ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትውልደ ኢትዮጵያዊው የአሜሪካን ጥብቅ መረጃዎች ለኢትዮጵያ አሳልፎ መስጠቱን አመነ
ትውልደ ኢትዮጵያዊው አብርሃም ተክሉ ለማ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የአሜሪካን ምስጢራዊ መረጃ ለኢትዮጵያ መንግሥት ለማስተላለፍ በማሴር ወንጀል በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ መሆኑን አመነ።
የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በሜሪላንድ የሚኖረው የ53 ዓመቱ አብርሃም ተክሉ ለማ፣ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2021 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ከፍተኛ ሚስጥራዊነት ያላቸውን የአሜሪካ መረጃዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ለማስተላለፍ በተደረገ ሴራ ውስጥ መሳተፉን አምኗል።
የአሜሪካ ፍትህ መስሪያ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ማክሰኞ ጥቅምት 24/2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ረዳት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጆን ኤ. አይዘንበርግ "ለማ በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ከፍተኛ የሆነ ክህደት ፈጽሟል" ማለታቸውን ጠቅሷል።
አቃቤ ሕጉ አክለውም አብርሃም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስተዳዳሪነት የነበረውን የይለፍ ፈቃድ በመጠቀም፣ ደህንነቱ ከተጠበቀ ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ምስጢራዊ መረጃን ጨምሮ የብሔራዊ መከላከያ መረጃን በሕገወጥ መንገድ በማውጣት ለኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣኖች አስተላልፏል" ሲሉ ተናግረዋል።
አብርሃም ከአሜሪካ መንግሥት የወሰዳቸውን ሚስጢራዊ መረጃዎች "በአንድ ክልላዊ ግጭት ውስጥ የነበሩ ታጣቂ ኃይሎችን ለመፈለግና ለመግደል እንደሚጠቀሙበት ተስፋ አድርጎ ነበር" ሲሉ አብራርተዋል።
የኤፍቢአይ የፀረ-ስለላና የስለላ ወንጀሎች ክፍል ረዳት ዳይሬክተር ሮማን ሮዝሃቭስኪ "ለዩናይትድ ስቴትስ ሕገ መንግሥት ጥበቃ እሰጣለሁ ብሎ ቃለ መሃላ ቢፈጽምም፣ አብርሃም ለማ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክሎ የስለላ ተግባር በመፈጸም አገራችንን ክዷል" ማለታቸውን የፍትህ ሚኒስቴር በመግለጫው ጠቅሷል።
አብርሃም ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ የሰጣቸው ምስጢራዊ መረጃዎች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ መዋላቸውንም የኤፍቢአይ ረዳት ኃላፊ ተናግረዋል።
"ለማ በራሱ የእምነት ክህደት ቃል መሠረት ምስጢራዊ የብሔራዊ መከላከያ መረጃ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አስተላልፏል፤ እነሱም ይህን መረጃ እየተካሄደ በነበረው ግጭት ወቅት በተካሄዱ ወታደራዊ ዘመቻዎች ላይ ተጠቅመውበታል" ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም አብርሃም ላይ ስለቀረበው ክስ ምንም ያለው ነገር የለም።
አብርሃም በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት ለበርካታ የአሜሪካ መንግስሥት ተቋማት የመረጃ ቴክኖሎጂ ባለሙያ ሆኖ ይሰራ ነበር።
ከሰራባቸው ተቋማት መካከል የአሜሪካ ብሔራዊ የስለላ ምርመራ ቢሮ ፣ የውጭ ጉዳይ እና የፍትህ መስሪያ ቤቶች ይገኙበታል።
የፍትህ መስሪያ ቤት እንደገለጸው፣ በቀረቡ የግንኙነት ሰነዶች ውስጥ አብርሃም ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በጦርነት ላይ በነበሩ ታጣቂ ቡድኖች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ሲያበረታታ እንደነበር ያመለክታሉ።
አብርሃም ታህሳስ 9/2014 ዓ.ም. ለአንድ ተባባሪው ባስተላለፈው መልዕክት "እነዚህን ሰዎች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት አለብን። አለበለዚያ በኢትዮጵያ መቼም ሰላም አይኖርም" ሲል መጻፉ በፍትህ ሚኒስቴር መግለጫ ላይ ተካትቷል።
በዚያኑ ቀን አብርሃም ተጨማሪ መረጃ ለተባባሪው አስተላልፎ "እባክህ ድሮ[ኖችን] ላክ "ብሎ ጽፎ ነበር።
አቃቤ ሕጉ በተጨማሪም "የምስጢራዊ መረጃዎች በሚገኙበት ለመንቀሳቀስ የይለፍ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ለዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ ታማኝነታቸው የሚያሳዩ መሆናቸውን ቃል ይገባሉ፤ እንዲሁም ምስጢራዊ መረጃዎችን የመጠበቅ ሕጋዊና ሥነ ምግባራዊ ኃላፊነት አለባቸው። ይህንን አደራ የሚያፈርሱ ሰዎች በሕግ ሙሉ ኃይል ይከሰሳሉ" ብለዋል።
እንደ አቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ግለሰቡ ያስተላለፋቸው መረጃዎች በዚያን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ከነበረው የትጥቅ ግጭት ጋር በቀጥታ የተያያዙ እንደነበሩ ተገልጿል።
ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ያስተላለፋቸው መረጃዎች የአሜሪካን ብሔራዊ ደኅንነት ሊጎዱ የሚችሉ ሚስጥራዊ መረጃዎች እንደነበሩ አቃቤ ሕግ አስረድቷል።
አቃቤ ሕጎች እንደሚሉት፣ አብርሃም በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ የደህንነት ይለፍ ፈቃድ ያለው ሲሆን፣ ይህንን ልዩ የመረጃ መዳረሻ በመጠቀም በርካታ ሚስጥራዊ ሰነዶችን፣ ማስታወሻዎችን፣ ፎቶግራፎችንና ሌሎች ጥንቃቄ የሚሹ መረጃዎችን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የፖለቲካ፣ የወታደራዊ እና የመረጃ ደህንነት ኃላፊዎች አስተላልፏል።
በኮሎምቢያ ዲስትሪክት የአሜሪካ ዓቃቤ ሕግ ዣኒን ፌሪስ ፒሮ "ለማ ከሁለት ዓመታት በላይ የተጣለበትን እምነት በመጠቀም በከፍተኛ ደረጃ ሚስጢራዊነቱ የተጠበቀን የአሜሪካ መንግሥት መረጃ ለውጭ መንግሥት ሲያስተላልፍ ቆይቷል" ሲሉ ወንጅለውታል።
"ይህን በማድረጉ ለፈጸመው ቃለ መሐላ፣ ለሥራ ባልደረቦቹ እና ለአገሩ ክህደት ፈጽሟል፤ በተመሳሳይም የአገራችንን ብሔራዊ ደህንነት ለአደጋ አጋልጧል። ወንጀሉን መፈጸሙን ማመኑ ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል፤ የአሜሪካን እጅግ ስሱ ምስጢሮች የሚያጋልጡ ሰዎች ይመረመራሉ፣ በሕግ ይከሰሳሉ እና ተጠያቂ ይደረጋሉ።" ብለዋል።
የኤፍቢአይ የፀረ-ስለላና የስለላ ወንጀሎች ክፍል ረዳት ዳይሬክተር ሮማን ሮዝሃቭስኪ በበኩላቸው "ጥፋተኝነቱን ማመኑ ግልጽ ማሳሰቢያ ሊሆን ይገባል፤ ኤፍቢአይና አጋሮቻችን የውጭ ስለላ አገልግሎቶችን እና ከእነሱ ጋር በመተባበር ከዩናይትድ ስቴትስ ጥቅም በተቃራኒ የሚሰሩ ማንኛውንም ግለሰቦች ለማስቆም ያለ እረፍት እንደሚሰሩ ያሳያል" ብለዋል።
አብርሃም የስለላ ተግባራቱን በሚፈጽምበት ወቅት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በሚገናኝበት ጊዜ እንቅስቃሴዎቹን ለመደበቅ የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስድ እንደነበር ተገልጿል።
ከእነዚህም መካከል ምስጢራዊ ሰነዶችን ከያዙ ተቋማት ውስጥ መረጃዎቹን በኤሌክትሮኒክስ ቅጂ በማውጣት እና ከፍተኛ የደህንነት የመረጃ ይዘት ያላቸውን በእጅ በመጻፍ መውሰዱን እና በድብቅ ማውጣቱ ተጠቅሷል።
አብርሃም ምስጢራዊ መረጃዎቹን በእጅ ጽሑፍ በመገልበጥ እና ደህንነታቸው ከተጠበቀ የአሜሪካ ተቋማት በማውጣት ለኢትዮጵያ መንግሥት መስጠቱ ተጠቅሷል።
አብርሃም ለውጭ መንግሥት የብሔራዊ መከላከያ መረጃ ለማስተላለፍ በማሴር የቀረበበትን ክስ በማመኑ ከ10 እስከ 22 ዓመት የሚጠጋ እስራት ሊፈረድበት ይችላል ተብሏል።
ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን ለመስጠት እአአ ለሚያዝያ 14/ 2027 ቀጠሮ ሰጥቷል።