በሴኔጋል 100 ስደተኞችን ይዞ የነበረ ጀልባ ወቅያኖስ ላይ መገልበጡ ተዘገበ
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል የባሕር ዳርቻ አካባቢ 100 የሚጠጉ ስደተኞችን አሳፍሮ ነበር የተባለ ጀልባ መገልበጡን ተከትሎ፣ ባለሥልጣናት ነፍስ የማዳን እና የፍለጋ ሥራ እያከናወኑ መሆኑ ተዘገበ።
የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች በአደጋው አንድ ሰው መሞቱን ቢገልጹም፣ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ቢያንስ አራት አስከሬኖች መገኘታቸውን እና በርካቶች አሁንም የደረሱበት አለመታወቁን ገልጸዋል።
በሰሜን ምዕራብ ሴኔጋል በምትገኘው ቲዬፕ ከተማ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ሲያጋጥም ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም በደረሰው አደጋ ቢያንስ 39 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ በሴኔጋል ስደተኞች ላይ ከደረሱ አሰቃቂ አደጋዎች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ኦማር ሶው፣ የአሁኑ አደጋ ከሌሊቱ 8:00 ሰዓት አካባቢ መከሰቱን እና ከየባሕር ዳርቻው ላይ የእርዳታ ጩኸት ይሰማ እንደነበር ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
አደጋው በደረሰበት ጀልባ ላይ 100 የሚጠጉ ሰዎች እንደነበሩ ከመካከላቸውም አምስት ሴቶች እንደሆኑ ለፖሊስ ቃሉን የሰጠ አንድ ከአደጋው የተረፈ ተሳፋሪ ተናግሯል።
ፖሊስ አደጋው የደረሰበት ጀልባ ላይ የማንነት ሰነዶችን፣ በርካታ ሞባይል ስልኮችን እና ሌሎች የግል ንብረቶችን አግኝቷል። ከእነዚህ መካከል የአንድ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሊሆን ይችላል ተብሎ የተገመተ የትምህርት ቁሳቁስም ተገኝቷል።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዲዮማዬ ፋዬ ረቡዕ በተካሄደ የካቢኔ ስብሰባ ላይ ወደ አውሮፓ ለመድረስ በሕገ-ወጥ መንገድ በባሕር ለመጓዝ የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር እንደገና መጨመሩ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ባለፈው ወር በተከሰተው እና ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች ከሞቱበት አደጋ በኋላም ፕሬዝዳንቱ ሴኔጋላውያን ለአደገኛ የባሕር ጉዞዎች ሕይወታቸውን እንዳያጋልጡ አሳስበው ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) በጥቅምት ወር እንደገለጸው፣ እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ በምዕራብ አፍሪካ የአትላንቲክ ውቅያኖስ የስደት መስመር ላይ ቢያንስ 454 ሰዎች ሞተዋል ወይም ደብዛቸው ጠፍቷል።
ጀልባዎች እማኝ የሚሆን የተረፈ ሰው ወይም ምልክት ሳይተዉ የሚጠፉባቸው አደጋዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ይህ የባሕር ላይ አደጋ ሰለባዎች ቁጥር ከእውነታው ያነሰ ሊሆን እንደሚችል ድርጅቱ አሳስቧል።