የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የሳይበር ደኅንነት
ክስተት” እንዳጋጠመው እና የመረጃ ጥሰቱን የተፅዕኖ መጠን ለማወቅ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ለደንበኞቹ አሳወቀ።
ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ በክስተቱ የደንበኞች
የፋይናንስ መረጃ ለሌላ አካል ስለመድረሱ የሚያመለክት ማስረጃ እንዳልተገኘ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 9/2019 ዓ.ም. ለ‘ሼባ ማይልስ’
ተጠቃሚዎች በላከው የኢሜይል መልዕክት ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታማኝ ደንበኞች አገልግሎት
የሚያገኙበት ‘ሼባ ማይልስ’ ከ5.4 ሚሊዮን ገደማ ደንበኞች እንዳሉት ባለፈው ዓመት የወጣ መረጃ ያመለክታል።
“የመረጃ ጥሰት የሕዝብ
ማስታወቂያ” በሚል ርዕስ የተላከው ኢሜይል ክስተቱ ያጋጠመው የሼባ ማይልስ ሥርዓት ላይ ብቻ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።
ለሼባ ማይልስ ደንበኞች የተላከው መልዕክት፣
በአየር መንገዱ “በሲስተሞቻች ላይ ውስን አድማስ” ያለው “የሳይበር ደኅንነት ክስተት” ማጋጠሙን አስረድቷል። “ክስተቱ የተወሰኑ
ደንበኞችን መረጃዎች ነክቶ ሊሆን ይችላል” ብሏል።
የአየር መንገዱ መልዕክት፣ ክስተቱ ያጋጠመው
“በቅርቡ” እንደሆነ ቢገልጽም ትክክለኛውን ቀን አላስቀመጠም።
በዚህ ጥሰት ምን ያህል ደንበኞች እንደተነኩ፣ ምን ዓይነት መረጃ
ጥሰት እንደደረሰበት ወይም ክስተቱ እንዴት እንደተደረሰበት በግልፅ አላሳወቀም።
ቢቢሲ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ተጨማሪ
መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።
ጉዳዩ “በከፍተኛ ትኩረት እና ጥንቃቄ” መያዙን
የገለጸው አየር መንገዱ፣ “ክስተቱን ለመመርመር እና ሙሉ ተፅዕኖውን
ለመገምገም ከሳይበር ደኅንነት አጋሮቻችን እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየሰራን ነው” ብሏል።
አየር መንገዱ ጉዳዩን ለመፍታት “ሙሉ ትኩረት
እና ሀብቱን” ማዋሉንም አክሏል። “ተጨማሪ መረጃዎች ሲገኙ” ለደንበኞቹ እንደሚያሳውቁም ቃል ገብቷል።
ደንበኞች ራሳቸውን ከሚደርሳቸው
“ከማንኛውንም አጠራጣሪ ወይም አስፈላጊ ያልሆነ ግንኙት” እንዲጠብቁ
አየር መንገዱ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህ ዓይነት የበይነ መረብ (ሳይበር) ደኅንነት ክስተት እንዳጋጠመው ያስታወቀው፣ በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ከፍተኛ የአገልግሎ መስተጓጎሎች ባጋጠሙበት ወቅት ነው። ባለፈው
ሳምንት ግዙፉ ማይክሮሶፍት ባጋጠመው መስተጓጎል አገልግሎቶቹ ተቋርጠው ነበር።
በአሜሪካ ደግሞ በአገሪቱ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ
ሥርዓት ላይ ባጋጠመ ክስተት ምክንያት በ25 ዓመት ውስጥ ረጅም ለተባለ ጊዜ በረራዎች ተቋርጠዋል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅነንት ተቋም በበኩሉ ማክሰኞ
ዕለት የመሥሪያ ቤቱ የውስጥ ግንኙነት ሥርዓት ተቋርጦ እንደነበር አሳውቋል። የአገሪቱ ባንኮችም ተመሳሳይ መስተጓጎል አስተናግደዋል።
ከዚህ አስቀድሞ ደግሞ በፈረንሳይ ሱፐርማርኬቶች
ማቀዝቀዣ ፍሪጅ መቆጣጠሪ ሥርዓት ላይ በተፈጸመ የሳይበር ጥቃት ምክንያት ምግቦች ተበላሽተዋል። ቀጥሎም በተለያዩ የአውሮፓ አገራት
ተመሳሳይ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል።
ፈረንሳይ፣ የሱፐርማርኬቶች ማቀዝቀዣ የሙቀት
መጠናቸው እንዲጨምር ላደረገው የሳይበር ጥቃት ተጠያቂ ያደረገችው ኢራንን ነው። ኢራን ግን ክሱን ውድቅ አድርጋለች።