በአሜሪካ ቴነሲ ግዛት የሚገኘውን ናሽቪል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዶሊ ፓርተን ስም ለመሰየም ታቀደ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአሜሪካዋ የቴነሲ ግዛት አስተዳዳሪ ቢል ሊ፣ የናሽቪል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን በዚህ ሳምንት ሕይወቷ ባለፈው የአገረ ሰብ ሙዚቃ ኮከብ ዶሊ ፓርተን ስም ለመሰየም ማቀዳቸውን አስታወቁ።

ይህ የተሰማው በርካታ የፓርተን አድናቂዎች አውሮፕላን ማረፊያው በእርሷ ስም እንዲሰየም ፊርማ ካሰባሰቡ በኋላ ነው።

በካንሰር በሽታ በ80 ዓመቷ ሕይወቷ ያለፈው ዶሊ ፓርተን የተወለደችው በቴነሲ ግዛት የገጠር አካባቢ ሲሆን በኋላ ላይ ወደ ዋና ከተማዋ ናሽቪል ተዛውራ እስከ ዕለተ ሞቷ በዚያው ኖራለች።

ሊ በሰጡት መግለጫ የፓርተን ቡድንን እንዳነጋገሩ ጠቅሰው፣ ዶሊን ለማክበር ላደረጉት ያልተለመደ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

"የዶሊ ፓርተን አስደናቂ ሕይወት በግዛታችን ሕያው ሆኖ ይኖራል" ብለዋል።

" ቴነሲ ዓለምን የምትቀበልበት ቦታ የግዛታችንን ተወዳጅ ልጅ ስም እንዲይዝ እና መንገደኞች በዶሊን ሙዚቃ፣ ልግስና፣ እምነት እና ደግነት አሻራዎች መቀበል ተገቢ ነው" ሲሉም ገዥው አርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የአውሮፕላን ማረፊያውን ስም ለመቀየር ፊርማ ማሰባሰብ የተጀመረው እአአ በጥር 2025 የነበረ ሲሆን ዶሊ ካረፈች በኋላ ጥያቄው በድጋሚ ተነስቷል። በዚህም እስከ አርብ ምሽት ድረስ ወደ 160 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ፊርማቸውን አሰባስበዋል።

ፊርማ ማሰባሰቢያው አየር ማረፊያው በስሟ መሰየሙ "ልዩ ብቃቷን እና የሰጠችውን ብርሃን በቴነሲ እና በመላው ዓለም ለማሳየት የሚረዳ ድንቅ መንገድ ነው" ሲል ይገልጻል።

ቢቢሲ በዚህ ላይ የዶሊ ፓተርንን ፋውንዴሽን አስተያየት ቢጠይቅም ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

የገዥው ቢሮ እንደገለጸው ስያሜው የናሽቪል አውሮፕላን ማረፊያ ባለሥልጣናት ቦርድ ድጋፍ የሚያስፈልገው ሲሆን ቦርዱ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር መስከረም 17 ስብሰባ ያካሂዳል።

የመጨረሻው ውሳኔም በፌደራል አቪየሽን አስተዳደር መጽደቅ ይኖርበታል።

አሜሪካ ሉዊስ አርምስትሮንግ ኒው ኦርሊያንስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና በኬንተስኪ የሚገኘውን ሉውስቪል መሐመድ አሊ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በታዋቂ ሙዚቀኞች እና ሌሎች ዝነኞች ስም የተሰየሙ በርካታ አውሮፕላን ማረፊያዎች አሏት።

በልዩ የድምፅ አወጣጧ፣ ልብ በሚነኩ ግጥሞቿ እና በተለዩ ውብ አልባሳቷ የምትታወቀው ፓርተን የግራሚ ሽልማትን 10 ጊዜ አሸንፋለች።

እንደ 'ኮት ኦፍ ሜኒ ከለርስ'፣ '9 ቱ 5' ፣ 'ጆሊን' እና 'አይ ዊል ኦልዎይስ ላቭ ዩ' ያሉ ሙዚቃዎቿ በዓለም አቀፍ ደረጃ 100 ሚሊዮን ቅጂዎች የተሸጡ ሲሆን በኢንተርኔት ከአንድ ቢሊዮን በላይ ዕይታዎችን አግኝተዋል።