ቀጥታ , ዢ፣ ፑቲን እና ትራምፕ ከ90 ደቂቃ ውይይት በኋላ የሦስትዮሽ ‘የጋራ የሰላም መግለጫ’ አወጡ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ለ90 ደቂቃ ከተወያዩ በኋላ የሦስትዮሽ “የጋራ የሰላም መግለጫ” አውጥተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዢ፣ ፑቲን እና ትራምፕ የሦስትዮሽ ‘የጋራ የሰላም መግለጫ’ አወጡ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ለ90 ደቂቃ ከተወያዩ በኋላ የሦስትዮሽ “የጋራ የሰላም መግለጫ” አውጥተዋል።

    የጋራ መግለጫው “የኒውክሌር ጦርነትን ማሸነፍ አይቻልም፤ መቼም ቢሆን ውጊያው መካሄድ የለበትም” ይላል።

    አገራቱ የተጣራ የነዳጅ ምርት መጠንን ለመጨመርም ቃል ገብተዋል።

    ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ፑቲን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጻ፤ ኪቭ እና አውሮፓ የዩክሬን ጦርነት እንዲቆም ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ዝግጁ አይደሉም ብለዋል።

    ትራምፕ ከፑቲን እንዲሁም ከዢ ጋር በተናጠል ውይይቶች አድርገዋል። የሩሲያውን ፕሬዝዳንት “ጓደኛዬ” ሲሉም ጠርተዋል።

    ከዢ ጋር ከተወያዩ በኋላ አሜሪካ እና ቻይና የዩክሬንን ጦርነት ማስቆም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

  2. ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ማያንማር በሮሂንጋ ማኅበረሰብ ላይ የዘር ጭፍጨፋ ፈጽማለች ሲል ብይን ሰጠ

    ማያንማር በሮሂንጋ የሙስሊም ማኅበረሰብ ላይ የዘር ጭፍጨፋ መፈጸሟን ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ብይን ሰጥቷል።

    ብይኑ የተላለፈው ከመላው ዓለም በተውጣጡ ዳኞች ነው። አንድ አገር የዘር ጭፍጨፋ በመፈጸም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሲባል የማያንማር የመጀሪያው ነው።

    ዳኛ ዩጂ አይዋሳዋ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ማያንማር የሮሂንጋ ማኅበረሰብን አብዛኛውን ክፍል “ለማጥፋት ውጥን እንደነበራት” ተናግረዋል።

    አገሪቱ “በስፋት ማስረጃ እንዳጠፋች” እንዲሁም የዘር ጭፍጨፋ የፈጸሙ ሰዎችን ሳትመረምር፣ ለፍርድ ሳታቀርብ እና ሳትቀጣ እንደቀረች ተናግረዋል።

    የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተምሳሌታዊ ዋጋ ቢኖረውም የሮሂንጋ ማኅበረሰብ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ አይሆንም።

    በአውሮፓውያኑ 2017 የሮሂንጋ መንግሥት በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ከ700,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገር ባንግላዲሽ ተሰድደዋል።

    ማያንማር በአብዛኛው ቡዲስቶች የሚኖሩባት አገር ናት። ክሱን ወደ ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት የወሰደችው ጋምቢያ ስትሆን፤ ማያንማር የቀረበባትን ውንጀላ አስተባብላለች።

    የማያንማር ኃይል በታጣቂዎች ለተፈጸመ ጥቃት ምላሽ እየሰጠ እንደነበር አገሪቷ ገልጻለች።

    ዳኛው በበኩላቸው ማያንማር በደረሰው ጉዳት ልክ ካሳ የመስጠት ኃላፊነት አለባት ብለዋል።

  3. ሶማሊያ የዩኤኢ አምባሳደር በ72 ሰዓታት አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዘች

    ሶማሊያ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አምባሳደር በ72 ሰዓታት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዘች። በአቡ ዳቢ ያሉትን አምባሳደሯንም ጠርታለች።

    ውሳኔው የተላለፈው የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን ተከትሎ ነው።

    በሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ የተመራ የካቢኔ ስብሰባ መካሄዱን ተከትሎ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አብዱልፈታህ ቃሲም ውሳኔውን ይፋ አድርገዋል።

    በሞቃዲሹ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት “ዩኤኢ በሶማሊያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን በመቀጠሏ እና የሶማሊያን ሉዓላዊነት በመጣሷ” መንግሥት አምስት የአጸፋ እርምጃዎችን የሚወስድ ይሆናል።

    የሶማሊያ ካቢኔ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት አቡ ዳቢ የሚገኙት የአገሪቱ አምባሳደር እንደሚመለሱ ተገልጿል። በሶማሊያ የዩኤኢ አምባሳደር ደግሞ በሦስት ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ታዝዘዋል።

    የሶማሊያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት እንድነት እና ብሔራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ተገልጿል።

    ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ላይ የቀረቡ ክሶችን በተመለከተ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለውጭ አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ማብራሪያ እንዲሰጥ ታዝዟል።

    ለሶማሊያ ሉዓላዊነት አደገኛ በሆኑ ድርጊቶች ከዩኤኢ ጋር የሚተባበሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል። እርምጃው ምን እንደሆነ ግን አልተጠቀሰም።

    የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በአገራቸው ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባች፣ የፌዴራል መንግሥቱን በመቃወም የክልል አስተዳደሮችን እየደገፈች እና የሶማሊያን አንድነት እና ሉዓላዊነት የሚጎዱ ፖሊሲዎችን እየተከተለች ነው ብለው መክሰሳቸው ይታወሳል።

    ፕሬዝዳንቱ ከትናንት በስትያ ባደረጉት ንግግር፤ ዩኤኢ የፌዴራል መንግሥቱን ፈቃድ ሳታገኝ ከአገሪቱ ክልሎች ባለሥልጣናት ጋር ስምምነቶችን በመፈራረም ለዓመታት የተገነባውን የዲፕሎማሲ መተማመን አፍርሳለች ብለዋል።

    የተባበሩትአረብ ኤምሬትስ የዲፕሎማሲ አማካሪ አንዋር ጋርጉሽ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ሶማሊያ የፖለቲካ ሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ እየገባች መሆኗን እና ፕሬዝዳንቱ የግል ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን በማንጸባረቅ ክስ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

    ተጨማሪ ዜናዎች፡

  4. የኤአይ ኩባንያው አንትሮፒክ አክሲዮን በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ክብረ ወሰን ያዘ

    ክላውድ የተባለውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መገልገያ ባለቤት የሆነው ኩባንያ አንትሮፒክ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአክሲዮን ገበያ ያቀረበው ድርሻ 81 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ክብረ ወሰን ሰበረ።

    ይህም አንትሮፒክ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ውድ ኩባንያዎች አንዱ አድርጎታል።

    የዚህን ኩባንያ አክሲዮን ለመግዛት የባለሀብቶች ፍላጎት በእጅጉ በመጨመሩ፣ መጀመሪያ ከታቀደው በላይ አክሲዮኖች ተሽጠዋል። የአክሲዮኑ ዋጋም ከተገመተው ከ70 እስከ 78 ዶላር የሚደርስ ዋጋ ከፍ ብሎ 83 ዶላር ደርሷል።

    አክሲዮኖቹ ሐሙስ በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ ላይ ግብይት የሚሸጡ ሲሆን፣ ይህም ዕድሜው አምስት ዓመት ብቻ የሆነውን ኩባንያ በ1.5 ትሪሊዮን ዶላር ያህል ዋጋ እንዲገመት ያደርገዋል።

    ይህ የአክሲዮን ሽያጭ በፍጥነት እያደገ ላለው የኤአይ ዘርፍ ወሳኝ የመፈተሻ አማራጭ ይሆናል ተብሎ ተወስዷል።

    አንትሮፒክ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ብቻ የተመሠረተ ኩባንያ ሆኖ አክሲዮኑን ለሕዝብ የሸጠ የመጀመሪያው ድርጅት ነው።

    በኤኤይ መሠረተ ልማቶች እና የኤኤይ መሣሪያዎች ልማት ውስጥ እጅግ ብዙ ገንዘብ በዓለም ዙሪያ ውጪ ተደርጓል። ሆኖም እነዚህ መዋዕለ ንዋዮች መቼ እና እንዴት ትርፍ ማስገኘት እንደሚጀምሩ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።

    ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ለመሳብ በቻለው ከፍተኛ የአክሲዮን ሽያጭ ምክንያት አንትሮፒክን በአውሮፓውያኑ 2021 ያቋቋሙት ሰባቱ መሥራቾች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ያላቸው ሰዎች ለመሆን ችለዋል።

  5. በሴኔጋል 100 ስደተኞችን ይዞ የነበረ ጀልባ ወቅያኖስ ላይ መገልበጡ ተዘገበ

    በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል የባሕር ዳርቻ አካባቢ 100 የሚጠጉ ስደተኞችን አሳፍሮ ነበር የተባለ ጀልባ መገልበጡን ተከትሎ፣ ባለሥልጣናት ነፍስ የማዳን እና የፍለጋ ሥራ እያከናወኑ መሆኑ ተዘገበ።

    የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች በአደጋው አንድ ሰው መሞቱን ቢገልጹም፣ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ቢያንስ አራት አስከሬኖች መገኘታቸውን እና በርካቶች አሁንም የደረሱበት አለመታወቁን ገልጸዋል።

    በሰሜን ምዕራብ ሴኔጋል በምትገኘው ቲዬፕ ከተማ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ሲያጋጥም ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

    ከዚህ ቀደም በደረሰው አደጋ ቢያንስ 39 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ በሴኔጋል ስደተኞች ላይ ከደረሱ አሰቃቂ አደጋዎች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።

    የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ኦማር ሶው፣ የአሁኑ አደጋ ከሌሊቱ 8:00 ሰዓት አካባቢ መከሰቱን እና ከየባሕር ዳርቻው ላይ የእርዳታ ጩኸት ይሰማ እንደነበር ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    አደጋው በደረሰበት ጀልባ ላይ 100 የሚጠጉ ሰዎች እንደነበሩ ከመካከላቸውም አምስት ሴቶች እንደሆኑ ለፖሊስ ቃሉን የሰጠ አንድ ከአደጋው የተረፈ ተሳፋሪ ተናግሯል።

    ፖሊስ አደጋው የደረሰበት ጀልባ ላይ የማንነት ሰነዶችን፣ በርካታ ሞባይል ስልኮችን እና ሌሎች የግል ንብረቶችን አግኝቷል። ከእነዚህ መካከል የአንድ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሊሆን ይችላል ተብሎ የተገመተ የትምህርት ቁሳቁስም ተገኝቷል።

    የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዲዮማዬ ፋዬ ረቡዕ በተካሄደ የካቢኔ ስብሰባ ላይ ወደ አውሮፓ ለመድረስ በሕገ-ወጥ መንገድ በባሕር ለመጓዝ የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር እንደገና መጨመሩ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

    ባለፈው ወር በተከሰተው እና ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች ከሞቱበት አደጋ በኋላም ፕሬዝዳንቱ ሴኔጋላውያን ለአደገኛ የባሕር ጉዞዎች ሕይወታቸውን እንዳያጋልጡ አሳስበው ነበር።

    የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) በጥቅምት ወር እንደገለጸው፣ እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ በምዕራብ አፍሪካ የአትላንቲክ ውቅያኖስ የስደት መስመር ላይ ቢያንስ 454 ሰዎች ሞተዋል ወይም ደብዛቸው ጠፍቷል።

    ጀልባዎች እማኝ የሚሆን የተረፈ ሰው ወይም ምልክት ሳይተዉ የሚጠፉባቸው አደጋዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ይህ የባሕር ላይ አደጋ ሰለባዎች ቁጥር ከእውነታው ያነሰ ሊሆን እንደሚችል ድርጅቱ አሳስቧል።

  6. የአውሮፓ ኅብረት የ12 የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶች በግዛቱ እንዳይበሩ አገደ

    የአውሮፓ ኅብረት ከአቪዬሽን ደኅንነት ጋር በተያያዘ የ12 የአፍሪካ አገራት ንብረት የሆኑ በርካታ አየር መንገዶች በአህጉሪቱ ውስጥ እንዳይበሩ ከለከለ።

    አየር መንገዳቸው ላይ ክልከላ ከተጣለባቸው አገራት መካከል ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲ እና ታንዛኒያ ይገኙበታል።

    በዚህ ውሳኔ መሠረት የሊቢያ፣ የአንጎላ፣ የኮንጎ-ብራዛቪል፣ የዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ የኦኳቶሪያል ጊኒ፣ የላይቤሪያ፣ የሳኦ ቶሚ እና ፕሪንሲፒ እንዲሁም የሴራሊዮን አየር መንገዶች በሙሉ ወደ አውሮፓ ከመብረር ታግደዋል።

    ይህንን ተከትሎም፣ በአገራቱ ውስጥ የሚገኙ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አየር መንገዶች በሙሉ ከበረራ ታግደዋል። ከእነዚህም መካከል ታንዛኒ 34፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ 13፣ ሱዳን 12፣ ሊቢያ 10 አየር መንገዶች ታግደውባቸዋል።

    ዕገዳው በአንዳንድ አገራት ላይ ሙሉ ለሙሉ የሚጣል ሲሆን በሌሎች ላይ ደግሞ በተወሰኑ አየር መንገዶች ላይ ብቻ ተግባራዊ የሚሆን ነው። ሙሉ ዕገዳ ከተጣለባቸው 12 አገራት በተጨማሪ በስም የተጠቀሱ የአልጄሪያ እና የዚምባብዌ አየር መንገዶች በተናጠል ታግደዋል።

    በአውሮፓ ኅብረት የአየር ትራንስፖርት ደኅንነት ግምገማ መሠረት በ12 የአፍሪካ አገራት ላይ ሙሉ ለሙሉ እና በተወሰኑ አገራት በተናጠል በአየር መንገዶች ላይ በተጣለው እገዳ ምክንያት 89 የሚደርሱ የአፍሪካ አገራት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ታግደዋል።

    ይህ ዓይነቱ አውሮፓ የአየር መንገዶች ምዘና እና ፈቃድ አሠራር የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2006 ነው። በዚህ አሠራር ከታገዱ በኋላ መመዘኛውን የሚያሟሉ አየር መንገዶች የመብረር ፈቃድ ሊያገኙ ይችላሉ።

  7. እስልምና በ2035 ክርስትናን በመብለጥ በዓለም ትልቁ ሃይማኖት እንደሚሆን ተተነበየ

    እስልምና ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2035 ክርስትናን በመብለጥ በዓለም ትልቁ ሃይማኖት ይሆናል ተብሎ እብደሚጠበቅ የፒው የምርምር ማዕከል ትንበያ አመለከተ።

    ላለፉት 25 ዓመታት በሃይማኖታዊ የሕዝብ አሰፋፈር ላይ ተዓማኒነት ያላቸው ሪፖርቶችን ሲያወጣ የቆየው ፒው፣ እስልምናም ሆነ ክርስትና እያደጉ ቢሆንም፣ እስልምና ግን እጅግ በፈጠነ ሁኔታ እያደገ መሆኑን ገልጿል።

    ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ሙስሊሞች ከሌሎች ዋና ዋና ሃይማኖቶች ይልቅ ብዙ ልጆችን የመውለድ ዝንባሌ ስላላቸው እንደሆነ ማዕከሉ ትናንት ኀዳር 9 ቀን 2019 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ዝርዝር ትንበያ አስረድቷል።

    የፒው ከፍተኛ የሥነ-ህዝብ ተመራማሪ ኮራንድ ኮንራድ ሃኬት፣ ሃይማኖትን መቀየር እና ሌሎች የሃይማኖት ለውጦች ከወሊድ መጠን አንጻር ያላቸው ድርሻ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ስለማብራራታቸው ኤፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    እንደፒው መረጃ ከሆነ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2020 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ የሙስሊሞች የወሊድ መጠን በአንዲት ሴት 3.1 ልጆች ነበር። ክርስቲያኖች ሴቶች ደግሞ በ2.5 ልጆች ይከተላሉ።

    የሌሎች ሃይማኖቶች አማካይ የወሊድ መጠን 1.6 ሲሆን፣ ይህም እያንዳንዱ ትውልድ ራሱን ለመተካት አስፈላጊ ነው ተብሎ ከሚታሰበው 2.1 ምጣኔ ያነሰ ነው።

    ከዚህ ቀደም በነበረው የፒው ግምት እንደሚያሳየው፣ በ2020 በዓለም ዙሪያ 2.27 ቢሊዮን ክርስቲያኖች እና 2.02 ቢሊዮን ሙስሊሞች ነበሩ።

    በአዲሱ የፒው ትንበያ መሠረት ደግሞ፣ በ2035 በዓለም ላይ 2.57 ቢሊዮን ሙስሊሞች እና 2.52 ቢሊዮን ክርስቲያኖች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    አሁን ያለው አዝማሚያ ከቀጠለ፣ በ2070 ደግሞ በዓለም ዙሪያ ከ3.6 ቢሊዮን በላይ ሙስሊሞች እና ከ3 ቢሊዮን በታች ክርስቲያኖች ይኖራሉ።

    በ2020 እና በ2070 መካከል የዓለም ሕዝብ ቁጥር በ29 በመቶ እንደሚጨምር ፒው አስታውቋል።

    ማዕከሉ ከተነተናቸው የሃይማኖት ቡድኖች መካከል ከዚህ ዕድገት ጋር እኩል ይጓዛሉ ተብሎ የሚጠበቁት ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። ክርስቲያኖች በ30 በመቶ፣ ሙስሊሞች ደግሞ በ80 በመቶ ያድጋሉ።

    ሂንዱዎች እና አይሁዶች በጠቅላላ ቁጥራቸው እያደጉ ቢሆንም፣ ከዓለም ሕዝብ ቁጥር አንጻር ያላቸው ድርሻ ግን እንደሚቀንስ ፒው ገልጿል።

    የቡድሂስቶች ቁጥርም ሆነ ከዓለም ሕዝብ ያላቸው ድርሻ እንደሚቀንስ ተገምቷል። ይህ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ በቻይና፣ በደቡብ ኮሪያ እና በጃፓን አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር እንደሚቀንስ የሚጠበቅ መሆኑ ነው።

    በመጪዎቹ አሥርት ዓመታት ውስጥ፣ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ቁጥር ዕድገት የሚከሰተው በአፍሪካ፣ በተለይም አብዛኛው ሕዝብ ክርስቲያን ወይም ሙስሊም በሆነበት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት እንደሆነ ፒው ገልጿል።

    ከፍተኛ “ሃይማኖት የሌላቸው” ሰዎች ድርሻ ያላትን ነገር ግን አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሯ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ያለችውን ቻይናን ሳይጨምር፣ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር በ2070 ከ180 ሚሊዮን በላይ እንደሚያድግም ፒው አስታውቋል።

  8. ትራምፕ ኢራን ባዮሎጂካል የጦር መሣሪያዎችን እየሠራች መሆኑን የሚያመለክት “ፍንጭ መኖሩን” ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ የኢራንን የኒውክሌር አቅም ስላወደመች ቴህራን ባዮሎጂካል ወይም ኬሚካል የጦር መሣሪያዎችን እየሠራች እንደሆነ የሚያመለክት ፍንጭ መኖሩን ተናገሩ።

    በእስያ ፓስፊክ መሪዎች ጉባኤ ላይ ለመታደም ቻይና የሚገኙት ትራምፕ ይህንን ያሉት በዚያው ከፎክስ ኒውስ ጋር ትናንት ረቡዕ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ነው።

    ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤንኤን፣ ኢራን የትራም አስተዳደር ባለሥልጣናትን ዒላማ ያደረገው የኬሚካል መሣሪያ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችላትን ዕቅድ እያዘጋጀ መሆኑን የአሜሪካ የስለላ መረጃ ማሳየቱ ዘግቦ ነበር።

    በረቡዕ ዕለቱ ቃለ ምልልስ ላይ የተጠየቁት ትራምፕ፣ ሕዝቡ ስለዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ስጋት ሊፈጠርበት እንደማይገባ በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል።

    “ኒውክሌር እጅግ ጠንካራ ነው፤ እናም ጋዝ እና ባዮ [መሣሪያዎችን] እየተመለከቱ ነው። ታውቃለህ ባዮሎጂካል የጦር መሣሪያዎችን እና ሌሎች ነገሮችን እየተመለከቱ ነው፤ ጥሩ አይደለም” ብለዋል።

    “አዲስ ዓመት እየመጣ ነው፤ [ከአውሮፓውያኑ] ጥር 1 በኋላ ምን እንደሚፈጠር እናያለን” ሲሉም ተደምጠዋል። ትራምፕ አክለውም፣ “ይህ ከተፈጸመ እናጠፋቸዋለን” በማለት አስጠንቅቀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ ከኢራን ጋር መነጋገሯን እንደቀጠለች በቃለ መጠይቃቸው አንስተዋል። ቴህራን ስምምነት ማድረግ እንደምትፈልግ በድጋሚ የተናገሩ ሲሆን፣ እርሳቸው ግን ዘላቂ የሆነ ስምምነት እንደሚፈልጉ አመልክተዋል።

    በተጨማሪም ባለፈው ሰኔ ከኢራን ጋር የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት አንስተው “የጊዜ ብክነት ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል።

  9. ከ190 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመሸጥ ክብረ ወሰን የሰበረው ሥዕል

    በታዋቂው የደች ሠዓሊ ቪንሰንት ቫን ጎ የተሳለው ሥዕል በ190.4 ሚሊዮን ዶላር በመሸጥ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገበ።

    ሶዝቢስ በተባለው አጫራች ለሽያጭ የቀረበው ሥዕል በአውሮፓውያኑ 2022 በ117.2 ሚሊዮን ዶላር የተሸጠውን የቫን ጎ ቀደምት ሥዕልን የጨረታ ክብረ ወሰን ተሻግሮ ሄዷል።

    ናዚዎች የስዕሉ ባለቤቶቹ በግዴታ እንዲሸጡት አድርገዋል የሚል ውዝግብ ተነስቶ ነበር። ሥዕሉ በኒው ዮርክ ረቡዕ ዕለት የተሸጠው ከስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነው።

    ሥዕሉ በአውሮፓውያኑ 1890 ቫን ጎግ ከሞቱ በፊት ባሉት የመጨረሻ ሁለት ወራት ውስጥ ከሠራቸው ሥራዎች አንዱ ነው።

    ሶዝቢስ እንደሚለው፣ ሥዕሉ የዚያ ዘመን የሆኑ እና አሁንም በግል ባለቤትነት የሚገኙ እጅግ አስፈላጊ የሥነ ጥበብ ሥራዎች መካከል አንዱ ነው።

    ሥዕሉን በዚህ ከፍተኛ መጠን በተባለው ገንዘብ ማን እንደገዛው ግን ወዲያውኑ አልታወቀም።

  10. የዩክሬንን የሚደግፈውን የአሜሪካ መከላከያ ኩባንያ በመሰለል የተጠረጠረ ሩሲያዊ በቁጥጥር ሥር ዋለ

    ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ በሚሰጥ አንድ የቴክኖሎጂ እና የመከላከያ ኩባንያ ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞችን ለመሰለል በመሞከር የተጠረጠረ ሩሲያዊ በካሊፎርኒያ ሲልከን ቫሊ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ።

    ኢጎር ዲዩ የተባለው ግለሰብ በሳን ፍራንሲስኮ አቅራቢያ በምትገኘው ፓሎ አልቶ ከተማ ድብቅ የስለላ ዘመቻ ለማካሄድ የውጭ መንግስት ወኪል ሆኖ በመስራት ተከሷል። በስለላው ዒላማ ተደርጎ የነበረው ኩባንያ ‘ፓላንቲር ቴክኖሎጂስ’ እንደሆነ ቢቢሲ ተገንዝቧል።

    ዲዩ በተጨማሪም ሠራተኞችን በመከታተል እና የሐሰት የመታወቂያ ሰነዶችን በመያዝ ክስ ቀርቦበታል።

    በክስ ሰነዱ ላይ የኩባንያው ስም አልተጠቀሰም። ይሁን እንጂ፣ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት የምትጠቀምበትን ሶፍትዌር የሚያመርት እንዲሁም በአክሲዮን ገበያ ላይ የሚገበያይ የቴክኖሎጂ እና መከላከያ ኩባንያ ተብሎ ተገልጿል።

    የሰሜን ካሊፎርኒያ ዲስትሪክት የአሜሪካ አቃቤ ህግ ክሬግ ሚሳኪያን “የቀረቡት ክሶች ኩባንያው ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታካሂደው ጦርነት እገዛ በማድረጉ ምክንያት የአሜሪካ የቴክኖሎጂ እና መከላከያ ኩባንያ ሠራተኞችን ዒላማ ለማድረግ እና ለማዋከብ በመንግሥት የተደገፈ ዘመቻ መኖሩን ያሳያሉ” ብለዋል።

    አሰሪዎቹ ሩሲያን “’እናት አገር’ እያሉ ይጠሯት የነበረ ሲሆን፣ ኩባንያው በዩክሬን በሩሲያ ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ የጦር መሳሪያዎችን ያቀርብ ስለነበር ስለ ኩባንያው መረጃ እንዲሰበስብ መመሪያ ሰጥተውት ነበር” ተብሏል።

    በዘርፉ ያሉ አንድ ምንጭ ዒላማ የተደረገው ፓላንቲር መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ዘመቻው ግን የኩባንያውን የግል ሲስተሞች ሰብሮ መግባት አለመቻሉን ገልጸዋል።

    ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት እኚህ ምንጭ፣ አንድ የሩሲያ ሰላይ በአሜሪካ ምድር ተገኝቶ ኩባንያውን ለመሰለል ሲሞክር ሲያዝ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን ተናግረዋል።

    ፓላንቲር በቀረቡት ክሶች ዙሪያ እስካሁን ምንም አይነት መግለጫ አልሰጠም።

    ተያያዥ ዘገባ፦

  11. ትራምፕ፣ ዢ እና ፑቲን ዛሬ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ላይ በአካል ስብሰባ ሊያደርጉ ነው

    የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ፣ የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን፣ የቻይናው ዢ ጂንፒንግ ዛሬ ሐሙስ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ላይ በአካል የሦስትዮሽ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የሩሲያ አቻቸው ፑቲን በእስያ ፓስፊክ መሪዎች ጉባኤ (ኤፔክ) ለመሳተፍ በደቡባዊ ቻይና ሼንዘን ከተማ ይገኛሉ። አስተናጋጃቸውም የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ናቸው።

    የእስያ ፓስፊክ መሪዎች ጉባኤ በመካሄድ ላይ ሲሆን የዚህ ጉባኤ ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር የሆነው የሦስቱ መሪዎች ስብሰባ በሰዓታት ውስጥ እንደሚጀመር ይጠበቃል። የአሜሪካ፣ የሩሲያ እና የቻይና ፕሬዝዳንቶች በአካል ተገናኝተው ውይይት ሲያደርጉ ይህ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ረቡዕ ሼንዘን አየር ማረፊያ ሲደርሱ ፕሬዝዳንት ዢ በፈገግታ ተቀብለዋቸዋል። የቻይና መሪ እንግዶችን በአየር ማረፊያ ተገኝተው ሲቀበሉ ማየት እጅጉን ያልተለመደ ነገር ነው።

    አንድ የውጭ አገር መሪ እንዲህ ዓይነት አቀባበል ሲደረግለትም ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ይታመናል። ቀጥሎም ትራምፕ ከፑቲን ጋር ሰላምታ የተለዋወጡ ሲሆን ሦስቱ መሪዎች ሲጨባበጡ የሚያሳዩ ፎቶዎች ወጥተዋል።

    መሪዎቹ የሚያደርጉት የሦስትዮሽ ስብሰባው በምን ጉዳይ ላይ እንደሚተኩር እስካሁን በትክክል አልታወቀም።

    ስብሰባው የሚካሄደው ‘ካይሊን ቪላ’ ተብሎ በሚጠራው ታዋቂ ስፍራ እንደሚሆን ተገምቷል። በአውሮፓውያኑ 1997 የተከፈተው እና በመንግሥት የሚተዳደረው ይህ ግቢ የቻይና እና የውጭ አገራት መሪዎችን የማስተናገድ ረጅም ታሪክ አለው።

    ቻይና ከመደበኛ የስብሰባ አዳራሽ ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን ስፍራ መምረጧ ውይይቱ “ራሱ የቻለ ትልቅ ስብሰባ ሳይሆን ከጉባኤው ጎን ለጎን የሚደረግ ውይይት” መሆኑን እንደሚጠቁም በዴፖል ዩኒቨርሲቲ የመሪዎች ጉባኤ ዲፕሎማሲ ባለሙያ የሆኑት ሚንሴዮን ኩ ተናግረዋል።

    የቻይናው ፕሬዝዳንት “ዢ ይህንን ይፈልጋሉ፤ ምክንያቱም ቻይና የኤፔክ አስተናጋጅ በመሆኗ የእስያ ፓስፊክ መሪዎች ጉባኤ ዋናው ኹነት እንዲሆን እንጂ በሦስትዮሽ ስብሰባው እንዲጋረድ አትፈልግም” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ከሦስቱ ልዕለ ኃያላን አገራት ባሻገር፣ ከመላው ዓለም የተውጣጡ መሪዎችም በኤፔክ ጉባኤ ላይ ተገኝተዋል፤ ተከታታይ ስብሰባዎችንም እያደረጉ ነው።

    የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ አገራቸው አሜሪካ ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ ከእስያ አገራት ጋር የንግድ ስምምነቶችን እየተፈራረሙ ነው።

    የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካኢቺ ደግሞ አገራቸው ከቤጂንግ ጋር ግንኙነቷ ከተቀዛቀዘ ወዲህ በቻይና የመጀመሪያውን ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ነው።

    ተያያዥ ዘገባዎች፦

  12. የኅዳር 10 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የሐሙስ ኅዳር 10 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።

  13. አሜሪካ የኢራንን ደሴት መደብደቧን ተከትሎ ኩዌት ከሁለት ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት ተሰነዘረባት

    የኢራን እና አሜሪካ ፍጥጫ መካረሩን ተከትሎ፣ ኩዌት እና ባህሬን ማክሰኞ ሌሊት ከቴህራን የተሰነዘሩባቸውን የአየር ጥቃቶችን መመከታቸውን አስታወቁ።

    ኩዌት በኢራን የድሮን ጥቃት የደረሰባት ከሁለት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    ሁለቱ አገራት ጥቃት የተፈጸመባቸው፣ የአሜሪካ የጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ በሚገኘው የቀሽም ደሴት ላይ ያከን የኢራን ሚሳዔል ማስወንጨፊያ ከደበደበ በኋላ እንደሆነ የአሜሪካ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    የኢራን ጦር በበኩሉ የአሜሪካ ኃይሎች የሚገኙበትን አሊ አል ሳሌም የአየር ኃይል ጦር ሠፈር ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል። የኩዌት ባለሥልጣናት ግን ጉዳት ስለመድረሱ አልገለጹም።

    የኩዌት ጦር ማክሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ የተሰነዘሩትን “የድሮን ስጋቶችን” መመከቱን እና በሰዎች ላይም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።

    የኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ጥቃቱን አውግዟል። ጥቃቱ “የኩዌትን ሉዓላዊነት በግልጽ የጣሰ፣ ደኅንነቷን እና መረጋጋቷን በቀጥታ አደጋ ላይ የጣለ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግን በከፍተኛ ሁኔታ የጣሰ ነው” ብሏል።

    የባህሬን ጦር ደግሞ ረቡዕ ዕለት የአገሪቱ አየር መከላከያ ስርዓቶች “በርካታ የኢራን የአየር ጥቃቶችን በአየር ላይ እንደጠለፉ እና እንዳወደሙ” አስታውቋል።

    የአሜሪካ ባሕር ኃይል 5ኛ ፍሊት የሚገኝባት ባህሬን፣ ከሁለት ወራት ፋታ በኋላ ባለፉት ስድስት ቀናት ውስጥ አራት ጥቃቶች እንደተፈጸሙባት ገልጻለች።

    በሌላ በኩል፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥት ንብረት የሆነው የነዳጅ ኩባንያ ማክሰኞ ዕለት በባሕረ ሰላጤው ሲጓዝ በነበረ አንድ የነዳጅ ጫኝ መርከቡ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመበት አስታውቋል። በዚህ ጥቃት አንድ የመርከብ ሠራተኛ የደረሰበት አለመታወቁን ጠቅሷል።

    ኢራን እና አሜሪካ የጥቃት ልውውጥ ውስጥ መግባታቸው እንዲሁም በሚያደገጉት ድርድር ላይ ለውጥ አለመታየቱ፣ ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት ወደ ከፋ ደረጃ ሊያድግ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

    ጦርነቱ የተጀመረው አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው የካቲት መጨረሻ ላይ ኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው።

    በሁለቱ አገራት የተደበደበችው ኢራን፣ እስራኤል ላይ እንዲሁም የአሜሪካ ወታደራዊ ንብረቶችን እና ሠራተኞችን በሚያስተናግዱ የባሕረ ሰላጤው አረብ ሀገራት ላይ የሚሳዔል እና ድሮን ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።

  14. የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የሳይበር ደኅንነት ክስተት” እንዳጋጠመው አስታወቀ

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የሳይበር ደኅንነት ክስተት” እንዳጋጠመው እና የመረጃ ጥሰቱን የተፅዕኖ መጠን ለማወቅ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ለደንበኞቹ አሳወቀ።

    ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ በክስተቱ የደንበኞች የፋይናንስ መረጃ ለሌላ አካል ስለመድረሱ የሚያመለክት ማስረጃ እንዳልተገኘ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 9/2019 ዓ.ም. ለ‘ሼባ ማይልስ’ ተጠቃሚዎች በላከው የኢሜይል መልዕክት ገልጿል።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታማኝ ደንበኞች አገልግሎት የሚያገኙበት ‘ሼባ ማይልስ’ ከ5.4 ሚሊዮን ገደማ ደንበኞች እንዳሉት ባለፈው ዓመት የወጣ መረጃ ያመለክታል።

    “የመረጃ ጥሰት የሕዝብ ማስታወቂያ” በሚል ርዕስ የተላከው ኢሜይል ክስተቱ ያጋጠመው የሼባ ማይልስ ሥርዓት ላይ ብቻ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።

    ለሼባ ማይልስ ደንበኞች የተላከው መልዕክት፣ በአየር መንገዱ “በሲስተሞቻች ላይ ውስን አድማስ” ያለው “የሳይበር ደኅንነት ክስተት” ማጋጠሙን አስረድቷል። “ክስተቱ የተወሰኑ ደንበኞችን መረጃዎች ነክቶ ሊሆን ይችላል” ብሏል።

    የአየር መንገዱ መልዕክት፣ ክስተቱ ያጋጠመው “በቅርቡ” እንደሆነ ቢገልጽም ትክክለኛውን ቀን አላስቀመጠም።

    በዚህ ጥሰት ምን ያህል ደንበኞች እንደተነኩ፣ ምን ዓይነት መረጃ ጥሰት እንደደረሰበት ወይም ክስተቱ እንዴት እንደተደረሰበት በግልፅ አላሳወቀም።

    ቢቢሲ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።

    ጉዳዩ “በከፍተኛ ትኩረት እና ጥንቃቄ” መያዙን የገለጸው አየር መንገዱ፣ “ክስተቱን ለመመርመር እና ሙሉ ተፅዕኖውን ለመገምገም ከሳይበር ደኅንነት አጋሮቻችን እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየሰራን ነው” ብሏል።

    አየር መንገዱ ጉዳዩን ለመፍታት “ሙሉ ትኩረት እና ሀብቱን” ማዋሉንም አክሏል። “ተጨማሪ መረጃዎች ሲገኙ” ለደንበኞቹ እንደሚያሳውቁም ቃል ገብቷል።

    ደንበኞች ራሳቸውን ከሚደርሳቸው “ከማንኛውንም አጠራጣሪ ወይም አስፈላጊ ያልሆነ ግንኙት” እንዲጠብቁ አየር መንገዱ አሳስቧል።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህ ዓይነት የበይነ መረብ (ሳይበር) ደኅንነት ክስተት እንዳጋጠመው ያስታወቀው፣ በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ከፍተኛ የአገልግሎ መስተጓጎሎች ባጋጠሙበት ወቅት ነው። ባለፈው ሳምንት ግዙፉ ማይክሮሶፍት ባጋጠመው መስተጓጎል አገልግሎቶቹ ተቋርጠው ነበር።

    በአሜሪካ ደግሞ በአገሪቱ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ ባጋጠመ ክስተት ምክንያት በ25 ዓመት ውስጥ ረጅም ለተባለ ጊዜ በረራዎች ተቋርጠዋል።

    የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅነንት ተቋም በበኩሉ ማክሰኞ ዕለት የመሥሪያ ቤቱ የውስጥ ግንኙነት ሥርዓት ተቋርጦ እንደነበር አሳውቋል። የአገሪቱ ባንኮችም ተመሳሳይ መስተጓጎል አስተናግደዋል።

    ከዚህ አስቀድሞ ደግሞ በፈረንሳይ ሱፐርማርኬቶች ማቀዝቀዣ ፍሪጅ መቆጣጠሪ ሥርዓት ላይ በተፈጸመ የሳይበር ጥቃት ምክንያት ምግቦች ተበላሽተዋል። ቀጥሎም በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ተመሳሳይ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል።

    ፈረንሳይ፣ የሱፐርማርኬቶች ማቀዝቀዣ የሙቀት መጠናቸው እንዲጨምር ላደረገው የሳይበር ጥቃት ተጠያቂ ያደረገችው ኢራንን ነው። ኢራን ግን ክሱን ውድቅ አድርጋለች።

  15. ትራምፕ፣ ፑቲን እና ዢ ጂንፒንግ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ላይ በአካል ተገናኝተው ተጨባበጡ

    በቻይና ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ለሚያደጉት ታሪካዊ ውይይት እየተዘጋጁ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን ከአንድ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገናኙ።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በእስያ ፓስፊክ መሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሼንዘን ከተማ ደርሰው ከአውሮፕላን ሲወርዱ በቻይናው መሪ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ጉባኤው የሚጠናቀቀው ዓለም በትኩረት እየተጠባበቀው ያለው የሁለቱ መሪዎች እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ስብሰባ ከተደረገ በኋላ ነው።

    ትራምፕ ከአውሮፕላን ከወረዱ በኋላ ከቻይና ፕሬዝዳንት ጋር በጥንቃቄ በተቀናጀ አኳኋን ሲጨባበጡ እና ሲተቃቀፉ ታይተዋል። ቀጥሎ ደግሞ የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ከመጀመቱ በፊት ለፑቲን ሰላምታ ሰሲጡ እና አጭር ቃላትን ሲለዋወጡ ተስተውሏል።

    ትራምፕ እና ፑቲን ነገ ሐሙስ ከጉባኤው ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። የዩክሬን ግጭት ከንግግር አጀንዳዎቻቸው አንዱ ሊሆን ይችላል።

    ይሁን እንጂ የእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር መድረክ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የሆነው ሐሙስ ዕለት የሚካሄደው የአሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ የሦስትዮሽ ውይይት ነው።

    ሦስቱ መሪዎች አንድ ላይ በአካል ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

    የስብሰባው ሙሉ አጀንዳ ይፋ ባይደረግም፣ ስለ ዩክሬን እና ኢራን ግጭቶችን፣ ስለ ኒውክሌር መሣሪያዎች መስፋፋትን፣ ስለ ንግድ ውጥረቶችን እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ዘርፍ ስለተመዘገቡ እድገቶች ሊወያዩ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተዋል።

    ትራምፕ እና ፑቲን ለብቻቸው የሚያደርጉ ውይይት ምን ዓይነት ቅርጽ እንደሚኖረው እስካሁን ግልጽ አይደለም። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ግን ብዙ ልዑካን የማይገኙበት፣ አጭር እና መደበኛ ያልሆነ ንግግር እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

    የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የኪየቭ ወይም የአውሮፓ ተወካዮች ባልተገኙበት ጦርነቱን ለማስቆም ስለሚዘጋጅ ዕቅድ ሊወያዩ ይችላሉ የሚል ስጋት አንስተዋል።

    ትራምፕ እና ፑቲን ከነሐሴ 2017 ዓ.ም. በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገናኝተው የተጨባበጡት ዛሬ ረቡዕ ነው። በወቅቱ የሩሲያው መሪ ስለ ዩክሬን ጦርነት ለመነጋገር ወደ አላስካ ተጉዘው የነበረ ቢሆንም ውይይቱ ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።

  16. የናይጄሪያ 36 ግዛቶች የየራሳቸውን ፖሊስ እንዲያደራጁ እና እንዲያሰማሩ ሊፈቀድ ነው

    ከናይጄሪያ የፌደራል ኃይሎች ጎን ለጎን ግዛቶች የየራሳቸውን ፖሊስ እንዲያደራጁ እና እንዲያሰማሩ ሊፈቀድ ነው።

    የአገሪቱ 36 ግዛቶች ለቀረበው ረቂቅ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል።

    ረቂቁ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚያስፈልገው ሲሆን፤ ሕግ ሆኖ እንዲተገበር ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ፊርማቸውን ማኖርም ይጠበቅባቸዋል።

    ግዛቶች ፖሊስ እንዲያሰማሩ በፌደራል እና በግዛቶች ደረጃ ሕጉ መተግበር እንዳለበት ተገልጿል።

    ረቂቁ የቀረበው ናይጄሪያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሰላም ማጣት እየተፈተነች ባለችበት ወቅት ነው።

    የፌደራል ኃይሉ የጅምላ እገታ፣ በማኅበረሰቦች መካከል የሚፈጠር ግጭት እና ዝርፊያን ለመቆጣጠር እየሞከረ ይገኛል።

    የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የፖሊስ ኃይል እጥረት ክፍተት ፈጥሯል። ፖሊሶች በአግባቡ ሥልጠና እንደማይሰጣቸው እና በቂ መሣሪያ እንደሌላቸውም ተመልክቷል።

    አሁን ላይ ተግባራዊ እየሆነ ያለው አሠራር በ1999 በወጣው ሕገ መንግሥት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ፖሊሶች የሚሰማሩት በማዕከላዊ መንግሥቱ ሥር ነው።

    ግዛቶች የየራሳቸውን ፖሊስ አደራጅተው እንዲያሰማሩ መፍቀድ አለመረጋጋት ሲከሰት በፍጥነት ምላሽ እንዲሰጡ እንደሚረዳ ይታመናል። ፖሊሶቹ ማኅበረሰባቸውን በተሻለ ሁኔታ እንደሚገነዘቡ በማንሳትም ሐሳቡን የሚደግፉ አሉ።

  17. ጋና የገዛችው የ60 ሚሊዮን ዶላር ፕሬዚደንታዊ ጄት ቁጣ ቀሰቀሰ

    የጋና መንግሥት አዲስ የገዛው የ60 ሚሊዮን ዶላር ፕሬዚደንታዊ ጄት ሕዝባዊ ቁጣ ቀሰቀሰ።

    መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበትን ፕሬዚደንታዊ ጄት የገዛው በርካታ ዜጎች በኑሮ ውድነት እየተፈተኑ ባለበት ወቅት ነው።

    60 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት ፈረንሳይ ሰራሹ 'ፋልኮን 6ኤክስ' ፖለቲካዊ ውዝግቦችን ያስከተለ ሲሆን ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም "ቅድሚያ ለሚሰጠው ነገር ቅድሚያ ባለመስጠት" የፕሬዚደንት ጆን ማሃማን አስተዳደር ከስሰዋል።

    ሆኖም መንግሥት እያደገ የመጣው የአገሪቷ ኢኮኖሚ እየተሻሻለ በመምጣቱ የጄቱ ዋጋ ተመጣጠኝ መሆኑን እና እያረጀ የመጣውን የፕሬዚደንቱን ጄት ለመተካት በማስፈለጉ ግዥው በምክንያት የተፈፀመ መሆኑን አስረድቷል።

    ውዝግቡ የተከሰተው የማሃማ አስተዳደር ጋና ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም እርዳታ እንድትጠይቅ ያስገደዳትን እና ለዓመታት ያጋጠማትን የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲያገግም ለማድረግ እየጣረ ባለበት ወቅት ነው።

    የጋና አየር ኃይል፣ የፈረንሳይ ኤርስፔስ ኩባንያ በሆነው ዳሶልት አቪየሽን የተመረተውን እና 60 ሚሊዮን ዶላር የወጣበትን አውሮፕላን ሰኞ ዕለት ተረክቧል።

    ፕሬዚደንታዊ አውሮፕላኑ የተገዛው ባለፈው ታኅሳስ ወር ምክር ቤቱ የአገሪቷን የጦር አውሮፕላኖች የማዘመን ሰፊ ፕሮግራም አካል አድርጎ ግዥውን ካፀደቀው በኋላ ነው። ይህም ከኤርባስ የተገዙ አራት ሄሊኮፕተሮችን ያካትታል።

    ጋና ጄቱን ሰኞ እለት የተረከበች ቢሆንም የተገዛበት ወቅት እና ዋጋን በተመለከተ በኦንላይን እና በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ዘንድ ትችትን አስከትሏል።

    አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ለአውሮፕላኑ የወጣው ገንዘብ በሌሎች ለሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ነገሮች ላይ መዋል ነበረበት ብለዋል።

    አንድ የኤክስ ተጠቃሚ “ገንዘቡ ከ100 ሺህ በላይ ነርሶችን እና 200 ሺህ መምህራንን መቅጠር ይችላል” ብሏል።

    መንግሥት በበኩሉ የጋና የኢኮኖሚ ሁኔታ ጥሩ መሻሻል አሳይቷል ሲል ትችቱን ውድቅ አድርጓል።

    • ተያያዥ ዜና፡
  18. በሱዳን ጦርነት በዚህ ዓመት ብቻ 2 ሺህ 230 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል - ተመድ

    በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት በዚህ ዓመት ብቻ 2 ሺህ 230 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እንዳረጋጋጠ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታወቀ።

    ከእነዚህ መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት የተገደሉት በድሮን ጥቃቶች መሆኑን ገልጿል። ይህም “የግጭቱ መገለጫ ባህሪ እየሆነ መጥቷል” ብሏል።

    የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ተርክ “ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የጦርነት ሕጎችን ችላ ማለታቸውን” አውግዘው፤ ይህም የጦር ወንጀል ሆኖ ሊቆጠር እንደሚችል ተናግረዋል።

    በሱዳን መንግሥት ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ከሦስት ዓመት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን እልባት ያላገኘ ሲሆን በዓለም አስከፊ ከሆኑ ሰብዓዊ ቀውሶችን አንዱን አስከትሏል።

    እየተካሄደ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ከቅርብ ወራት ወዲህ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የድሮን ጥቃቶችን ፈፅመዋል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት ከባለፈው ዓመት ጥር እስከ ሰኔ ወር ያሉትን ጊዜያት በሚሸፍነው ሪፖርቱ “በሱዳን እየጨመሩ የመጡት የድሮን ጥቃቶች የግጭቱን ገፅታዎች የሚያሳዩ ናቸው፤ ተፋላሚዎቹ ከጦር ግንባሮች እና በቁጥጥራቸው ሥር ካሉ ቦታዎች ርቀው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል” ብሏል ።

    ድርጅቱ ከሪፖርቱ ጋር አብሮ ባወጣው መግለጫውም በጦርነቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 2 ሺህ 230 ከፍ ማለቱን እና ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 630ዎቹ የተገደሉት በድሮን ጥቃቶች መሆኑን ማረጋገጡን ገልጿል። ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችልም አመልክቷል።

    በግጭቱ በቀጥታ ከተገደሉት በተጨማሪ የኃይል እና የውሃ መሠረተ ልማቶች የድሮን ጥቃቶች ዒላማ መሆናቸው እየጨመረ መምጣቱንም ሪፖርቱ አክሏል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  19. የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላን ተከስክሶ 19 ሰዎች ሞቱ

    የሩሲያ ወታደራዊ የመጓጓዣ አውሮፕላን በሳይቤርያ ተከስክሶ ሁሉም 19 ተሳፋሪዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያ ዘገበ።

    የሩሲያ መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ኤኤን-12 የተባለው ወታደራዊ አውሮፕላን በኬሜሮቮ ግዛት “ሰዎች በማይኖሩበት አካባቢ የታቀደ በረራ” ሲያካሂድ አደጋው ተከስቷል።

    አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፤ ትክክለኛውን መንስዔ ለማወቅ የሩሲያ አቪዬሽን ባለሥልጣን ምርመራ ከፍቷል።

    የአካባቢው አገረ ገዢ ኢላያ ሴርዴዩክ የድንገተኛ ጊዜ ሠራተኞች ተሰማርተው “በፍጥነት እሳቱን እንዳጠፉ” ተናግረዋል።

    አደጋው የተከሰተው ያጉኖቮ በተባለ መንደር ሲሆን ፖሊስ በአካባቢው እንቅስቃሴን እንዳይደረግ አግዷል።

    አገረ ገዢው እንዳሉት አሁን ላይ ዋነኛው ሥራ ለሚካሄደው ምርመራ ድጋፍ መስጠት ነው።

    የእሳት አደጋ ሠራተኞች ሥራቸውን ሲያከናውኑ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችንም አጋርተዋል።

    አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት ያለውን ቅጽበት የሚያሳዩ ከደኅንነት ካሜራ የተገኙ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወሩ ይገኛሉ።

  20. በዌስት ባንክ የ72 ዓመት ፍልስጤማዊት በእስራኤል ሰፋሪዎች መገደሏ ተገለጸ

    በእስራኤል በኃይል በተያዘው እና በቅርቡ የእስራኤል ሰፋሪዎች በገቡበት የዌስት ባንክ መንደር ውስጥ በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ አንዲት ሴት መገደሏን እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ክስተቱን በተመለከተ ከሁለቱም ወገን የሚወጡ መረጃዎች የተለያዩ ናቸው።

    በአካባቢው የሚኖሩ ፍልስጤማውያን፣ በፍልስጤም ባለሥልጣናት ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ጀሪቾ አቅራቢያ በሚገኘው አል ዱዩክ አልታህታ ሰፋሪዎቹ ጥቃት መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር በበኩሉ የፍልስጤም መኪና የእስራኤል ተሽከርካሪን በመግጨት ጥቃት መፈፀሙን ገልጿል።

    ከዚያም በምላሹ ተኩስ በከፈተው እስራኤላዊ ላይ ድንጋይ መወርወራቸውን አስረድቷል። ሆኖም ጦሩ ተተኩሶባቸው የተገደሉትን ሴት በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

    በአካባቢው የሚኖሩ ፍልስጤማውያን እንዳሉት ግን ሰኞ ምሽት የተፈፀመው ጥቃት የደረሰው እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በጀመሩት ትንኮሳ ነው።

    ፍልስጤማውያን ሕፃናት ድንጋይ መወርወር ጀመሩ ያሉት ነዋሪዎቹ፣ ከዚያም ሰፋሪዎቹ ተኩስ መክፈታቸውን እና በቤታቸው ደጅ ላይ የነበሩ ፋዳ አል ፋሂዳ የተባሉ የ72 ዓመት ሴት መገደላቸውን ተናግረዋል።

    የሟች የልጃቸው ሚስት የሆነችው ኔማ አል ፋሂዳ፣ ፋዳ ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመትተው መሞታቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች።

    በቅርቡ በዌስት ባንክ በሚገኝ አዲስ አካባቢ እስራኤላውያን መስፈራቸውን ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።

    ሰፋሪዎቹ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት "ምስጢራዊ" ባሉት ዘመቻ በመንደሯ የሚገኙ ስምንት ቤቶችን ገዝተው ገብተዋል።

    መኖሪያ ቤቶቹ የእስራኤል ኃይሎች ሙሉ ቁጥጥር በሚያደርጉበት አካባቢ የሚገኙ ናቸው።

    በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እስራኤል የምታካሂደው ሁሉም ሰፈራ ሕገ ወጥ ነው።

    • ተያያዥ ዜናዎች፡