅሷል።

ወደ መቀለ የተጓዙት የፕሪቶሪያ ስምምነት አደራዳሪው ኦባሳንጆ ስለ ትግራይ ክልል ጉብኝታቸው በይፋ አስተያየት አልሰጡም።

ይሁን እንጂ ኦባሳንጆ ወደ መቀለ ከመጓዛቸው አስቀድሞ ቅዳሜ ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው በአገራዊ ምክክር ጉባኤ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። "ግጭት እና ጦርነቶች፣ አመጽ እና የደኅነንት እጦት" በሙሉ "በቃን" ሊባሉ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ኦባሳንጆ በግንቦት መጀመሪያ የአፍሪካ ኅብረት "በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፉ" በኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ መሾማቸው ይታወሳል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ካሸማገሉት መካከል ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ አንዱ ናቸው።

ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን ባለማክበር እና በመጣስ እየተካሰሱ የቆዩ ሲሆን፣ ከወራት በፊት ደግሞ የህወሓት መሪዎች በስምምነቱ የተመሠረተውን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር አስወግደው ከተቆጣጠሩ በኋላ ውጥረቱ ተባበስሶ ወደ ግጭት ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።