ትራምፕ የ'ኦንታሪዮ' ሐይቅን ስም መቀየራቸውን ተከትሎ፣ ካናዳ ነባሩን ስያሜ የያዘ ግዙፍ ቢልቦርድ አቆመች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ ከካናዳ ጋር የምትጋራውን 'ኦንታሪዮ' ሐይቅ ስያሜ የሚቀይር ሕግ መፈረማቸውን ተከትሎ፣ የኦንታሪዮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳግ ፎርድ በሐይቁ ዳርቻ ላይ "ኦንታሪዮ ሐይቅ፤ አሁንም ሁልጊዜም" የሚል ግዙፍ ቢል ቦርድ ሰቀሉ።

ትራምፕ ሐሙስ ዕለት የፈረሙት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የሐይቁ ስም ወደ 'የአሜሪካ ሐይቅ' (ሌክ አሜሪካ) የሚቀይር ነው። ፕሬዝዳንቱ ቀጥለውም በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ የሚገኘውን ይህንን ሐይቅ የተመለከቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተሠሩ ቪዲዮዎችን በተከታታይ ለጥፈዋል።

የኦንታሪዮ ጠቅላይ ሚኒስትር ፎርድ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ [ከመምጣታቸው] ረጅም ጊዜ በፊትም ይህ ሐይቅ ሌክ ኦንታሪዮ ተብሎ ይጠራ ነበር። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሄዱም ከረጅም ጊዜ በኋላም አሁንም ሌክ ኦንታሪዮ ተብሎ ይጠራል" ብለዋል።

ይህ የቃላት ጦርነት የተጀመረው፣ አሜሪካ እና ካናዳ ሲያደርጉ የነበረው የንግድ ድርድር ከፈረሰ በኋላ ነው። ይህንን ተከትሎም አሜሪካ 20 ቢሊዮን ዶላር በሚያወጡ የካናዳ ምርቶች ላይ አዲስ የ50 በመቶ ታሪፍ ጥላለች። ካናዳ ደግሞ ከሚቀጥለው ወር አንስቶ "እኩል በእኩል" የሆኑ የአጸፋ ታሪፎችን በአሜሪካ ምርቶች ላይ እንደምትጥል አስታውቃለች።

ትራምፕ የሐይቁን ስያሜን 'ሌክ አሜሪካ' ለመቀየር የፈረሙት ትዕዛዝ ወዲያውኑ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ምንም እንኳ ትራምፕ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ስፍራዎችን ስያሜ መቀየር የሚችሉ ቢሆንም፣ ሌሎች አገራት ስያሜውን የመከተል ግዴታ የለቸባቸውም። የካናዳ ባለሥልጣትም የትራምፕን እርምጃ ውድቅ አድርገውታል።

ፕሬዝዳንቱ ቅዳሜ ዕለት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ካጋሯቸው በርካታ በኤአይ የተሠሩ ቪዲዮዎች አንዱ፣ 'ሌክ ኦንታሪዮ' ቢልቦርድን በእግራቸው መትተው ሲጥሉ እና በምትኩ 'እንኳን ወደ ሌክ አሜሪካ በሰላም መጣችሁ' የሚል ሰሌዳ ሲሰቅሉ ያሳያል።

ሌላ ቪዲዮ ደግሞ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዓይነት ፀጉር ያላቸው እና ጠመንጃ የያዙ የካናዳ ዝይዎች 'ሌክ አሜሪካ' የሚል አዲስ ስም በወጣለት ሐይቅ ዙሪያ ሲሰማሩ አሳይቷል።

የኦንታሪዮ ጠቅላይ ሚኒስትር ፎርድ፣ ትራምፕ ሐይቁን ስም የቀየሩት "ኦንታሪዮ እና ካናዳ ለራሳቸው መቆማቸው ስላልተመቻቸው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ በተሰቀለው 'ሌክ ኦንታሪዮ' የሚል ቢልቦርድ ፊት ለፊት ቆመው ባደረጉት ንግግርም "ምናልባት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወይም ሌላ ሰው ረስቶት እንደሆን በሚል ለማስታወስ ይህንን ሰሌዳ አቁመናል። አሁንም ለዘላለምም ኦንታሪዮ ሐይቅ ነው" ብለዋል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒም በተመሳሳይ "ነገሮች በስማቸው መጠራት አለባቸው። ይህ ሐይቅ አሁንም ሆነ ለዘላለምም ኦንታሪዮ ሐይቅ ተብሎ ይጠራል" ብለው ነበር።

ኦንታሪዮ፣ ሁሮን፣ ሚቺጋን እና ኢሪ የተባሉት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙት አራት ታላላቅ ሐይቆች ስያሜያቸውን ያገኙት ከቀደም የአካባቢው ነዋሪዎች ቋንቋ ነው። 'ሱፔሪየር' ተባለው አምስተኛው ሐይቅ ደግሞ መነሻው ፈረንሳይኛ በሆነ እና ወደ እንግሊዝኛ በተቀየረ ቃል ተሰይሟል።

ከእነዚህ ታላላቅ ሐይቆች ትንሹ የሆነው 'ሌክ ኦንታሪዮ' ከካናዳ ኦንታሪዮ ግዛት እና ከአሜሪካ ኒው ዮርክ ግዛት ጋር ይዋሰናል።