አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ ቁልፍ አጋሮቿ የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ ልታቋርጥ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አሜሪካ የእስላማዊ መንግሥት ቡድንን (አይኤስ) ለማሸነፍ የረዷትን ቁልፍ የመካከለኛው ምሥራቅ አጋሮቿን ወታደራዊ ድጋፍ ለማቋረጥ ማቀዷን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ምንጮቹ እነዚህ የአሜሪካ አጋሮች ከኢራን የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑንም አብራርተዋል።

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር በኢራቅ ከፊል ራስ ገዝ ግዛት ለሆነችው የኩርዲስታን ክልል መሪዎች አስተዳደሩ ለኩርድ የጸጥታ ኃይል - ፔሽመርጋ ድጋፍ ለማድረግ የገባውን ስምምነት ለማደስ ዕቅድ እንደሌለው ይፋ አድርጓል።

ቢቢሲ በውይይቱ ላይ ከተሳተፉ ሁለት ባለሥልጣናት እንዲሁም ስለጉዳዩ ቀጥተኛ እውቀት ካላቸው ሌሎች ሁለት ምንጮች መረጃዎችን ሰብስቧል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት እነዚህ ምንጮች ስለድጋፉ መቋረጥ ሲያስረዱ ዝርዝር መረጃዎች ይፋ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

የኩርድ ባለሥልጣናት የገንዘብ ድጋፉ መቀነስ የኃይል ክፍተትን እንደሚፈጥር እና በኢራቅ ወደሚገኙ የኩርዲስታን ግዛት በርካታ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ላስወነጨፈችው ኢራን የልብ ልብ የሚሰጥ እንደሚሆን ያላቸውን ስጋት ጨምረው አስረድተዋል።

ለፔሽመርጋ የሚደረገውን የደኅንነት ድጋፍ ማቆም በኢራቅ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የአሜሪካ አጋር የነበሩትን ያዳክማል ሲሉ ተንታኞች ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አሜሪካ በአካባቢው ያሉትን አጋሮቿን በመደገፍ ረገድ እምነት ሊጣልባት እንደማይችል መልዕክት ያስተላልፋል ሲሉ ተንታኞቹ አስረድተዋል።

"አሜሪካ በኢራቅ እና በሰፊው መካከለኛው ምሥራቅ ግቧን ለማሳካት ብዙ ደም ያፈሰሱትን ኩርዶችን መደገፍ ልታቆም ትችላለች" ሲሉ በአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ኩርዲሽ ኢኒሼቲቭ ፎር ፒስ ዳይሬክተር የሆኑት ዬሬቫን ሰኢድ ተናግረዋል።

"ኩርዶች ያለ ደጋፊ ከቀሩ ለኢራን፣ ለቻይና እና ለሩሲያ ትልቅ ድል ይሆናል" ብለዋል።

ትራምፕ በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው እንደ መካከለኛው ምሥራቅ ባሉ ቀጣናዎች አሜሪካ የምታደርገውን ወታደራዊ ተሳትፎ ለመቀነስ ቃል ገብተዋል እንዲሁም አርብ ዕለት ስድስተኛ ወሩን የያዘውን ጦርነት አስጀምረዋል።

በፔንታጎን እና በኩርድ ክልላዊ መንግሥት መካከል የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት የሚያበቃው እአአ መስከረም 30 ሲሆን፣ አሜሪካ እና ሌሎች አገራት የቀሩትን ወታደሮቻቸውን ከኢራቅ የሚያስወጡት በዚሁ ዕለት ነው።

የሠራዊቱ መውጣት በአይኤስ ላይ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻ በይፋ ያስቆማል።

በዚህ ዘመቻ የፔሽመርጋ ታጣቂዎች ከጥምር ጦሩ ወታደሮች ጋር በመተባበር አይኤስ የኢራቅ እና የሶሪያን ግዛቶችን መቆጣጠር እንዳይችል ተዋግተዋል።

በኢራቅ ኩርድ ዋና ከተማ ኢርቢል የሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያም የጥምር ጦሩ ወታደሮች ከወጡ በኋላ በሚቀጥለው ወር ይዘጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በኢራቅ ኩርዲስታን 180,000 ወታደሮች ያሉት ፔሽመርጋ እአአ በ2026 የበጀት ዓመት ለጦር መሣሪያዎች እና ለወታደራዊ ስልጠና የ61 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝቷል።

ፔንታጎን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ለ2027 የበጀት ዓመት ባቀረበው የበጀት ጥያቄ መሠረት የቡድኑ የጸጥታ ድጋፍ በሙሉ እንዲቋረጥ ሐሳብ አቅርቧል።

የፔንታጎነ ውሳኔ በኢራቅ ኩርዲስታን ግዛት ድንጋጤ የፈጠረ ቢሆንም፣ ባለሥልጣናቱ አሜሪካ የአሁኑን ስምምነት በማራዘም ድጋፏን ትቀጥላለች የሚል ተስፋ ሰንቀው ነበር።

የባለሥልጣናቱ ስጋት የጨመረው ኢራን በኢራቅ በሚገኙ ኩርዶች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃቶችን አጠናክራ በመቀጠሏ ነው።

ኢራን እና በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች በግንቦት መጨረሻ በኢራቅ ኩርዲስታን ውስጥ 158 የሚሳኤል ወይም የድሮን ጥቃቶችን ፈጽመዋል ሲል በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ፋውንዴሽን ፎር ዲፌንስ ኦፍ ዴሞክራሲስ አመልክቷል።

የጥቃቶቹ ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም በቅርቡ ከኢራቅ እና ከኩርድ መሪዎች ጋር የተወያዩ የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት አገራቸው የመግባቢያ ስምምነቱን ለማራዘም ዕቅድ እንደሌላት መናገራቸው ስለውይይቱ የሚያውቁ በርካታ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፔንታጎን እአአ በ2016 ለፔሽመርጋ ወታደራዊ ድጋፍ የሚሰጥ የመጀመሪያውን የመግባቢያ ስምምነት ፈርሞ በ2022 ደግሞ አድሶታል።

የፔንታጎንን ውሳኔ የሚያውቁ አንድ ምንጭ የአሜሪካ ወታደሮች ከወጡ በኋላ በኢራቅም ሆነ በኢራቅ ኩርዲስታን የተወሰነ የጸጥታ ድጋፍ ለማድረግ አማራጮችን እየታዩ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢራቅ የሚገኙ የኩርዲስታን መሪዎች በጉዳዩ ላይ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ቢቢሲ ለዋይት ሐውስ ጥያቄ ቢያቀርብም በሐምሌ ወር የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት ከኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር አሊ አል ዛይዲ ጋር ያደረጉት ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሷል።

በወቅቱ የወጣው መግለጫ "ዩናይትድ ስቴትስ፣ ኢራቅ እና የጥምር ጦሩ አጋሮች አይሲስን በማሸነፍ ከፍተኛ ስኬት አስመዝግበዋል፤ አሁን ደግሞ የኢራቅ የጸጥታ ኃይሎች፣ ፔሽመርጋን እና ሌሎች የኢራቅ ኩርዲስታን ክልል የጸጥታ ኃይሎችን በኢራቅ ውስጥ አሸባሪዎችን መዋጋትን በበላይነት ይቆጣጠራሉ" ይላል።

ለፔሽመርጋ የሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍ የሚያበቃው አሜሪካ በዓለም ላይ ትልቁን ቆንስላ ፅ/ቤት በኢርቢል ከከፈተች ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።