የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳዑዲ ስለተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር "በቅርበት እየተነጋገረ" መሆኑን ገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ "የሕግ ሂደት ላይ ያሉ እና የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው" ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ "ከሚመለከታቸው" የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር "በቅርበት እየተነጋገረ" መሆኑን አስታወቀ።

በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚገኙባት ሳዑዲ አረቢያ ከጥር እስከ ሰኔ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ሰባት ኢትዮጵያውያንን በሞት መቅጣቷን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሦስት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሐሚስ ሙሻይት በተባለው እስር ቤት ብቻ ቢያንስ 63 ኢትዮጵያውያን ደግሞ የሞት ፍርድ ተላልፎባቸው እየተጠባበቁ መሆኑን አምነስቲ እና ሌላኛው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ "ኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ አገር ለሚገኙ ዜጎቹ ደኅነት፣ ጥበቃ እና የቆንስላ እገዛ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ" ጠቅሷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት "የሕግ ሂደት ላይ ያሉ እና የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው" ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ከሳዑዲ ጋር "በከፍተኛ የመንግሥት ደረጃ መነጋገር እንደቀጠለ" ገልጿል።

በተጨማሪም ሪያድ ውስጥ በሚገኘው ኤምባሲ እና በጅዳ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት አማካኝነት "አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለገጠሟቸው የኢትዮጵያውያን ዜጎች ሰብአዊነትን ከግምት ያስገባ" እርምጃ እንዲወሰድ የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን ገልጿል።

በዲፕሎማሲያዊ ቢሮዎቹ አማካኝነት ኢትዮጵያውያኑ "የቆንስላ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እና ተገቢውን መፍትሔ ለማስገኘት ከሚመለከታቸው የሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር መደበኛ ግንኙነት እና ገንቢ ውይይት" እየተካሄደ መሆኑንም ጠቅሷል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚገልጸው፤ ጥረቶች ሳዑዲ ውስጥ ፍርድ የተላለፈባቸው በአጠቃላይ 1,971 ኢትዮጵያውያን ንጉሳዊ ምሕረት እንዲያገኙ አስችለዋል። እነዚህን ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የመመለስ ተግባር መጀመሩንም በመግለጫው አንስቷል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያውያኑ ምህረት እንዳገኙ ከአንድ ወር በፊትም አስታውቆ ነበር። መስሪያ ቤቱ ይህንን በገለጸበት ሳምንት ደግሞ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት አራት ኢትዮጵያውያን ላይ የሞት ፍርድ መፈጸሙን ገልጿል።

የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው ኢትዮጵያውያን አብረዋቸው የነበሩ ሰዎች ላይ ፍርዱ ሲፈጸም እየተመለከቱ ጭንቅ ውስጥ መግባታቸውን ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያኑ ለሞት ፍርደ ያበቃቸው "የሕግ ሂደት ተገቢውን መንገድ" ያልተከተለ እንደሆነ በማንሳት ይከስሳሉ።

የሂውማን ራይትስ ዎችም ሚያዝያ ላይ ባወጣው መግለጫ ይህንን ጠቅሷል። የተቋሙ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ናዲያ ሃርድማን "ሳዑዲ አረቢያ መሠረታዊ የሕግ ሂደትን በሌለባቸው [ፍርዶች አማካኝነት] የኃይል ድርጊት በሌለባቸው ወንጀሎች የተከሰሱ የውጭ ስደተኞችን ስደተኞችን ለሞት ለመቅጣት ፈቃደኛ መሆኗ መብቶቻቸውን እና ሕይወታቸውን እንደማታከብር ያንጸባርቃል" ብለዋል።

ዛሬ መግለጫ ያወጣው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን "ጥቅም፣ መብት እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ እና የቆንስላ አማራጮችን በሙሉ መጠቀም እንደቀሚጥል" አስታውቋል።