ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከምድር በታች በሚገኝ ጥልቅ ሥፍራ ለሚሊዮን ዓመታት የኖረው 'የዲያቢሎስ ትል'
መሬትን በጥልቅ ቆፍረን የምድር ውስጠኛ ከፍል (ክረስት) የሚባለው ላይ ብንደርስ የምንመለከተው ነገር ምቾት የሚሰጥ አይሆንም።
የፀሐይ ብርሃን እየጠፋ ሲሄድ እና የቀለጠ አለት ወደ ሚገኝበት የምድር እምብርት ስንጠጋ የሙቀት መጠኑ እና ግፊቱ እየጨመረ ይሄዳል።
ነገር ግን ከመሬት በታች በ1.3 ኪ.ሜ ጥልቀት ውስጥ ሕይወት ያለው ነገር አይገኝም ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል።
በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ትሎች አንዳንድ ጊዜ ደማቅ ብርቱካናማ ወይም ነጭ ምንጣፎችን ፈጥረው ይገኛሉ። በአጉሊ መነጽር ሲታዩም ትንሽ ትል በአፉ ላይ ሹል ነገሮችን በመጠቀም ሲንቀሳቀስ ይታያል።
ይህ ሃሊሴፋሎበስ ሜፊስቶ (Halicephalobus mephisto) ወይም 'ዲያብሎስ ትል' በመባል የሚታወቀው ሲሆን ረቂቅ ተሕዋስያንን ለማግኘት ይሯሯጣል።
ምንም እንኳን ቅንጣት የሚያክል ቢሆንም በሚኖርበት ሥነ ምኅዳር ውስጥ ዓሣ ነባሪ ማለት ነው። በሚሞትበት ወቅትም አካሉ ለትሎች እና ለሌሎች ሕይወት ላላቸው ነገሮች ምግብነት ይውላል።
ይህም የዚህን ትል የሕይወት ዑደት ለማስቀጠል ይረዳል።
እንደ አውሮፓውያኑ ከ1980ዎቹ በፊት፣ አብዛኛዎቹ የሥነ ሕይወት ባለሙያዎች ሕይወት ከመሬት 30 ሴንቲ ሜትር በታች ይኖራል ብለው አያስቡም ነበር።
በ2011 የዲያብሎስ ትል (devil worm) መገኘት የምድርን ጥልቀት በመረዳት የመጣውን ዕውቀት ለውጦታል።
የደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ጥቃቅን ነፍሳትን የሚያጠኑት (ጂኦማይክሮባዮሎጂስት) የሆኑት ካረን ሎይድ "እዚያ ትል ማግኘት ከቻልን ሌላ ምን የማናውቀው ነገር አለ?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
ተመራማሪዎች ከአንድ ነጠላ ትል ሌሎችን መፍጠር ችለዋል። አሁን ዝርያዎቹ በሞቃታማው እና በጨለማው ጥልቅ የመሬት ክፍል ውስጥ እንዴት እንደሚኖሩ ለመረዳት ጥናት አድርገዋል።
ወደ መሬት ማዕከል ዘልቆ በመግባት መመራመር
በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ፣ በቤልጂየም የሚገኘውን የምርምር ተቋም የመሠረቱት የሥነ ሕይወት ባለሙያ ጋኤታን ቦርጎኒ፣ በዕድሜ የገፉ ሳይንቲስቶች በምድር ሆድ ውስጥ የበለጠ ውስብስብ ነገር ሊኖር ይችላል በሚለው ሀሳብ ላይ ሲያፌዙ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የመጀመሪያዎቹ በጥልቅ ከርሰ ምድር ውስጥ የተገኙ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሚመለከት የታተሙ የጥናት ውጤቶች ግን የእነዚህን ተመራማሪዎች ጥርጣሬ ውድቅ ያደረገ ነው።
ለምሳሌ እአአ በ1997 በጋዝ ጉድጓድ ውስጥ በ2.8 ኪ.ሜ ጥልቀት ላይ ባክቴሪያዎች ተገኝተዋል።
ቦርጎኒ ከትል ዝርያዎች መካከል አንዱ የሆኑት ኔማቶድ የሚባሉ ትናንሽ ትሎች በጥልቅ የመሬት ክፍል ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ ያምኑ ነበር።
ሀሳቡ ወድያውኑ ተቀባይነት የሚያገኝ አልነበረም፤ ነገር ግን ቦርጎኒ ትንንሽ እንስሳት ምን ያህል ጠንካራ እንደሆኑ ስለተገነዘቡ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።
በአውሮፓውኑ 2008 ቦርጎኒ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን የቢያትሪክስ የወርቅ ማዕድን ለመጎብኘት ከሌሎች ልምድ ካላቸው ተመራማሪዎች ጋር ሄዱ።
ቦርጎኒ ለማዕድን ማውጫ የተቆፈሩ ትልቅ ጉድጓዶች ውስጥ ውሃ እንዲያልፍ በማድረግ ትናንሽ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታትን ለማግኘት ሞክረዋል። ከ6,000 ሊትር በላይ ውሃ ከተጠቀሙ በኋላ አንድ ትንሽ ትል አግኝተዋል።
በሁለት ሌሎች የደቡብ አፍሪካ ማዕድን ማውጫዎች፣ ከ12 ሚሊዮን ሊትር በላይ ውሃ ተጠቅመው የተለያዩ የትል ዝርያዎችን፣ ከሌሎች አከርካሪ አጥንት ከሌላቸው እንስሳት፣ ፈንገሶች እና በርካታ ጥቃቅን ፍጥረታት ጋር አግኝተዋል።
አብዛኛዎቹ ዝርያዎች ምድር ላይም ይታወቃሉ፤ ነገር ግን በቢያትሪክስ ማዕድን ማውጫ ሥፍራ ጭራዋ ተቆርጦ የተገኘችው ትል ለሳይንስ አዲስ ስለነበረች ሃሊሴፋሎበስ ሜፊስቶ ተብላ ተሰይማለች።
የተቆረጠ ጅራት ለራውንድ ወርም የሞት ፍርድ ማለት ነው። ግን እንደ ዕድል ሆኖ ትሏ ሴት ነበረች። በተጨማሪም ያለምንም ወንዴ ዝርያ መራባት የምትችል በመሆኗ ከመሞቷ በፊት ስምንት እንቁላሎችን ጥላለች።
አንዳንድ የትል ዝርያዎች በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ በሆኑት በጆን ብራክት ላብራቶሪ መግባት ችለዋል። እዚህ ልክ እንደ የዲያብሎስ ትል ዘመድ እንደሆነው ካይኖርሃብዲቲስ ኤሌጋንስ (Caenorhabditis elegans) በጥንቃቄ እንዲያድጉ ይደረጋል።
የዲያቢሎስ ትል እየተባለ የሚታወቀው ፍጥረት በውሃ ውስጥ አይዋኝም። ይልቁንም በፕላስቲክ ቱቦ ጎኖች ላይ ይጣበቃል፣ ይህም ምናልባት ከመሬት በታች ባሉ ድንጋዮች ላይ እንዲጣበቅ ረድቶታል።
በጣም የሚያስደንቀው ነገር የዲያብሎስ ትል በአነስተኛ ሙቀት ውስጥ ለመኖር ይቸገራል። በ20 ዲግሪ ሴልሺየስ እድገቱ ይቀንሳል እና የሕይወት ዑደቱን ለማጠናቀቅ ስምንት ቀናት ብቻ ይወስዳል። ለመኖር 37 ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጠንን ይመርጣል።
ብዙውን ጊዜ ይህንን ያህል ሞቃት የሆኑ አካባቢዎች የካይኖርሃብዲቲስ ኤሌጋንስን የሚገድሉ ናቸው። ነገር ግን በዚያ የዲያብሎስ ትል በየሁለት ቀኑ ያለምንም ችግር ተመችቷቸው የሚራባበት ነው።
ለመኖር ራስን ማላመድ
የአንድን ትል ዝርያ በተለይም ለረጅም ጊዜ ከተገኙበት አገራቸው ርቀው የቆዩትን ብቻ በመመርመር ማጥናት ከባድ ነው፤ ነገር ግን አንድ ትል ከመሬት በታች እንዴት በሕይወት ሊኖሩ እንደቻሉ ፍንጮችን አግኝተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2019 የዲያብሎስን ትል ዲኤንኤ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ሲያጠኑ ሙቀትን የሚለዩ ፕሮቲኖችን የሚያመነጩ እጅግ በጣም ብዙ ዝርያዎችን አግኝተዋል። እነዚያም ሌሎች ፕሮቲኖችን በከፍተኛ የሙቀት መጠን ከሚመጣ ጉዳት የሚከላከሉ ሞለኪውሎች ናቸው።
በ2024 የብራችት ቡድን ሳይቶክሮም ኦክሲዳዝ ሲ የተባለ ሌላ ሞለኪውል በቅርበት አግኝተዋል፤ ይህም ኦክስጅንን ለመመገብ እና ሕይወትን ለማቆየት አስፈላጊ ነው።
በተከታታይ ሙከራዎች አማካኝነት የዲያብሎስ ትል ሳይቶክሮም ኦክሲዳዝ ሲ በከፍተኛ ሙቀት ብቻ እንደሚሠራ ተረድተዋል።
በመደበኛ ሙቀት ውስጥ ሞለኪውሉ ይዘጋል፣ ይህም የኃይል ማመንጨትን ያቀዘቅዛል። ትሎቹ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ለምን በጣም ቀርፋፋ እንደሆኑ ያብራራል።
ብራችት ያ በትሉ ዘረ መል ውስጥ የታየው የሞለኪውሉ መለዋወጥ በሕይወት እንዲኖር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል እንደሚሆን ያስረዳሉ። "በተሻለ የሙቀት አካባቢ የበለጠ እንዲራቡ ይረዷቸዋል" ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ የዲያብሎስ ትል ያለ ወንዴ ዘር ለመራባት የቻለው ሕይወትን ለማስቀጠል የሚያደርገው ትግል አካል መሆኑን ለማወቅ ምርምር እያደረጉ ነው።
የዲያብሎስ ትሎች ብዙውን ጊዜ ከመሬት በታች ጥልቅ በሆነ ሥፍራ በብዛት መሰሎቻቸውን የማግኘት ዕድላቸው ጠባብ ነው።
በዚህም የተነሳ ከግንኙነት ውጭ ራሳቸውን ለማራባት አስገድዷቸው ሊሆን ይችላል።
ምናልባት የዲያብሎስ ትል ወንዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህም ከሴቲቱ ጋር ግንኙነት እንዲፈጠር ያግዛል፤ ነገር ግን እስካሁን ድረስ የትሉን ወንዴ ዝርያ ማግኘት አለመቻሉን ብራችት አብራርተዋል። ያም ሆነ ይህ ትሎቹ በሕይወት ለመቆየት ምን ያህል ተለዋዋጭ መሆናቸውን አሳይተዋል።
"ምግብ ባገኙበት ቦታ ሁሉ [ክብ ትሎች] በዚያ ለመኖር ራሳቸውን ያላምዳሉ።"
'የዲያቢሎስ ትል' እንዴት በጥልቅ የመሬት ክፍል ውስጥ ሊኖር ቻለ?
እነዚህ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት እንዴት ወደዚያ ጥልቅ የመሬት ክፍል ሊደርሱ እንደቻሉ እንቆቅልሽ ነው።
ከስዊትዘርላንድ የመጡት ቦርጎኒ እና የጂኦባዮሎጂ ባለሙያዋ ካራ ማግናቦስኮ ያካሄዱት ጥናት እንደሚያሳየው፣ አንዳንድ ክብ ትሎች ከምድር ገጽ ወደ ጥልቅ የመሬት ክፍሎች በውሃ አማካኝነት ይጓዛሉ። የመሬት መንቀጥቀጥ መሬቱን በማናወጥ እነዚህን ትሎች ወደ ጥልቅ ለማንቀሳቀስ ሊያግዝ ይችላል።
በሌላ በኩል ብዙዎቹ ባክቴሪያዎች ለረጅም ጊዜ በጥልቅ የመሬት ክፍል ውስጥ ኖረው ሊሆን ይችላል። በ2021 በቻይና የጥልቅ ባሕር ሳይንስ እና ምህንድስና ተቋም የጂኦማይክሮባዮሎጂስት ማጊ ላው እና ባልደረቦቻቸው ያደረጉት ጥናት በሦስት የተለያዩ አህጉራት ውስጥ በጥልቅ ምድር አካባቢዎች የሚገኘው ዴሱልፎሩዲስ አውዳክስቪዬተር የተባለው ባክቴሪያ በጄኔቲክ መልኩ ተመሳሳይነት እንዳለው አረጋግጠዋል። ይህ የትል ዝርያ በላይኛው የመሬት ክፍል ላይ መኖሩ አልተረጋገጠም።
ተመራማሪዋ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ባክቴሪያው በመሬት ጥልቅ ውስጥ ከሚሊዮን ዓመታት ጀምሮ መኖር እንደጀመረ ይገምታሉ።
"እንደ ሰዎች፣ ዓለምን የምንገዛው እኛ እንደሆንን እናስባለን፤ ግን አይደለንም" ይላሉ ቫን ሄርደን።
"እዚህ ለቢሊዮኖች ባይሆንም ለሚሊዮኖች ዓመታት መኖራቸውን ማወቅ ለእኔ እጅግ በጣም ዐይን ገላጭ ነው። እዚህ ለረዥም ጊዜ እንደሚቆዩ መረዳት መቻሌም በጣም አስደስቶኛል።"