ኢዜማ ከአገራዊ ምክክሩ ጋር በተያያዘ አምስት ማሳሰቢያዎች ሰጠ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአገራዊ ምክክሩ ላይ ከተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ በቀጣይ የምክክር ሂደቱ ምዕራፎች መተግበር አለባቸው ያላቸውን አምስት ማሳሰቢያዎች ይፋ አደረገ።

ኢዜማ፣ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ ተመካካሪዎች በሙሉ ድጋፍ ያልፈረሙባቸውን ምክረ-ሐሳቦች እንደማይቀበል ጨምሮ አስታውቋል።

4000 ተመካካሪዎችን አሳትፎ ከሐምሌ 8 ጀምሮ ከአንድ ወር በላይ የተካሔደው እና በርካታ ጥያቄዎች የተነሱበት የምክክር ሂደት ቅዳሜ ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም. በተካሔደ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ተጠናቅቋል።

ምክክሩ ቢጠናቀቅም፣ ኮሚሽኑ የመጨረሻውን ምክረ ሐሳቦች ለመንግሥት እና ለሕዝብ የሚያቀርቡበት እንዲሁም የትግበራ ሂደቶች እንደሚቀሩ ያነሳው ኢዜማ፣ እነዚህ ሁለት "ዋና ምዕራፎች በጥንቃቄ እንዲያዙ" ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

ፓርቲው በማሳሰቢያው ከጠቀሳቸው አምስት ነጥቦች ቀዳሚው፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለመንግሥት እና ለሕዝብ የሚያቀርበው "በንባብ የቀረበውን የተመካካሪዎችን የመጨረሻ ምክረ-ሐሳብ ብቻ" መሆን እንዳለበት የሚገልፅ ነው። ኮሚሽኑ ምክረ-ሐሳቦችን በሚያቀርብበት ወቅት፣ በአጠቃላይ የምክክሩን መንፈስ ባከበረ መልኩ እንዲሆንም አሳስቧል።

"ኮሚሽኑ በተመካካሪዎች የቀረቡትን 400 ምክረ-ሐሳቦች ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ" የሚለው ሌላው የኢዜማ ማሳሰቢያ ነው።

ይህንንም በምክክሩ ሒደት ከጥቃቅን ቡድኖች ጀምሮ የተደረጉ ውይይቶች ቃለ ጉባዔዎች በማገናዘብ እንዲከወን እና በማቋቋሚያ አዋጁ መሠረት የምክረ-ሐሳቦቹን አፈፃፀም እንዲከታተል አስገንዝቧል።

የአገራዊ ምክክሩ ሂደት ውጤታማ የሚሆነው የቀረቡት ምክረ-ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጉ እንደሆነ የጠቀሰው ፓርቲው፣ አፈፃፀሙም ከተገቢው በላይ ጊዜ እንዳይወስድ መንግሥት በፍጥነት እንዲፈፅም አሳስቧል።

የምክክሩን ምክረ-ሐሳቦችን አተገባበር የሚከታተል ገለልተኛ እና ሕጋዊ አካል አንዲቋቋምም ኢዜማ በመግለጫው ጠይቋል።

ፓርቲው ማሳሰቢያውን በሰጠበት መግለጫው፣ ሀገራዊ ምክክሩ በይፋ ከተጀመረበት ሐምሌ 08/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው "ረጅም እና እልህ አስጨራሽ" ሂደት ውስጥ "በርካታ ስልታዊ ማነቆዎች እና አሠራርን ያላከበሩ ችግሮች" ማጋጠማቸውን ገልጿል።

ሆኖም ጉዳዩን ወደ አደባባይ ከማውጣት ይልቅ ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ቅሬታዎቹን በተደጋጋሚ ሲያቀርብ መቀጠሉን የገለፀ ሲሆን፣ ይህም "ሂደቱ እንዳይበላሽ በማሰብ" ያደረገው መሆኑን ነው የጠቀሰው።

አንዳንድ በኤክስፐርትነት እና በአስተባባሪነት ስም የተመደቡ አካላት በምክክሩ ሂደት "ግልጽ ወገንተኛነት እና የተዛባ አካሄድ" ማንፀባረቃቸው፣ በሂደቱ ላይ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል መሆናቸውን በማንሳት፤ በርካታ ችግሮችን ከኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመወያየት እንዲፈቱ ማድረጉን አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የምክክር ሂደቱን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ሁለት የኮሚሽኑ አባላት ጣልቃ ገብተዋል ሲል ክስ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ኮሚሽኑ ግን አስተባብሏል።

ኢዜማ በመግለጫው፣ በስምንቱ የምክክር ቡድኖች ውስጥ የነበሩ ተመካካሪዎች "በውይይት አጎልብተውት፣ በሙሉ ድጋፍ ፈርመውበት ለጠቅላላው ጉባኤ ያቀረቧቸውን ምክረ-ሐሳቦች ብቻ የሚቀበላቸው" መሆኑን ይፋ አድርጓል።

በአጠቃላይ በሀገራዊ ምክክሩ የነበረውን ሂደት ከነጉድለቶቹም ቢሆን እንደ መልካም ጅምር እንደሚወስድ የገለፀው ኢዜማ፣ ይህ ሂደት ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ የመፍታት ልማድ እንዲዳብር አዲስ በር እንደሚከፍት ያለውን እምነት ገልጿል።

በምክክር ሂደቱ ላይ በተለይ አዲስ አበባ ከተማን በተመለከተ የአካሔድ ግድፈቶች ተስተውለዋል በሚል በርካታ ቅሬታዎች መነሳታቸው ይታወቃል። በአጠቃላይ ከቀረቡት 400 ምክረ-ሐሳቦች ውስጥ አራት ጉዳዮች የልዩነት ምክረ-ሐሳብ ሆነው ቀርበዋል።

በመዝጊያው ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ምክረ-ሐሳቦቹ "ወደየሚላኩበት ቦታ ይላካሉ" ብለዋል።

ከአራት ዓመታት በላይ ዋና ዋና በተባሉ አወዛጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ ሲካሄድ የነበረው ጥረት አጀንዳዎችን እና ተወያዮችን ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ አሰባስቦ የመጨረሻው ምክክር አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል።

አራት ሺህ የሚሆኑ ተሳታፊዎች በስምንት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከአንድ ወር በላይ የተካሄደው ሀገራዊ ምክክር በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት በመድረስ ተጠናቋል።

ሂደቱን በተመለከተ የተለያዩ ወገኖች የድጋፍ እና የተቃውሞ ሐሳባቸውን ሲገልጹ የነበረ ሲሆን፣ በምክክሩ የተደረሰው ውጤት ለሚመለከታቸው አካላት ቀርበው ቀጣይ ሂደታቸውን በተመለከተ ውሳኔ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።