የሊቢያ ከፍተኛ የሃይማኖት ባለሥልጣን የናይኪ ምርቶች እንዳይለበሱ ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በሊቢያ ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥልጣን ያለው ‘ዳር አል ኢፍታ’፣ ሙስሊሞች የናይኪ አርማን የያዙ ልብሶችን እንዳይገዙ፣ እንዳይሸጡ ወይም እንዳይለብሱ የሚከለክል ውሳኔ አስተላለፈ።
በትሪፖሊ የሚገኘው ይህ ተቋም ክልከላውን የጣለው፣ ግዙፉ የአሜሪካ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ የተሰየመው በግሪካውያን የድል አምላክ ስም በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል።
በናይኪ አርማ ላይ የሚገኘው የ’ራይት’ (ስዉሽ) ምልክት የተሰራው ከአምላኳ ክንፎች በመነሳት እንደሆነም አክሏል።
አርማውን የያዙ አልባሳትን መልበስ ‘ሽርክ’ ወይም ከፈጣሪ ውጪ ሌላ አካልን ከማምለክ ጋር የተያያዘ ነገርን እንደማስተዋወቅ ይቆጠራል ሲል ሞግቷል።
ሊቢያ የጥንታዊቷ የግሪክ ‘ሳይሬን’ ከተማ መገኛ ነች፤ በከተማዋ ከሚገኙ አርኪዮሎጂካል ግኝቶች መካከል በዚሁ ስም የሚጠራው የግሪክ አማልክት ሃውልት ይገኝበታል።
በተጨማሪም የሃይማኖት ኮሚቴው፣ ናይኪ እስራኤልን ይደግፋል የሚል ክስ አቅርቧል። አማኞች እስራኤልን የሚደግፉ ኩባንያዎች ምርቶች እንዳይጠቀሙ ጥሪ አቅርቧል።
‘ፈትዋ’ በሚል የሚታወቀው ይህ አይነቱ ውሳኔ፣ በእስልምና የሕግ ጉዳዮች ላይ የሚሰጥ የሃይማኖታዊ አስተያየት ነው። ውሳኔው በሊቢያው ታላቁ ሙፍቲ ሳዲቅ አል ጋሪያኒ ጸድቋል።
ውሳኔውን ያሳለፈው ‘ዳር አል ኢፍታ’ በምዕራብ ሊቢያ ትሪፖሊ ውስጥ የሚገኝ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሃይማኖት ተቋም ነው።
የዚህ ተቋም የሃይማኖታዊ ውሳኔዎች ቀልል የማይባል ማኅበራዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ቢሆኑም፣ የመንግሥት ትዕዛዝ ወይም በሕግ ተፈጻሚ የሚደረግ ውሳኔ አይደሉም።



















