በሳዑዲ ነሐሴ ላይ ብቻ ቢያንስ 60 ኢትዮጵያውያን ከዕፅ ጋር በተያያዙ ጥፋቶች መያዛቸውን ዘገባዎች አመለከቱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ከዕፅ ጋር በተያያዙ ጥፋቶች የሚፈረደቸባው ሰዎችን በሞት እየቀጣች ባለችው ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ፣ በነሐሴ ወር ብቻ ጫትን ጨምሮ የተለያዩ ዕፆችን በማጓጓዝ የተጠረጠሩ ቢያንስ 60 ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዘገባዎች አመለከቱ።

ትናንት ረቡዕ ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም. ተጨማሪ 15 ኢትዮጵያውያን ከ290 ኪሎ ግራም ጫት ጋር መያዛቸው ተዘግቧል።

የሳዑዲ የድንበር ጥበቃ ጠቅላይ ዳይሬክቶሬት፣ 12ቱ ኢትዮጵያውን በቁጥጥር ስር የዋሉት ጃዛን እና አስሪ በተባሉት ግዛቶች ውስጥ በተካሄዱ ሦስት ዘመቻዎች እንደሆነ 'ሳውዲ ጋዜት' የተባለው አገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

ሪያድ ግዛት ውስጥ ደግሞ የተከለከለ መድኃኒት ሲያስታዋውቁ ነበሩ የተባሉ ሌሎች ሦስት ኢትዮጵያውን መያዛቸውን የ'አልሪያድ' ዘገባ ያሳያል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ ሳዑዲ አረቢያ ከዕፅ ጋር በተያያዙ ክሶች ምክንያት በተፈረደባቸው ኢትዮያውያን ላይ ተከታታይ የሞት ቅጣት እየፈጸመች ባለበት ወቅት ነው።

ባለፉት ሐምሌ እና ሰኔ ወራት በቀናት ልዩነት ኢትዮጵያውያን ላይ የሞት ቅጣቶች ተፈጻሚ ሆነዋል። ከጥር ወዲህ ቢያንስ 17 ኢትዮጵያውያን በሞት መቀጣታቸውን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች 'ሂውማን ራይትስ ዎች' ሐምሌ ላይ አስታውቋል።

በአሁኑ ሰዓትም 200 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የሞት ቅጣት ተፈርዶባቸው እስር ላይ እንደሚገኙ በስፍራው የሚገኙ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሳዑዲ ባለሥልጣናት ከዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች የጠረጠሯቸው ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ሥር ማዋል ቀጥለዋል።

ለአገሪቱ መንግሥት ቅርበት ባለው 'ሳዑዲ ጋዜት' እና 'አልሪያድ' ላይ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከነሐሴ 2/2018 ዓ.ም. አንስቶ በዘጠኝ ዘመቻዎች 60 ኢትዮጵያውያን ተይዘዋል።

ኢትዮጵያውያኑ የተያዙት እንደ ጫት፣ ሀሺሽ እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ክኒኖችን ለማስገባት በመሞከራቸው እንደሆነ ዘገባዎቹ ያመለክታሉ። ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአሲር እና ጃዛን ግዛቶች ነው።

ትናንት በእነዚህ ሁለት ግዛቶች ውስጥ መያዛቸው የተገለጸው ኢትዮጵያውያን፣ 290 ኪሎ ግራም ጫት፣ 33 ኪሎ ግራም ሀሺሽ እና 72,415 የሕክምና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ክኒኮችን ወደ አገሪቱ ሊያስገቡ ነበር የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በሦስት ዘመቻዎች በተያዙት ኢትዮጵያውያን ላይ "የመጀመሪያ ደረጃ ሕጋዊ ሒደት" እንደተጠናቀቀ እንዲሁም ተጠርጣሪዎቹ ለሚመለከተው አካል እንደተላለፉ ባለሥልጣናት መግለጻቸውን ሳዑዲ ጋዜት ዘግቧል።

29,430 ክኒን ይዘው ትናንት እንደተያዙ የተገለጸው ሦስት ኢትዮጵያውያንም ጉዳያቸው ወደ ዐቃቤ ሕግ መመራቱን አልሪያድ አስነብቧል።

ኢትዮጵያውያኑ ምን ዓይነት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ግልፅ አይደለም። ይሁን እንጂ ሳዑዲ ውስጥ ባለፈው ዓመት የሞት ቅጣት ከተፈጸመቸባው 365 ሰዎች ውስጥ 68 በመቶው ፍርዱ የተላለፈባቸው ከዕፅ ጋር በተያያዙ ጥፋቶች እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው እና ፍርዱ እስከሚፈጸምባቸው እየተጠባበቁ ያሉ አብዛኛው ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ጥፋቶች እንደተፈረደባቸው ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ሐምሌ ላይ በሞት የተቀጡት አምስት ኢትዮጵያውያንም "አደንዛዥ ዕፅ በድብቅ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲያስገቡ" እንደተያዙ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ገልጿል።

ሞት ከተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን መካከል የተወሰኑት ዕፅ ይዘው የተገኙት "ተታልለው" እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌሎች ደግሞ "በአዘዋዋሪዎች ቃል በሚገባላቸው የገንዘብ ስጦታ እና ሌሎች ተስፋዎች በመሳብ" እንደ ጫት ያሉ በሳዑዲ ሕግ የተከለከሉ ዕፆችን ይዘው ሲገቡ እንደሚያዙ ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ በአገሪቱ የሚገኙ ሁለት ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።

እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟቾች ሳዑዲ አረቢያ የምትፈጽመውን የሞት ቅጣት አውግዘዋል። ሂውማን ራይትስ ዎች፣ ገዳይ ካልሆነ ዕፅ ጋር በተያያዘ የሞት ፍርድ ሂደት የሚተላለፍበት ሕጋዊ ሂደት ላይም ጥያቄ አንስቷል።

በተቋሙ የሳዑዲ አረቢያ ተመራማሪ የሆኑት ጆይ ሼአ "ሳዑዲ ባለሥልጣናት የተገለሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በሞት እየቀጡ ያሉት አንዳንድ ጊዜ ጠበቃ ወይም አስተርጓሚ ባልተገኘበት ለጥቂት ደቂቃዎች በሚቆይ የችሎት ሂደት ነው" ማለታቸው ሐምሌ ላይ በወጣው መገለጫ ላይ ተጠቅሷል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በእስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የቀረበባቸውን ክስ ለመቃወም ወይም በጠበቃ በኩል ለመከራከር ዕድል እንዳልተሰጣቸው እንዲሁም የይግባኝ ሂደት እንዳልተመቻቸላቸው ገልጸዋል።

አንድ ኢትዮጵያዊ፤ "በመጀመሪያው ቀን ዳኛ ፊት ስትቀርብ 'በዚህ ወንጀል ተከሰኻል፤ ክሱን ትቀበላለህ?' ብሎ ይጠይቅሃል። ለሁለተኛ ጊዜ ስትቀርብ ደግሞ የሞት ፍርድ ይፈርድብሃል። ከዚያ በኋላ የምትከላከልበት ወይ ይግባኝ የምትልበት ዕድል የለም" ሲል አስረድቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ጉዳያቸው "የሕግ ሂደት ላይ ያሉ እና የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው" የአገሪቱ ዜጎችን በተመለከተ "ከሚመለከታቸው" የሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር "በቅርበት እየተነጋገረ" መሆኑን ሐምሌ ላይ አስታውቆ ነበር።

ሳዑዲ ውስጥ ፍርድ የተላለፈባቸው በአጠቃላይ 1,971 ኢትዮጵያውያን ንጉሳዊ ምሕረት እንዲያገኙ ማድረጉንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።