ቀጥታ , ትራምፕ ፓርቲያቸው በአጋማሽ ዘመን ምርጫ የተሸነፈው በኢራን ጦርነት ምክንያት መሆኑን ተናገሩ

ሪፐብሊካኖች በአጋማሽ ዘመን ምርጫ የተሸነፉት በኢራን ጦርነት ምክንያት እንደሆነ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስም “የተሸነፍነው በጦርነቱ ምክንያት ነው” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዩኬ የባርያ ንግድን በተመለከተ ‘የጊዜ ገደብ ያለው’ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች

    ዩናይትድ ኪንግደም ለባሪያ ንግድ ይቅርታ መጠየቅን በተመለከተ “መዋቅራዊ፣ የጊዜ ገደብ ያለው፣ አካታች እና በቀናነት ላይ የተመሠረተ” ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።

    አትላንቲክ ውቅያኖስን የተሻገው የባሪያ ንግድ ያሳደረውን “ታሪካዊ ጠባሳ” በተመለከተ ዩኬ ለንግግር ዝግጁ መሆኗን ያስታወቀችው ከኮመንዌልዝ አገራት ውይይት በኋላ በወጣ የአቋም መግለጫ ነው።

    በአንቲጓ የኮመንዌልዝ አገራት መሪዎች ውይይት እያደረጉ ነበር።

    በአቋም መግለጫቸው ላይ “ዩኬ ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖች ጋር የአፍሪካውያን የባሪያ ንግር ያሳደረውን ታሪካዊ ጠባሳ በተመለከተ መዋቅራዊ፣ የጊዜ ገደብ ያለው፣ አካታች እና በቀናነት ላይ የተመሠረተ ውይይት ለማድረግ መስማማቷን በበጎ እንቀበለዋለን” ብለዋል።

    የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ ቡርንሃም ይፋዊ ይቅርታ መጠየቅን በተመለከተ የውይይት በሩን ክፍት ማድረጋቸውን ተከትሎ የመጣ ውሳኔ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ መጠየቅን በተመለከተ አወንታዊ አቋም ቢያንጸባርቁም የካሳ ክፍያ እንደማይሰጥ ተናገረዋል።

    የባርያ ንግድን በተመለከተ ውይይት የሚደረግበት የጊዜ ገደብ የሚወሰነው በቀጣይ እንደሆነ እና በአንድ ዓመት ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጸሐፊ ኤድ ሚሊባንድ ተናግረዋል።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  2. ፒዛ ላይ አናናስ አላደርግም ያለው ጣልያናዊ ሼፍ ከሥራ ተባረረ

    ፒዛ ላይ አናናስ መጨመር “ባህሌን ማዋረድ ነው” ያለው ጣልያናዊ ሼፍ ከሥራ ተባረረ።

    ዴቪድ ታምቡሬላ የተባለው ሼፍ ይሠራ የነበረው ላ ኮስታ በተባለ ሬስቶራንት ነበር። ሬስቶራንቱ አሁን ላይ የተዘጋ ሲሆን፤ ሼፉ የተባረረው ያለፈው ግንቦት ላይ ነው።

    ሼፉ የተባረረው የተለያዩ ቅሬታዎች ከቀረቡበት በኋላ ሲሆን፤ ከቅሬታዎቹ አንዱም ፒዛ ላይ አናናስ አላደርግም ማለቱ ነው።

    ከሬስቶራንቱ ኃላፊዎች የሚሰጠው ትዕዛዝ “ከባህል ጋር የሚጻረር” ከሆነ መቀበል እንደማይጠበቅበት ተናግሯል።

    ሼፉ ከወራት በፊት ቢባረርም ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ሥራውን ማጣቱን አሁን ላይ የገለጸው ለአውስትራሊያ የሥራ ኮሚሽን ነው።

    ኮሚሽኑ እንዳለው ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ሦስት ጊዜ ያህል ሼፉ ፒዛ ላይ አናናስ እንደማያደርግ ገልጿል።

    “ፒዛ ላይ አናናስ አለመጨመር ለጣልያናውያን ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ነው” ሲልም ለሬስቶራንቱ ኃላፊዎች ተናግሮ ነበር።

  3. የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ልጅ በቁጥጥር ሥር ዋለ

    የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ልጅ የሆነው ቤላሚን ቻቱንጋ ሙጋቤ በሰዎች ላይ ከደረሰ ጥቃት ጋር በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

    ሁለት ቅንጡ መኪኖች ላይ ከተቃጣ የዝርፊያ ሙከራ ጋር በተያያዘ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ልጅ ጨምሮ አምስት ሰዎች መታሰራቸውን የዚምባብዌ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ተሽከርካሪዎቹ በአገሪቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን መያዛቸው ተዘግቧል።

    የ29 ዓመቱ ቤላሚን፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ከሁለተኛ ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ከወለዷቸው ልጆች የመጨረሻው ነው።

    ለ37 ዓመታት አገሪቱን የመሩት ሙጋቤ በአውሮፓውያኑ 2017 ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ 2019 ላይ በ93 ዓመታቸው መሞታቸው ይታወሳል።

    በሀራሬ በሚገኘው ብሮምፕተን የእግንዶች ማረፊያ ከመኪና ዝርፊያ ጋር በተያያዘ በሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎም ከሁለት ቀናት በፊት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ልጅ ታስሯል።

    ዛሬ ሐሙስ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

  4. በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኢቦላ የተገኘበት እንግሊዛዊ ወደ አገሩ ሊወሰድ ነው

    በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኢቦላ የተገኘበት እንግሊዛዊ ወደ አገሩ እንደሚወሰድ ተገለጸ።

    አሁን ላይ እየተሰራጨ በሚገኘው የኢቦላ ቫይረስ ዝርያ የተያዘ የመጀመሪያው የዩናይትድ ኪንግደም ዜጋ ነው።

    እስካሁን ድረስ ወደ 5,000 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ሕይወታቸው አልፏል።

    ግለሰቡ መቼ ወደ ዩኬ እንደሚጓዝ አልተገለጸም።

    የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ “እንደዚህ ያሉ ኬዞችን በተመለከተ የተዋቀረ አሠራር አለን” ብለዋል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ በቫይረሱ የተያዘው ሰው የሕክምና ባለሙያ ነው። ሮይተርስ በዘገባው የጠቀሰውን ውስጣዊ ሰነድ ቢቢሲ አልተመለከተም።

    በዩኬ በኢቦላ የተያዙ ሰዎች እምብዛም የሌሉ ሲሆን በቫይረሱ የሞተም ሰው የለም።

    በአውሮፓውያኑ 1976 አራት የአገሪቱ ዜጎች በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጿል። ይህም በቤተ ሙከራ ከነበረ ንክኪ ጋር በተያያዘ ነው።

    ከ2014 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ ሦስት በምዕራብ አፍሪካ ይሠሩ የነበሩ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘው ነበር።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  5. ትራምፕ ፓርቲያቸው በአጋማሽ ዘመን ምርጫ የተሸነፈው በኢራን ጦርነት ምክንያት መሆኑን ተናገሩ

    ሪፐብሊካኖች በአጋማሽ ዘመን ምርጫ የተሸነፉት በኢራን ጦርነት ምክንያት እንደሆነ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስም “የተሸነፍነው በጦርነቱ ምክንያት ነው” ብለዋል።

    ዴሞክራቶች፤ በሪፐብሊካኖች በአብላጫ ተይዘው የነበሩትን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን እንዲሁም ሴኔቱንም አሸንፈዋል።

    የምርጫው ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በታች ወርዷል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ “የተሸነፍነው በጦርነቱ ምክንያት ነው፤ ፕሬዝዳንቱም ይሄንን ተናግረዋል” ብለዋል።

    በአውሮፓውያኑ 2024 ለትራምፕ ድምጻቸውን የሰጡ መራጮች አሁን ላይ ሪፐብሊካኖች ላይ ፊታቸውን ማዞራቸውን ገልጸዋል።

    ጄዲ ቫንስ ከአጋማሽ ዘመን ምርጫው ውጤት ጋር በተያያዘ የሰጡት አስተያየት ራሳቸውን ከትራምፕ ለማራቅ እየሞከሩ እንደሆነ ያሳያል ተብሏል። ለዚህም ምክንያቱ በ2028 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊወዳደሩ የሚችሉበት ዕድል መኖሩ ነው።

    ዴሞክራቶች በምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኙበት ምክንያት የኢራን ጦርነት መሆኑን ትራምፕም አምነዋል።

    ትራምፕ ፓርቲያቸው በምርጫው ለመሸነፉ “ከፍተኛ” ድርሻ የነበረው ጦርነቱ መሆኑን ቢገልጹም፤ በድጋሚ ነገሮችን የማከናወን ዕድል ቢሰጣቸው “መልሰው እንደሚፈጽሙት” ተናግረዋል።

    ጄዲ ቫንስ ለሽንፈቱ ጦርነቱን ምክንያት ማድረጋቸውን በተመለከተ የተጠየቁት ትራምፕ ከምክትል ፕሬዝዳንቱ ጋር እንደሚስማሙ ተናግረዋል።

    ሆኖም ግን ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግ መቻላቸውን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

  6. የጥቅምት 26/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የጥቅምት 26/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። እንድትከታተሉን በአክብሮት እንጋብዛለን።

  7. ሪፐብሊካኖች ለሽንፈታቸው ትራምፕን ተጠያቂ አደረጉ

    ሪፐብሊካኖች ለሽንፈታቸው ተጠያቂው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደሆኑ እየገለጹ ነው።

    የሪፐብሊካን ወትዋች (ሎቢይስት) ቢል ሚለር “ተጠያቂው እሳቸው ናቸው፤ ሌላ ማንም አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    የአጋማሽ ዘመን ምርጫው ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ሪፐብሊካኖች ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።

    ሚለር “በጣም አስከፊ ነገር ነው። ማንም ይሄ ይሆናል ብሎ አልጠበቀም” ብለዋል።

    ትናንት ምሽት የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫው ውጤት መውጣት ሲጀምር በፓርቲው ውስጥ መደናገጥ ተፈጥሯል። ከዚያም ድንጋጤው በትራምፕ ወደ መናደድ ዞሯል።

    አብዛኞቹ ሪፐብሊካኖች ለሽንፈታቸው ተጠያቂ ያደረጉት ፕሬዝዳንቱን ነው።

    እንደ ቴክሳስ፣ ካንዛስ እና ሳውዝ ካሮላይና ባሉ የሪፐብሊካን ደጋፊ የሆኑ ግዛቶች ጭምር ዴሞክራቶች አሸንፈዋል።

    ትራምፕ መራጮች ቅድሚያ ለሚሰጧቸው ጉዳዮች ጆሮ መንፈጋቸው እና ዋነኛ ትኩረታቸው “ሌጋሲያቸው” ላይ መሆኑ ፓርቲውን ዋጋ አስከፍሎታል ብለዋል።

    በሚኒሶታ የሪፐብሊካን ስትራቴጂ ነዳፊ ግሬግ ፔፒን “በስህተት ላይ ስህተት እየተሠራ ነበር። በየግዛቱ በግልጽ የታየው ዜጎች ትራምፕን እንደጠሉ ነው” ብለዋል።

    የትራምፕ ደጋፊ የሆኑ የዋይት ሀውስ ሠራተኛ በትራምፕ “ክፉኛ መበሳጨታቸውን” ተናግረዋል።

    ዋነኛ ያሏቸው ምክንያቶች የኢራን ጦርነት፣ በአገራት ላይ ታሪፍ መጣል እና ስደተኞች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች ናቸው።

  8. ኢራን በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ምን ሚና ነበራት?

    ኢራን በአሜሪካ ምርጫ ጉልህ ሚና አላት።

    የዛሬ 47 ዓመት በዚሁ ቀን የኢራን ተማሪዎች በቴህራን የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ተቆጣጥረው የዋሽንግተን ዲፕሎማቶችን አገቱ።

    444 ቀናት የወሰደው ቀውስ በአውሮፓውያኑ 1980 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጂሚ ካርተር፣ በሮናልድ ሬገን እንዲሸነፉ ምክንያት ሆኗል።

    የአሜሪካ እና ኢራን ጦርነትን ተከትሎ የመጣው የነዳጅ ዋጋ መናር እና የኑሮ ውድነት ሪፐብሊካኖች በአጋማሽ ዘመን ምርጫው እንዲሸነፉ ምክንያት ሆነዋል።

    ዴሞክራቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በሴኔቱም አብላጫ ድምጽ አግኝተዋል።

    ለኢራን መንግሥት ቅርብ የሆኑ ተንታኞች በሰጡት ትንታኔ፤ ቴህራን ከዋሽንግተን ጋር የሚደረገውን ድርድር ማዘግየቷን ገልጸዋል።

    በነዳጅ አቅርቦት ላይ ጫና በማሳደር የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

    ለዚህ ምክንያቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን በፖለቲካ ማዳከም እና ሪፐብሊካኖች በምርጫው አብላጫ ድምጽ እንዳያገኙ ማድረግ ነው።

    ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ኢራን ታግተው የነበሩ አሜሪካውያን ዲፕሎማቶችን የለቀቀችው ሬጋን ቃለ መሐላ በፈጸሙ በደቂቃዎች ውስጥ ነበር።

    በዘንድሮው ምርጫ ዴሞክራቶች የሚቆጣጠሩት ኮንግረስ የትራምፕን እርምጃዎች ይገድባል ብላ ቴህራን ተስፋ ታደርጋለች።

    ትራምፕ በኢራን ላይ በቀጣይ ወታደራዊ እርምጃ እንዳይወስዱ ማስቻል ዋነኛው ግብ ነው።

    ኮንግረሱ ትራምፕ የሚጠይቁትን ገንዘብ መገደብ እንዲሁም ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔዎቻቸው ላይ ጥያቄ ማንሳት ይችላል።

    ሆኖም ግን ትራምፕ ወታዳራዊ እርምጃ በመውሰድ እና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ረገድ የበላይ ውሳኔ ሰጭ መሆናቸው አይለወጥም።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  9. በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዴሞክራቶች በማሸነፋቸው የዓለም መሪዎች ምን አሉ?

    በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዴሞክራቶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን አሸንፈዋል።

    በሴኔቱ ላይም አብላጫ ድምጽ እንደሚያገኙ ተተንብዩዋል። ይህንን ተከትሎ አንዳንድ የዓለም መሪዎች የምርጫውን ውጤት በደስታ የተቀበሉ ሲሆን የትራምፕ አስተዳደር ላይ ያነጣጠረ አስተያየት ሰጥተዋል።

    • የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ- አሜሪካውያን ጥላቻን፣ የአየር ንብረት ለውጥ ክህደትን እና ልዩ ተጠቃሚነትን በድምጻቸው ተቃውመዋል ብለዋል።
    • የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ስቶር- ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት ስላልተሰጣቸው ኖርዌይን በጥብቅ ሲተቹ ከቆዩ በኋላ አሁን ከኦስሎ መርሆዎች ጋር አብረው የሚሄዱ ድምጾች ከአሜሪካ መውጣት ጀምረዋል ሲሉ ገልጸዋል።
    • የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ- በነጭ ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት ፈፅማለች በሚል በሪፐብሊካኑ ትራምፕ የተከሰሰችው እና ከአሜሪካ ጋር ግንኙነቷ የሻከረው ደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ምርጫው ለዓለም አቀፍ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ብለዋል።
    • የአውሮፓ ፓርላማ ምክትል ፕሬዚዳንት ክሪስቴል ሻልዴሞሴ- የምርጫው ውጤት ዩክሬን የበለጠ ድጋፍ እንድታገኝ ሊያግዝ እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
  10. የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ አሜሪካውያን “ጦርነት አንፈልግም” ሲሉ ድምጻቸውን ሰጥተዋል አሉ

    የኢራን ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ሞሐመድ ባጋር የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲ በአጋማሽ ዘመን ምርጫ ከባድ ሽንፈት ካጋጠመው በኋላ አሜሪካውያን “ለጦርነት እምቢ ብለዋል” ሲሉ ተናገሩ።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሃመድ ባገር ጋሊባፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ “ይህንን መልዕክት እንደግፋለን” ሲሉም ጽፈዋል።

    “የአሜሪካ መንግሥት የሕዝቡን ፍላጎት በመክዳት ለዓለም አቀፍ ጥቅም ፈላጊዎችና ለጫና ፈጣሪዎች ካገለገለ፣ የእኛ እምቢታ ከአስፈሪ ውጤት ጋር እንደሚመጣ ይረዳል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

    ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ሪፐብሊካን በአጋማሽ ዘመን ምርጫው ያገኘው ጥቂት ድምጽ በከፊል ከጦርነቱ እና ከዚያ ጋር ተያይዞ ከፍ ካለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር የተያያዘ መሆኑን አምነዋል።

    ሆኖም ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ከእስራኤል ጋር በመተባበር በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም በወሰዱትን ውሳኔ እንደማይጸጸቱ ገልጸዋል።

    ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ “በምርጫው ውጤት ውስጥ የኢራን ጉዳይ አንዱ ምክንያት ነበር ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

    “ሰዎች በኢራን ጉዳይ እየወሰድኩ ያለሁትን እርምጃ ይደግፋሉ፤ ነገር ግን ለአጭር ጊዜ ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ መክፈል የሚያስከትለውን ውጤት ለመሸከም ፈቃደኛ አልነበሩም፤ ይህንን እረዳለሁ” ሲሉ አክለዋል።

    ትራምፕ ለሲቢኤስ ኒውስ በሰጡት ሌላ ቃለ ምልልስ፣ “ግጭቱ የሚያበቃው እኔ ያበቃል ስል ነው” ብለዋል።

    ባለፉት ሳምንታት ትራምፕ ግጭቱን ለማስቆም ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ መደረስ ካልተቻለ፣ ከአጋማሽ ዘመን ምርጫው በኋላ አሜሪካና እስራኤል ወደ ሙሉ ውጊያ ሊመለሱ እንደሚችሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

    በተጨማሪም፣ ረቡዕ ዕለት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በሆርሙዝ ወሽመጥ ውስጥ በተቀበሩ የባህር ውስጥ ፈንጂዎች አራት የነዳጅ ማመላለሻ መርከቦች በእሳት መያያዛቸውን ገልጿል።

    ታስኒም የዜና ወኪል ከአራቱ መርከቦች ሁለቱ አሁንም በእሳት እየነደዱ መሆናቸውን እና ሌሎች ሁለት መርከቦችን መመታታቸውን ዘግቧል። መርከቦቹ በሆርሙዝ ወሽመጥ ውስጥ እንዳይጠቀሙበት በተከለከለው ደቡባዊ የባህር መስመር ለማለፍ እየሞከሩ እንደነበር ገልጿል።

    ቢቢሲ የአብዮታዊ ዘቡን ክሶች በገለልተኛ መንገድ አላረጋገጠም።

  11. ሂውማን ራይት ዎች የሪፖርተር ጋዜጣ መታገድ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚፈጸመው “ጥቃት አካል ነው” ሲል ተቃወመ

    ዓለም አቀፉ ሰብአዊ መብቶች ተቋም ‘ሂውማን ራይትስ ዎች’ ሪፖርተር ጋዜጣ መታገድ የኢትዮጵያ መንግሥት “በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እና ሲቪል ምኅዳር ላይ እያካሄደ ያለው ጥቃት አካል ነው” ሲል ወቀሰ።

    መንግሥት በመገናኛ ብዙኃን ላይ እየተከተለ ያለውን አካሄድ “በአፋጣኝ እንዲቀለብስ” ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአገሪቱ አጋራት መንግሥትን እንዲወተውቱም ጥሪ አቅርቧል።

    ሂውማን ራይትስ ዎች ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “አገሪቱ ውስጥ ከቀሩት ጥቂት ገለልተኛ ተቋማት አንዱ” ሲል በገለጸው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የተወሰደውን እርምጃ ተቃውሟል።

    የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሰኞ ዕለት አንጋፋውን ሪፖርተር እና እንግሊዘኛውን ‘ዘ ሪፖርተር’ ጋዜጦች የሚያሳትመው ‘የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር’ የምዝገባ ምስክር ወረቀት “ላልተወሰነ ጊዜ” መታገዱን አስታውቋል። በዚህም የተነሳ በተቋሙ ሥር የሚታተሙት ጋዜጦች “ህትመት እና ከስርጭት ሙሉ በሙሉ ታግዶ እንዲቆይ” መወሰኑን ገልጿል።

    ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ይህንን እርምጃ ከወሰደባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ ጋዜጣዎቹ “የአገር ገጽታን የሚያጠለሹ፣ የአገርን ብሄራዊ ደህንነትን የሚጎዱ፣ የሕዝቦችን አብሮነትና እሴት የሚሸረሽሩ መረጃዎች” በማሰራጨታቸው እንደሆነ ገልጿል።

    ሪፖርተር “ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጻረሩ ይዘቶችን” አሰራጭቷል በሚል የከሰሰው ባለሥልጣኑ፣ የሚወጡት ዘገባዎች፣ “የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ዲፕሎማሲ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ” እንደሆኑም በመግለጫው ጠቅሷል።

    ሰብአዊ መብቶች ተቋሙ ሂውማን ራይትስ ዎች በዛሬው መግለጫው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት “የትኛውንም ተቺ ዘገባ ለማፈን ግልጽ ያልሆኑ ‘ብሔራዊ ጥቅም’ የሚሉ ክሶችን የሚጠቀምበት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ይጠቁማል” ሲል እርምጃውን ተቃውሟል።

    “ይህ እርምጃ መንግሥት በመገናኛ ብዙኃን እና በሲቪክ ምኅዳሩ ላይ እያካሄደ ያለው እየቀጠለ ያለ ጥቃት አካል” እንደሆነም ገልጿል።

    የመገናኛ ብዙኃን መታገድ “አዲሱ የተለመደ ነገር” ሲል ገለጸው ተቋሙ፣ ባለፈው ዓመት የአዲስ ስታንዳርድ እና ዋዜማ ፈቃዶች መሰረዛቸውን እንዲሁም የውጭ መገናኛ ብዙኃን የዘገባ ፈቃድ መሰረዙን አስታውሷል።

    ሂውማን ራይትስ ዎች አክሎም፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት ለማስጠንቀቂያው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፤ የአገሪቱ አጋር አካላትም መንግሥት አካሄዱን በአፋጣኝ እንዲቀለብስ ግፊት ሊያደርጉ ይገባል” ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

  12. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለ ሪፐብሊካኖች ሽንፈት እስካሁን ምን አሉ?

    የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ውጤት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደፈለጉት አልሆነም።

    ዴሞክራቶች ሴኔቱን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን በማሸነፍ የኮንግረሱን የላይኛው እና የታችኛው ምክር ቤቶችን ተቆጣጥረዋል። ይህ ድል ቀሪውን የትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ዘመን አካሄድ የሚወስን እንደሚሆን ይጠበቃል።

    ፕሬዝዳንቱ ለዚህ ውጤት የተለያዩ ምላሾችን ሰጥተዋል።

    የኢራን ጦርነት እና የነዳጅ ዋጋ

    • ትራምፕ የኢራን ጦርነት እና በከፍተኛ መጠን የናረው የነዳጅ ዋጋ ዲሞክራቶች በአጋማሽ ዘመን ምርጫ ለገጠማቸው ሽንፈት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አምነዋል።
    • የነዳጅ ዋጋ መጨመር በሪፐብሊካን ፓርቲ ላይ ጉዳት ማድረሱን ለፎክስ ኒውስ የተናገሩት ትራምፕ፣ ሕዝቡ ለነዳጅ ተጨማሪ ገንዘብ ለመክፈል መገደዱን “እንዳልወደደው” ገልጸዋል። ከምርጫው በፊት የተደረገ የሕዝብ አስተያየት ጥናት በመራጮች ዘንድ ቀዳሚ አጀንዳ የሆነው የኢኮኖሚው ጉዳይ እንደሆነ አሳይቷል።
    • ለትራምፕ ከኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ደግሞ፣ የምርጫውን ውጤት ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። አሜሪካ በኢራን ጦርነት ውስጥ የነበራትን ተሳትፎ ግን “እጅግ ብልህ ውሳኔ” ሲሉ ገልጸውታል።

    ‘እኔ ለምርጫ አልቀረብኩም’

    • ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እና ለመገናኛ ብዙኃን በሰጧቸው ቃለ መጠይቆች፣ ስማቸው በድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ ቢኖር ኖሮ ሪፐብሊካኖች ያሸንፉ እንደነበር በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
    • “ምርጫው ላይ እኔ አልነበርኩም፤ በእጩነት ስላልነበርኩ፣ በቂ ሰዎች ወጥተው ድምፅ እንዲሰጡ ማድረግ አልቻልንም” ሲሉ ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።

    ‘ዴሞክራቶች ጥሩ ስራ ሰርተዋል’

    • የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከፎከስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ዴሞክራቶች “ጥሩ እንደሰሩ” አምነዋል። ሪፐብሊካኖች “ግዙፍ የቅስቀሳ ሰልፎችን” ካደረጉም በኋላ በተመዘገበው ውጤቱ “ትንሽ እንደተደነቁ” አክለዋል።
    • ዴሞክራቶች ኮንግረስን መቆጣጠራቸው የትራምፕን እቅዶች የሚያሰናክል ቢሆንም፣ ፕሬዝዳንቱ ግን ከዴሞክራቶች ጋር አብረው ለመስራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
    • ትራምፕ፣ ከዴሞክራቶች ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችሉ “እጅግ በርካታ ነገሮች” መኖራቸውን ለፎክስ ኒውስ ቢገልጹም፣ ለዎል ስትሪት ጆርናል በሰጡት አስተያየት ግን አስፈላጊ ሆኖ ካገኙት “ድምፅ በድምፅ የመሻር (ቬቶ) ሥልጣናቸውን” እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል።
  13. በኒውዮርክ ማራቶን ላይ በመሮጥ ላይ የነበረች ወጣት ራሷን ስታ ሕይወቷ አለፈ

    የ24 ዓመቷ የኒውዮርክ ማራቶን ተወዳዳሪ ሬቸል አፓ፣ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 3 ኪሎ ሜትር ብቻ ሲቀራት ራሷን ስታ ሕይወቷ አለፈ።

    አባቷ ስቲቭ አፓ እንደተናገሩት ልጃቸው “ፍጹም ጤናማ እና በጥሩ የአካል ብቃት ሁኔታ” ላይ ነበረች።

    ከፔንስልቬኒያ ግዛት ሌዊስቤሪ የመጣችው ሬቸል አፓ በፓርኪንሰን በሽታ ለተጠቃው አያቷ ክብር ለመስጠትና ገንዘብ ለማሰባሰብ ከፓርኪንሰን ፋውንዴሽን ሻምፒዮንስ ቡድን ጋር እየሮጠች ነበር።

    ሬቸልአፓ ማራቶን ስትሮጥ የመጀመሪያዋ ቢሆንም፣ ስፖርተኛ እንደነበረች እና ለወራት ለዚሁ ውድድር በትጋት መዘጋጀቷን አባቷ ለኒውዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።

    አባቷ ጨምረውም እምብዛም ባልተለመደው ራብዶማዮላይሲስ (Rhabdomyolysis) የተባለ ሕመም መጠቃቷን እና መሞቷን ተናግረዋል።

    የኒውዮርክ ፖሊስ አፓ ወድቃ ከተገኘች በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስዳ በዚያው ምሽት ሕይወቷ ማለፉን ገልጿል።

  14. የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አሜሪካውያን "ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል" አሉ

    የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲው ያስመዘገበው ሰፊ የምርጫ ድል አሜሪካውያን ለውጥ እንደሚፈልጉ የሚያሳይ ማስረጃ ነው አሉ።

    ኦባማ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልዕክት፣ “ዛሬ ማታ የአሜሪካ ሕዝብ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል፤ ሰዎችን ከመከፋፈል ይልቅ የሚያቀራርብ ፖለቲካ፣ እንዲሁም የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ተጨባጭ መፍትሄዎችን የሚያቀርቡ መሪዎችን እንደሚፈልግ አሳይቷል” ብለዋል።

    ኦባማ በሚሺጋን እና በጆርጂያ ከበርካታ የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩዎች ጋር በመሆን የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ አካሄደዋል።

    በተጨማሪም “አሁን የእኛ ተግባር መሆን ያለበት እጃችንን ጠቅልለን ሥልጣን ባለን ቦታ ሁሉ አስፈላጊ ለውጦችን ማድረግ፣ ተጨማሪ ጉዳትን መከላከል እና ለወደፊቱ መሠረት መጣል ነው” ሲሉ አክለዋል።

  15. ዴሞክራቶች ከ38 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴክሳስ የሴኔት ወንበር አሸነፉ

    ዴሞክራቱ ጄምስ ታላሪኮ በቴክሳስ የሴኔት ተወካይነት ምርጫን በማሸነፍ፣ ከአውሮፓውያኑ 1988 ወዲህ ግዛቷን የወክሉ ዴሞክራት የሴኔት አባል ሆኑ።

    በዘንድሮው አሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫበወሳኟ ቴክሳስ ግዛት በተደረገው ውድድር ዴሞክራቶች ትልቅ ሽንፈት አጋጥሟቸዋል።

    ታላሪኮ በሪፐብሊካኑ ኬን ፓክስተን ላይ የተቀናጁት አስደናቂ ድል፣ ከአውሮፓውያኑ 1988 ወዲህ ዴሞክራት በቴክሳስ የአሜሪካ የሴኔት መቀመጫን ያሸነፈበት የመጀመሪያው ክስተት ሆኗል።

    በቴክሳስ የተመዘገበው ድል ዴሞክራቶች በመላው አሜሪካ ኮንግረስ ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠሩ ላስቻለቸው ግስጋሴ አስተዋጾ አድርጓል።

    የትምህርት ቤት መምህር የነበሩት ታላሪኮ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ እምብዛም አይታወቁም ነበር። በምርጫ ቅስቀሳቸው ማዕከላዊ አጀንዳ ያደረጉት በሪፐብሊካን አመራር ስር የተባባሰውን የኑሮ ውድነት ነው።

    ተቀናቃኛቸው ፓክስተን በአንጻሩ የታላሪኮ ምልከታ ለቴክሳስ ግዛት “እጅግ ተራማጅ” (too progressive) እንደሆኑ በመግለጽ ተከራክረዋል። በበርካታ መድረኮችም ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጎን ቆመው ቅስቀሳ አድርገዋል።

    የቴክሳስ ዋና ከተማ ኦስቲን ውስጥ በተዘጋጀው የምርጫ ውጤት ድግስ ላይ በቴሌቪዥን ታላሪኮ አሸናፊ መሆናቸው ሲገለጽ ደጋፊዎቹ በደስታ ፈንጥዘዋል።

    በብዝዎች እውን ይሆናል ተብሎ ያልተገመተውን ውጤት ያገኙት ደጋፊዎች፣ ሲሳሳሙ እንዲሁም ሲጠጡ ታይተዋል።

    በቴአትር አዳራሽ ውስጥ በተካሄደው የድል ድግስ ላይ በከፍተኛ ጭብጨባ ታጅበው ንግግር ያደረጉት ታላሪኮ፤ “ቴክሳስን አስመልሰናል” በማለት አሸናፊነታቸውን አውጀዋል።

    በዓለም አንደኛ ሀብታም ከሆነው ኤሎን መስክ ድጋፍ ሲያገኙ የነበሩት ተቀናቃኛቸው ፓክስተንን ያሸነፉት ታላሪኮ አክለውም፣ “በዓለም ላይ ያለ ገንዘብ በሙሉ የቴክሳስ ሕዝብ ዋጋ እንዳልሆነ አረጋግጠናል” ብለዋል።

  16. ትራምፕ የኢራን ጦርነት በአጋማሽ ዘመን ምርጫ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አመኑ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤል ጋር በመሆን ባለፈው ዓመት የካቲት ላይ የከፈቱት ኢራን ጦርነት ዛሬ ረቡዕ እየተካሄደ ባለው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ላይ ሚና መጫወቱት አመኑ።

    ፕሬዝዳንቱ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ አሜሪካ በተወሰኑ የኢራን አካባቢዎች ጥቃት ለመፈጸም እያቀደች ነው በሚል ስለወጡት ዘገባዎች አስተያየት ሰጥተዋል።

    “አንዳች ትልቅ ነገር ማድረግ አለብን” ሲሉ የተደመጡት ትራምፕ፣ ይህ እርምጃ “ከባድ ድብዳብን” ሊያካትት እንደሚችል ጠቁመዋል።

    ኢራናውያን “መቼም ቢሆን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አይኖራቸውም” ሲሉም ተናግረዋል።

    አክለው ደግሞ፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረው የነዳጅ ዋጋ ንረት በአጋማሽ ዘመን የምርጫ ውድድር ላይ በሪፐብሊካኖች ላይ ጉዳት ማድረሱን አምነዋል። ሰዎች ለነዳጅ ተጨማሪ ገንዘብ ለመክፈል መገደዳቸውን “አልወደዱትም” ብለዋል።

    እስካሁን ያለው የውጤት ትንበያ የፕሬዝዳንቱ ሪፐብሊካን ፓርቲ በኮንግረስ ሁለቱም ምክር ቤቶች ውስጥ ያለውን የበላይነት እንደሚያጣ ያሳያል። ትራምፕ ግን የምርጫውን ውጤት በፕሬዝዳንትነታቸው ላይ እንደተሰነዘረ “ምት” አድርገው እንደማይመለከቱት ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።

    ዴሞክራቶች እንዲህ ዓይነት ትልቅ ድል ለማግኘት “ለበርካታ ዓመታት ሲፈልጉ” እንደነበር የጠቀሱት ትራምፕ፤ “በመጨረሻም” እንዳሳኩት ጠቅሰዋል። ላከናወኑት “ጥሩ ሥራ” የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል።

  17. ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሜላት ኪሮስ በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ አሸነፈች

    ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሜላት ኪሮስ በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በማሸነፍ ታሪክ ሰራች።

    በዚህም ሜላት የኮሎራዶ ዲስትሪክት 1ን ተወካይ ሆና ለመመረጥ በቅታለች።

    ሜላት በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት እና ጄንዚ ሆናለች። በከፍተኛ የድምጽ ልዩነት ማሸነፍ የቻለችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የተነሳችለትን ዓላማ ከማስፈጸም በተጨማሪ ከታላላቆቿ ለመማር ዝግጁ መሆኗን ካሸነፈች በኋላ ባደረገችው ንግግር ገልጻለች።

    በጥር ወር ቃለ መሃላ በመፈጸም ስራዋን እንደምትጀምር ይጠበቃል። ለእጩነት በተደረገው ውድድር ሜላት ከ30 ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ ቆዩትን ዲያና ድጌትን ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

    የ29 ዓመቷ ሜላት በህጻንነቷ ነበር ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ያቀናችው።

    ሶሻል ዲሞክራቷ ሜላት እስራኤል በጋዛ የዘር ፍጅት ፈጽማለች በማለቷ አነጋጋሪ ሆናለች። ሜላት ከዕውቁ ዴሞክራት በርኒ ሳንደርስ ድጋፍ አግኝታለች።

    ሕክምና ለሁሉም፤ ቅድሚያ ለቤት፣ የህጻናት እና አረጋዊያን እንክብካቤ፤ የስደተኞች የሚያሳድደው መሥሪያ ቤት መዝጋትን እና የጦር መሣሪያ ሽያጭ ዕገዳን ቅድሚያ እንደምትሰጥ በምርጫ ቅስቀሳዋ ወቅት ደጋግማ ገልጻለች።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  18. በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዲሞክራቶች እየቀናቸው ነው

    በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዲሞክራቶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን ሲያሸንፉ ሴኔቱ ላይም አብላጫ ድምጽ እንደሚያገኙ ተተነበየ።

    ዲሞክራቶች በተወዳደሩባቸው እና ሪፐብሊካንን በመደገፍ በሚታወቁት ግዛቶች ከፍተኛ ድምጽ ማግኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ይህም ለዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ትልቅ እንቅፋት ነው ተብሏል።

    በዚህ ምርጫ 435 የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች እና 35 የሴኔት መቀመጫዎች ድምጽ ተሰጥቶባቸዋል። እንዲሁም በርካታ የግዛት አስተዳዳሪዎች ምርጫዎች ተካሂደዋል።

    ፓርቲው በሪፐብሊካን ቁጥጥር ሥር በነበሩት በቴክሳስ፣ ሳውዝ ካሮላይና እና ኦሃዮ አብላጫ ድምጽ በማግኘት ማሸነፉ ተገልጿል።

    በቴክሳስ፣ ዴሞክራቱ ጄምስ ታላሪኮ ሪፐብሊካኑን ኬን ፓክስተንን ሲያሸንፉ፤ በደቡብ ካሮላይና አኒ ኤንድሪውስ አሸንፈዋል፤ በኦሃዮ ደግሞ ሼሮድ ብራውን ድል በማድረግ ወደ ሴኔት ተመልሰዋል።

    እንደ ሰሜን ካሮላይና እና ጆርጂያ ባሉ ወሳኝ የምርጫ አካባቢዎች፣ የመጀመሪያ ውጤቶች ዲሞክራቶች እየመሩ መሆናቸውን በማሳየታቸው፣ ፓርቲው በሴኔቱ ውስጥ አብላጫ ድምፅ ለማግኘት የሚያስችል አቅጣጫ ላይ መሆኑን አሳይቷል።

    በርካታ የዜና ተቋማት በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ዴሞክራቶች በቂ መቀመጫዎችን በማሸነፍ ምክር ቤቱን ከሪፐብሊካኖች እጅ መልሰው እንደሚቆጣጠሩት ትንበያ ሰጥተዋል።

    ይህ ውጤት ዴሞክራቶች ብዙውን የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የሕግ ማስፈጸሚያ አጀንዳዎች እንዲያግዱ እና በቀሪዎቹ ሁለት ዓመታት በአስተዳደራቸው ላይ የኮንግረስ ቁጥጥርና ክትትል እንዲያጠናከሩ ያስችላቸዋል።

    ተንታኞች የዴሞክራቶችን ድል በዋናነት ከኢኮኖሚ፣ ከከፍተኛ የኑሮ ውድነት እና ከውጭ ፖሊሲዎች ጋር በተያያዘ በመራጮች ዘንድ የተፈጠረ ቅሬታ የመጣ መሆኑን ያስረዳሉ።

    ውጤቱ ለዴሞክራቲክ ፓርቲ በቅርብ ዓመታት ከታዩት የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ስኬቶች የተለየው ነው።

    ይህ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ውጤት በዋሽንግተን ያለውን የፖለቲካ ምህዳር በከፍተኛ ደረጃ ሊቀይር እንደሚችል ተገልጿል።

  19. የሊቢያ ከፍተኛ የሃይማኖት ባለሥልጣን የናይኪ ምርቶች እንዳይለበሱ ወሰነ

    በሊቢያ ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥልጣን ያለው ‘ዳር አል ኢፍታ’፣ ሙስሊሞች የናይኪ አርማን የያዙ ልብሶችን እንዳይገዙ፣ እንዳይሸጡ ወይም እንዳይለብሱ የሚከለክል ውሳኔ አስተላለፈ።

    በትሪፖሊ የሚገኘው ይህ ተቋም ክልከላውን የጣለው፣ ግዙፉ የአሜሪካ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ የተሰየመው በግሪካውያን የድል አምላክ ስም በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል።

    በናይኪ አርማ ላይ የሚገኘው የ’ራይት’ (ስዉሽ) ምልክት የተሰራው ከአምላኳ ክንፎች በመነሳት እንደሆነም አክሏል።

    አርማውን የያዙ አልባሳትን መልበስ ‘ሽርክ’ ወይም ከፈጣሪ ውጪ ሌላ አካልን ከማምለክ ጋር የተያያዘ ነገርን እንደማስተዋወቅ ይቆጠራል ሲል ሞግቷል።

    ሊቢያ የጥንታዊቷ የግሪክ ‘ሳይሬን’ ከተማ መገኛ ነች፤ በከተማዋ ከሚገኙ አርኪዮሎጂካል ግኝቶች መካከል በዚሁ ስም የሚጠራው የግሪክ አማልክት ሃውልት ይገኝበታል።

    በተጨማሪም የሃይማኖት ኮሚቴው፣ ናይኪ እስራኤልን ይደግፋል የሚል ክስ አቅርቧል። አማኞች እስራኤልን የሚደግፉ ኩባንያዎች ምርቶች እንዳይጠቀሙ ጥሪ አቅርቧል።

    ‘ፈትዋ’ በሚል የሚታወቀው ይህ አይነቱ ውሳኔ፣ በእስልምና የሕግ ጉዳዮች ላይ የሚሰጥ የሃይማኖታዊ አስተያየት ነው። ውሳኔው በሊቢያው ታላቁ ሙፍቲ ሳዲቅ አል ጋሪያኒ ጸድቋል።

    ውሳኔውን ያሳለፈው ‘ዳር አል ኢፍታ’ በምዕራብ ሊቢያ ትሪፖሊ ውስጥ የሚገኝ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሃይማኖት ተቋም ነው።

    የዚህ ተቋም የሃይማኖታዊ ውሳኔዎች ቀልል የማይባል ማኅበራዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ቢሆኑም፣ የመንግሥት ትዕዛዝ ወይም በሕግ ተፈጻሚ የሚደረግ ውሳኔ አይደሉም።

  20. ስፔናዊው እግር ኳስ ተጫዋች ሜዳ ላይ በተፈጠረ ግጭት ሕይወቱ አለፈ

    ቴኔሪፌ የተባለው የስፔን እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች የሆነው የ30 ዓመቱ ሄሱስ ዴ ሚጌል ሁለተኛ ዲቪዚዮን ጨዋታ ላይ ባጋጠመው ከባድ ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ አለፈ።

    አጥቂው ዴ ሚጌል ሰኞ ዕለት ከኤፍሲ አንዶራ ጋር በተደረገ ጨዋታ ላይ ከተቃራኒው ቡድን ተጫዋች ጋር በተፈጠረ ኃይለኛ ግጭት የተነሳ ጭንቅላት እና ደረቱ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።

    የተቃራኒ ቡድኑ ግብ ጠባቂ ሄሱስ ኦዎኖ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

    ሰኞ ዕለት ከጨዋታው በኋላ ዴ ሚጌል “የተረጋጋ ነገር ግን አሳሳቢ” ሁኔታ ላይ እንዳለ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ማክሰኞ ጠዋት ሁኔታው እንደተባባሰ ተገልጿል። ኋላ ላይም ሕይወቱ አልፏል።

    የተጨዋቹ ክለቡ ባወጣው መግለጫ “ልባችን ተሰብሮ፣ ቃላትን አጥተን እና እውነት ለመሆኑን ለማመን እየተቸገርን፣ ሄሱስ ዴ ሚጌል አላሜዳን በአሳዛኝ ሁኔታ መሞቱን እንገልጻለን” ብሏል።

    አደጋው የተፈጠረው 2 ለ 2 አቻ የነበሩት ቴኔሪፌ እና አንዶራ በጭማሪ ሰዓት እየተጫወቱ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ነው።

    ግብ ጠባቂው ኦዎኖ ከረጅም ርቀት የመጣውን ኳስ ለመመለስ ወደ ሜዳው አጋማሽ በሚሮጥበት ወቅት ከዴ ሚጌል ጋር በኃይለኛው ተጋጭቷል።

    ዴ ሚጌል ወደ ሜዳው የገቡት የህክምና ባለሙያዎች እርዳታ በሚያደርጉበት ወቅትም ራሱን ስቶ ነበር። ኋላም በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

    አደጋው የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾችን ክፉኛ ረብሾ የነበረ ሲሆን የዴ ሚጌል የቡድን ተጫዋቾች ሲያለቅሱ ታይተዋል።

    ዋናው ዳኛ ለግብ ጠባቂው ኦዎኖ ቀይ ካርድ ካሳዩ በኋላ ጨዋታውን አቋርጠውታል።

    ስፔ ንማድሪድ ውስጥ የተወለደው ዴ ሚጌል የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2015 ሌጋኔስን ሲቀላቀል ነበር። ስፔን ውስጥም ለስምንት የተለያዩ ክለቦች ተጫውቷል።

    ዴ ሚጉኤል በ2025 የተወለደች አንዲት ልጅ አለችው።