ቀጥታ , በአርሲ ሽርካ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት የተጠረጠሩ 73 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ውስጥ በሽርካ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት የተጠረጠሩ “የፋኖ አባላት እና የኦነግ ሸኔ አባላትን” ጨምሮ 73 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ተናገሩ። ኃላፊው መግለጫውን የሰጡት አሜሪካ፤ በንጹኃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች እንዲመረመሩ እና የወንጀሉ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ከጠየቀች ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በደቡብ አፍሪካ በአርሶ አደር ላይ ዘግናኝ የግድያ ሙከራ የፈጸሙ 5 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

    በደቡብ አፍሪካ አንድ አርሶ አደር ላይ ተኩስ በመክፈት እና በስለት ጆሯቸውን በመቁረጥ ዘግናኝ የግድያ ሙከራ የፈጸሙ 5 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

    ዶኖቫን ማርክስ የተሰኙ የ50 ዓመት አርሶ አደር ባለፈው ረቡዕ በደቡብ አፍሪካ ሰሜን ምዕራብ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ቬንተርስዶርፕ በተባለች አነስተኛ ከተማ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ስርቆት ተፈጽሞባቸው ነበር።

    ዶኖቫን ወደ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ባጠበቋቸው ሰዎች ቢተኮስባቸውም እንዲሁም በስለት ቢወጉም ሕይወታቸውሊተርፍ ችሏል። በደረሰባቸው ጥቃት ጆሯቸው መቆረጡን ፖሊስ ገልጿል።

    ይህን ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩት አምስቱም ግለሰቦች በሳምንቱ መጨረሻ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው በዶኖቫን ባለቤት እና ቤተሰብ ዘንድ እፎይታ ፈጥሯል።

    ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ እና መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ግድያውን ከመፈጸማቸው በፊት ወደ ዶኖቫን ቤት በመሔድ ሳር በማጨድ ላይ የነበረን ሠራተኛን እጅ እና እግር በማሰር “ዶኖቫን የት እንደሆነ” ጠይቀው እንደነበርተገልጿል።

    ዶኖቫን ወደ ቤቱ ሲመለሱ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ጠብቀው ደረታቸው አካባቢ እንደተኮሱባቸው ፖሊስ ገልጿል።

    “ከዚያም ወደ ቤት ውስጥ ጎትተው በማስገባት እጆቹንና እግሮቹን ካሰሩ በኋላ ሰውነቱን በስለት ወግተውታል” ተብሏል። ተጠርጣሪዎቹሦስት የጦር መሣሪያዎችን ወስደው በአርሶ አደሩ የጭነት መኪና ማምለጣቸው ተገልጻል።

    አርሶ አደሩ ራሳቸውን ፈርተው እርዳታ የሚሰጥ ሰው ጠርተዋል። በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል ተወስደውም አሁንም በሕክምና ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን ዶክተሮች ጆሯቸውን ማዳን ባለመቻላቸው ሰው ሠራሽ ጆሮ ሊያስፈልጓቸው ይችላሉ።

    የደቡብ አፍሪካ እርሻ ሚኒስትር ዊሊ ኦካምፕ በዶኖቫን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን፣ “በሀገራችንውስጥ ለእንደዚህ ዓይነት ትርጉም የለሽ እና አሰቃቂ ድርጊቶች ቦታ የለም” በማለት ተናግረዋል።

  2. በሰባት የአውሮፓ አገራት በመደብሮች የሚገኙ ማቀዝቀዣዎች የሳይበር ጥቃት ደረሰባቸው

    በሰባት የአውሮፓ አገራት በሚገኙ በደርዘን የሚቆጠሩ መደብሮች ውስጥ ያሉ ፍሪጆች እና ማቀዝቀዣዎች የሳይበር እንደሆነ የሚጠረጠር ጥቃት እንደደረሰባቸው ተሰምቷል።

    በዚህ ጥቃት፤ በቤልጂየም እና በሉክሰምበርግ የሚገኙ ወደ 40 የሚጠጉ የዴልሄዝ መደብሮች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    በስዊድን፣ በአየርላንድ፣ በኔዘርላንድስ እና በኤስቶንያ ደግሞ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መደብሮች መጎዳታቸው ተገልጿል።

    ጉዳት ከደረሰባቸው ማቀዝቀዣዎች መካከል አንዳንዶቹን የሚያመርተው ሳብኮቤል የተባለው የቤልጂየም ኩባንያ እንደገለጸው፣ ፍሪጆቹ ማቀዝቀዝ እንዳይችሉ ተደርገዋል።

    ይህ ሁኔታ ከወራት በፊት በፈረንሳይ መደብሮች ላይ ከተከሰተው ጥቃት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ይታመናል።

    የሳብኮቤል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቴፈን ሞይላንስ፤ ድርጊቱ የሳይበር ጥቃት እንደሆነ ገልጸው ኩባንያው “ጉዳት የደረሰበትን ሲስተም ከኔትወርኩ የመለየት ሥራ ሌት ከቀን እየሠራ ነው” ብለዋል።

    ሥራ አስፈፃሚው አክለውም ባለፈው ወር ላይ ተመሳሳይ ጥቃት በፈረንሳይ ከደረሰ በኋላ የደንበኞቻችን ፍሪጆች ከእንዲህ ዓይነት ተጋላጭነት ለመጠበቅ እየሠራን ነበር ብለዋል። ሆኖም “የሶፍትዌር እደሳ ብቻ አለነበረም የሚያስፈልገው” ሲሉ ተናግረዋል።

    እንዲህ ዓይነቱን ጥቃት ለመከላከል ቀላሉ መፍትሔ ፍሪጆቹን እና ማቀዝቀዣዎቹ ደህንነቱ የተጠበቀ ኢንተርኔት መጠቀም መሆኑንም ሞይላንስ ጠቁመዋል።

  3. ሪፖርተር ጋዜጣ “ላልተወሰነ ጊዜ” ከኅትመት እና ስርጭት ሙሉ በሙሉ ታገደ

    ሪፖርተር ጋዜጣ ከዛሬ ጥቅምት 23/2019 ዓ. ም. ጀምሮ “ላልተወሰነ ጊዜ” ከኅትመት እና ከስርጭት ሙሉ በሙሉ ማገዱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታወቀ።

    በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር ኃላፊነቱ የተወሰነ ማኅበር ሥር የሚተዳደረው ሪፖርተር ጋዜጣ 30 ዓመታት በኅትመት ቆይቷል።

    በእነዚህ ጊዜያት ከአማርኛ ዕትሙ በተጨማሪ “ዘ ሪፖርተር” የተሰኘ በእንግሊዝኛ የሚታተም ሳምንታዊ ጋዜጣ እና ወርሐዊ መጽሔት ለአንባቢያን ያቀርባል።

    የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሚዲያውን መታገድ በተመለከተ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ “ሪፖርተር አማርኛ፣ ዘ ሪፖርተር እግሊዝኛ እንዲሁም ኢትዮጵያን ሪፖርተር የዲጂታል ፕላትፎርም ላይ የሚሰራጩ ይዘቶች ላይ ከአንድ ዓመት በላይ ክትትል” ማድረጉን ገልጿል።

    በተደረገው የይዘት ክትትል “ተደጋጋሚ የሕግና የሙያ ሥነ ምግባር ጥሰቶች በሚዲያው መፈጸሙ ተረጋግጧል” ሲል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

    “በሀገር ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውድ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በማንሳት የሚሰጣቸው አርዕስት ማጮህ /Sensationalize/፣ በቁንጽል ዕይታ ላይ ተመሥርቶ በመዘገብ በኅብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬ እና ብዥታን መፍጠር” ጋዜጣው የፈጸማቸው የሕግ እና የሙያ ሥነ ምግባር ጥሰቶች መሆናቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።

    በተጨማሪም ጋዜጣው፤ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም እና ዲፕሎማሲ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት፣ የሀገር ገጽታን፣ ብሔራዊ ደኅንነትን የሚጎዱ፣ የሕዝቦችን አብሮነት እና እሴት የሚሸረሽሩ እንዲሁም ሚዛናዊነት የጎደለው አድሏዊ ዘገባዎችን ማሰራጨቱ ተገልጿል።

    እነዚህን የሕግ እና የሙያ ሥነ ምግባር ጥሰቶችን እንዲያርም ላለፈው አንድ ዓመት ውይይት መደረጉን የሚገልጸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፤ ጋዜጣው መታረም ያልቻለ በመሆኑ “የምዝገባ ምስክር ወረቀቱ ከሰኞ ጥቅምት 23/2019 ዓ. ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ከኅትመት እና ከስርጭት ሙሉ በሙሉ ታግዶ እንዲቆይ መወሰኑን” አስታውቋል።

    ይህ ውሳኔ የሕግ እና የሙያ ሥነ ምግባር ግዴታዎች ተሟልተዉ ተግባራዊ እስከሚደረጉ ድረስ የሚቆይ መሆኑን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

  4. በአርሲ ሽርካ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት የተጠረጠሩ 73 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ

    በኦሮሚያ ክልል አርሲ ውስጥ በሽርካ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት የተጠረጠሩ “የፋኖ አባላት እና የኦነግ ሸኔ አባላትን” ጨምሮ 73 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ተናገሩ።

    ኃላፊው መግለጫውን የሰጡት አሜሪካ፤ በንጹኃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች እንዲመረመሩ እና የወንጀሉ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡከጠየቀች ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

    በአዲሱ የኦሮሚያ ክልል የዞን አወቃቀር ደቡብ ምሥራቅ ዞን ሽርካ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

    በወረዳው ቢርቦ እና ጮሌ ቀበሌ ከተገደሉ ሰዎች በተጨማሪ ከ20 በላይ ነዋሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    በሽርካ ወረዳ ከደረሰው ጥቃት ቀደም ብሎ አጎራባች በሆነው መርቲ ወረዳ ጎራ ሲሊንጎ ቀበሌ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞ ከ15 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የወረዳው ምንጮች ለቢቢሲ መናገራቸውይታወሳል።

    የኢትዮጵያኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ በሁለቱ ወረዳዎች በተፈጸመውጥቃት 60 ምዕመኖቿ እንደተገደሉአስታውቃለች።

    ይህን ጥቃት አስመልክቶ ከሳምንት በፊት መግለጫ የሰጡት የአሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽንአገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ “የፅምዶ አባላትን” ተጠያቂ አድርገው ነበር።

    ኃላፊው ዛሬ ጥቅምት 23/2019 ዓ. ም. በድጋሚ በሰጡት መግለጫቸው ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ 73 ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አሳውቀዋል።

    በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች የፋኖ እና መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚለው ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባላት መሆናቸውንም ተናግረዋል።

    “እነዚህ 73 ሰዎች አንደኛ የጽንፈኛውፋኖ አባላት በዚያ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሽብርተኛውሸኔ አባላቶች ናቸው። እነዚህ ሁለት ኃይሎች ተናብበው ነው የሚሠሩት” በማለት ተናግረዋል።

    የክልሉ መንግሥት “ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ከማዋል በተጨማሪ” እየወሰደ ስላለው እርምጃ የተናገሩት አቶ ኃይሉ፤ በኦሮሚያ ክልል “የፅምዶ ኃይሎች እንቅስቃሴየሚያደርጉባቸውን 6 ቀበሌዎችንየማጽዳት ሥራዎች እየተከናወነ ይገኛል” ሲሉ በዛሬው መግለጫቸው ገልጸዋል።

    የክልሉ መንግሥት ጥቃቱን አስመልክቶ በቁጥጥር ሥር ስለዋሉ ተጠርጣሪዎችያሳወቀው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ፣ በአርሲ ጥቃት የፈጸሙ ለፍትሕ እንዲያቀርቡ ጥሪ ካቀረበ በኋላ ነው።

    ቢሮው ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 21/2019 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ አሜሪካ ሃይማኖት እና ብሔርን መሠረት ያደርጉ ጥቃቶችን እንደምታወግዝ አስታውቋል።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  5. የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ በየመን የድርጅቱ ሠራተኛ በሁቲዎች እጅ እያለ መሞቱን አወገዙ

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በየመን በሁቲ ቁጥጥር ሥር የነበረ የድርጅቱ ሠራተኛ መሞቱን ተከትሎ “እጅግ ማዘናቸውን” ገለጹ።

    ሟቹ መሐመድ ኢብራሂም አል-ሻሚ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ውስጥ ይሰራ የነበረ ሲሆን፣ ከሰኔ 6 ቀን 2024 ጀምሮ በሁቲዎች ምንም ክስ ሳይመሰረትበት ታስሮ ቆይቷል።

    ጉተሬዝ ቅዳሜ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መግለጫ፣ አል-ሻሚ በሁቲዎች እስር ውስጥ የሞተ ሁለተኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኛእንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት እንደ አውሮፓውያኑ በየካቲት 2025 የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሠራተኛ በእስር ላይ ሳለ ሕይወቱ አልፎ ነበር።

    “አሁንም በእስር ላይ ስላሉት የተመድ ሠራተኞች፣ የቀድሞ የተመድ ሠራተኞች እና የሰብዓዊ ድርጅቶችና የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ሠራተኞች የደህንነት እና የጤና ሁኔታ እጅግ ያሳስበኛል” ሲሉ ጉተሬዝ ተናግረዋል።

    በሁቲዎች እስር ውስጥ የሞተው የመጀመሪያው የተመድ ሠራተኛ አህመድ ባአላዊ ሲሆን፣ እሱም የዓለም የምግብ ፕሮግራም የአገር ሠራተኛ ነበር። እአአ ከጥር 23 2025 ጀምሮ በሰሜን የመን በአካባቢው ባለሥልጣናት በዘፈቀደ ታስሮ ከቆየ በኋላ በየካቲት 11 2025 ሕይወቱ አልፏል።

    የመን እአአ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በግጭት ውስጥ ትገኛለች። በዚያ ዓመት የሁቲ ታጣቂዎች ዋና ከተማዋን ሰነዓን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን መንግሥት ለመደገፍ በሳዑዲ አረቢያ የሚመራ ወታደራዊ ጥምረት በመጋቢት 2015 ጣልቃ ገብቷል።

    ግጭቱ በዓለም ላይ እጅግ ከባድ የሰብዓዊ ቀውሶች ካስከተሉ መካከል አንዱ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ሆነው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  6. በፍሎሪዳ የንግድ አውሮፕላን ተከስክሶ በውስጡ የነበሩ 9 ሰዎች ሞቱ

    በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት አንድ የንግድ አውሮፕላን እሁድ ዕለት በመኖሪያ ሰፈር ተከስክሶ በውስጡ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች በሙሉ መሞታቸውን የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    አደጋው የተከሰተው ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመዝናኛ ስፍራ ማር-አ-ላጎ 14 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።

    ከአደጋው በኋላ የተነሱ ምስሎች በመኖሪያ አካባቢ በሚገኝ መንገድ መሀል ትልቅ ጉድጓድ መፈጠሩን፣ እሳት መነሳቱን እና የከሊርጀት 60 (Learjet 60) አውሮፕላን ስብርባሪዎችን አሳይተዋል።

    የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር እንዳስታወቀው፣ አውሮፕላኑ ከአውስቲን ቴክሳስ ተነስቶ ወደ ባሃማስ እየተጓዘ ነበር።

    የአሜሪካ ሚዲያዎች እና የበረራ መረጃ ትንተናዎች እንደሚያመለክቱት፣ አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት በሰከንድ መቶዎች የሚቆጠሩ ጫማዎችን እየተምዘገዘገ እየወረደ ነበር።

    ከአደጋው ቀደም ብሎ በተቀዳ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ድምጽ ውስጥ፣ አብራሪው አውሮፕላኑ በደቂቃ 10,000 ጫማ እየወረደ መሆኑን ሲገልጽ ይሰማል።

    በመቀጠልም አብራሪው የድንገተኛ አደጋ መከሰቱን አስጠንቅቆ “በከፍተኛ ፍጥነት እየወረድን ነው፤ በደቂቃ 20,000 ጫማ እየወረድን ነው” ብሎ መጮሁ ተገልጿል።

    “ልንከሰከስነው... ጊዜ የለንም” ሲልም ለመቆጣጠሪያው ማማ መናገሩ ተዘግቧል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቀ እና ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ቪዲዮ፣ የአደጋውን ቅጽበት ያሳያል። በቪዲዮው ላይ መኪኖች በመኖሪያ አካባቢ በሚገኝ መንገድ ላይ ሲጓዙ ይታያሉ፤ ከዚያም አውሮፕላኑ በቀጥታ ወደ መሬት ተቀልብሶ ሲወድቅ እና ትልቅ ፍንዳታ ሲፈጥር ይታያል።

    የፍሎሪዳ ገዢ ሮን ዴሳንቲስ ከአደጋው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ያንን ቪዲዮ ስታይ በጣም የሚያስደነግጥ ነው። እንደ ሚሳይል እየተምዘገዘገ ወደ ታች እየመጣ ይመስላል፣ ከዚያም ግዙፍ ፍንዳታ ይከሰታል፤ ፍርስራሹም በየአቅጣጫው ይበተናል” ብለዋል።

    እስካሁን በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ማንነት በይፋ አልተገለጸም። ዴሳንቲስ በበኩላቸው “እስካሁን ድረስ መሬት ላይ የነበረ ተጎድቶ ወይም ሞቶ የተገኘ ሰው ስለመኖሩ ሪፖርት የለንም” ብለዋል።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  7. አሜሪካ የኢራንን ቅድመ ሁኔታዎች ከተቀበለች የሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ በሁለት ቀናት ውስጥ ሊከፈት ይችላል- አራግቺ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አሜሪካ በቴህራን የቀረቡትን ቅድመ ሁኔታዎች ከተቀበለች ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው የሆርሙዝ ወሽመጥ በሁለት ቀናት ውስጥ እንደገና ሊከፈት ይችላል አሉ።

    አራግቺ እንደገለፁት፣ ከኳታር አደራዳሪዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች የእቅዱን ማስፈጸሚያ ጊዜ ከአምስት ቀናት ወደ ሁለት ቀናት አሳጥረውታል።

    ሚኒስትሩ አክለውም ቴህራን ከኢዝላማባድ ስምምነት በኋላ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ፣ በቀጠናው የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎች እንዲቀነሱ፣ ለነዳጅ ሽያጭ የተቀመጡ ገደቦች እንደገና እንዲከለሱ እና በኳታር የሚገኙትን ጨምሮ የታገዱ የኢራን ንብረቶች እንዲለቀቁ ትጠይቃለች።

    ኢራን ከኦማን ጋር በተወያየችባቸው የመርከብ መጓጓዣ መስመሮች ላይ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲሰጥላትም ትፈልጋለች።

    አራግቺ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በዋሽንግተንና በቴህራን መካከል በሌሎች እስካሁን ያልተፈቱ ጉዳዮች ላይ አዲስ ድርድር ለመጀመር መንገድ ይከፍታል ብለዋል።

    ይህ ሃሳብ የቀረበው በባሕር ማጓጓዣና በኤነርጂ ገበያዎች ላይ ተጽእኖ ያሳደረውን ውጥረት ለመቀነስ የዲፕሎማሲ ጥረቶች በቀጠሉበት ወቅት ነው። የዓለም የነዳጅ ንግድ አንድ አምስተኛ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ አሁንም ለዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ መተላለፊያ ሆኖ እያገለገለ ነው።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር “በጥሩ ሁኔታ እየሄደ” መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ደግሞ ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት ለማድረስ ገና እንዳልወሰኑ ጠቁመዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት በበኩላቸው አሜሪካ ጥቃት ከፈጸመች የከፋ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ አስጠንቅቀዋል።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  8. ሩሲያ እና ዩክሬን የሳይበር ጥቃት ተፈጸመባቸው

    ሩሲያ እና ዩክሬን የአደጋ ጊዜ ማንቂያ መተግበሪያቸው ላይ ግዙፍ የሳይበር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አስታወቁ።

    የሳይበር ጥቃቱን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል የዲጂታል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ተቀስቅሷል።

    የዩክሬን ባለሥልጣናት ለዜጎቻቸው የጨረር ስጋት መኖሩን የሚገልጽ ሐሰተኛ መልዕክት ከተላከ በኋላ የአየር ጥቃት ማሳወቂያ መተግበሪያቸው የሳይበር ጥቃት እንደደረሰበት ተናግረዋል።

    የዩክሬን አየር ኃይል ወዲያውኑ መልዕክቱ ሐሰተኛ መሆኑን በመግለጽ ምንም ዓይነት የጨረር ስጋት የለም ብሏል።

    አክሎም ዜጎች በአገሪቱ ባለሥልጣናት በይፋ የሚሰጡ መረጃዎች ላይ ብቻ እንዲተማመኑ አሳስቧል።

    ከሰዓታት በኋላ የሩሲያ ድንገተኛ አደጋ ሚኒስቴር የአደጋ ማስጠንቀቂያ መተግበሪያው ላይ “ግዙፍ የሳይበር ጥቃት መፈጸሙን” ገልጾ የመረጃ መንታፊዎች ሐሰተኛ መረጃ እያሰራጩ መሆኑን ገልጿል።

    የአገሪቱ ባለሥልጣናት ለድንገተኛ አደጋ ማስጠንቂያ የሚያገለግሉት ሳይረኖች፣ ቴሌቪዥኖች እና የራዲዮ ስርጭቶች የጥቃቱ ሰላባ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

    የሳይበር ጥቃቱ የተፈጸመው በኬርሶን ግዛት ላይ ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ካበቃ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።

    ዩክሬን ጥቃቱን የፈጸመችው ሩሲያ ናት ስትል የወነጀለች ሲሆን ሞስኮ ግን ለጥቃቱ ተጠያቂ ናቸው ያለቻቸውን አካላት አላሳወቀችም።

    በሁለቱም አገራት ያሉ ባለሥልጣናት ክስተቶቹ የተገናኙ መሆን አለመሆናቸውን እየመረመሩ ነው።

  9. የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች የኢራንን አሳ አጥማጅ መርከብ በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ

    የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች 23 ሰዎችን የጫነች የኢራን አሳ አጥማጅ መርከብ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰማ።

    የሕንድ ውቅያኖስ የባሕር ላይ ደህንንት ማዕከል የባሕር ላይ ወንበዴዎቹ የንግድ መርከቦችን በመጠጋት ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ ሲል አስጠንቅቋል።

    አዚኒ የተባለችው የአሳ አጥማጅ መርከብ የታገተችው ሐሙስ ዕለት መሆኑ ታውቋል።

    መርከቧ በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ በባንዳር ባይላ እና ሀፉን ከተሞች መካከል እየቀዘፈች እንደነበር የፑንትላንድ የባሕር ላይ ፖሊስ እሁድ ዕለት አስታውቋል።

    የፖሊስ ባልደረባው የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እነደተናገረው 12 የባሕር ላይ ወንበዴዎች 21 ኢራናውያንን እና ሁለት ሶማሊያውያን ጸጥታ ባልደረቦችንን ያሳፈረችውን መርከቧን አግተዋል።

    ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ለመስጠት ኃላፊነት እንዳልተሰጠው በመግለጽ ስሙ አንዳይገለጽ የጠየቀው ይህ ግለሰብ የመርከበኞቹ ደህንነት በምን ሁኔታ ላይ እንደሆነ አይታወቅም ብሏል።

    የባሕር ኃይል ደህንነት ማዕከሉ ባወጣው ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ወንበዴዎቹ ያገቱትን መርከብ ተጠቅመው በንግድ መርከቦች ላይ ተጨማሪ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ ብሏል።

    የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል ዘመቻ ጉዳዩን እየመረመረ መሆኑን ገልጾ በአካባቢው የሚገኙ መርከቦች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን እንዲያሳውቁ ጥሪ አቅርቧል።

    ይህ የመርከብ እገታ የተከሰተው በኤደን ባሕረ ሰላጤና በምዕራባዊ ሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ የሶማሊያ ባሕር ወንበዴዎች እንደገና ካንሰራሩ በኋላ ነው።

    ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ይፋ በተደረገ መረጃ መሠረት ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ስድስት የንግድ መርከቦች ታግተዋል።

    ከእነዚህም ጥቃቶች አንዳንዶቹ ከሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በጣም ርቀው በሚገኙ ስፍራዎች የተፈጸሙ ናቸው።

    በመስከረም ወር የፑንትላንድ ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ ወንበዴዎቹ ኤምቲ ኦነር 25 በመባል የምትጠራውን ነዳጅ ጫኝ መርከብ ካገቱ በኋላ የጸጥታ አባላት ከመድረሳቸው በፊት አምስት ባሕረተኞችን ገድለዋል።

    የነዳጅ ጫኝ መርከቡ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በወንበዴዎች እጅ ነበር። ባለሥልጣናት 16 በባሕር ላይ ውንብድና የተጠረጠሩ ግለሰቦች መታሰራቸውን ገልጸዋል።

    ባለፉት አስር ዓመታት ዓለም አቀፍ የባሕር ኃይል ጥበቃዎች እና የባሕር ደህንነት ማሻሻያዎች በሶማሊያ አካባቢ የባሕር ላይ ውንብድናን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰውት ነበር። ነገር ግን በቅርቡ የተፈጸሙት የመርከብ እገታዎች በአገሪቱ ረዥም የባሕር ዳርቻ አካባቢ በሚያልፉ መርከቦች ላይ የደህንነት ስጋት ደቅነዋል።