የአሜሪካ እና የኢራን ጦርነት እንዴት ሊቆም ይችላል? የሦስት ተንታኞች ዕይታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ እና የኢራንን ጦርነት ለማስቆም ተጨባጭ የሆነ ስምምነት ላይ ይደረሳል የሚለው ተስፋ ደብዝዞ ይታያል፤ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ጥቃቶችን በመፈጸም እና የማይለሳለሱ አቋሞችን በማንጸባረቅ ላይ ናቸው።
እነዚህ ጥቃቶች የተከሰቱት አሜሪካ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገባች መሆኗን ከገለጸች ከቀናት በኋላ ነው፤ በኢራን እና ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው አገራት ላይ ያነጣጠረ ሰፊ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ይፋ አድርጋለች።
የአሜሪካ ዓላማ ኢራንን ወደ ድርድር ማምጣት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች እንድታቆም ማስገደድ ነበር። ይህ ለዓለም ንግድ በጣም ወሳኝ የሆነው የመርከብ መተላለፊያ መስመር፣ አሜሪካ እና እስራኤል ግጭቱን ባለፈው የካቲት ወር ከጀመሩ ወዲህ በተግባር ተዘግቶ ቆይቷል።
ሁለቱ ወገኖች በሰኔ ወር የፈረሙት እና በ60 ቀናት ውስጥ ወደ ቋሚ የተኩስ አቁም እና የሰላም ስምምነት ሊያመራ የነበረው የመግባቢያ ሰነድ ጊዜው አልፏል።
ግጭቱ ወደ ሰባተኛ ወሩ ሲገባ፣ በቀጣይ እንዴት ሊቀጥል ይችላል የሚለውን በተመለከተ ሦስት ባለሙያዎች አስተያየት ሰጥተዋል።
አሜሪካ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና
ጄሰን ካምቤል፣ ከዋሽንግተን ዲሲ የሜድል ኢስት ኢንስቲትዩት
ችግሩ አሁንም አሜሪካ በኢራን ላይ ያላት ስትራቴጂያዊ ዓላማ በትክክል ምን እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑ ነው። ከፖለቲካዊ አቋም አንፃር ዋይት ሐውስ ተቀብሎ ይዞት ሊቀጥል ስለ ሚችለው ሁኔታ ተደጋጋሚ እየገመገመ ይገኛል።
በቀዳሚነት ወታደራዊው እርምጃ ፈጣን ድል ለማስገኘት በቂ ይሆናል ተብሎ ተገምቶ ነበር፤ ሆኖም የተፈለገውን ውጤት አላመጣም።
አሁን የምናየው አሜሪካ ለመጠቀም እየሞከረች ያለችው የተለያዩ የጫና መንገዶችን ነው፤ እነዚህም ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሳሪያዎችን ያካትታሉ።
በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ አስተዳደር በአንድ ዓይነት መረጋጋት ወይም አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ መቆየት የተመቸው ይመስላል። ማዕቀቡን በመቀጠል እና ኢራን በወሽመጡ በኩል የመርከብ እንቅስቃሴን ለማወክ ያላትን አቅም በየጊዜው ማዳከም ዓላማ ያላቸው ይመስለኛል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት አዲሶቹ ማዕቀቦች የኢራንን መንግሥት ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጣ ለማስገደድ በቂ እንደሚሆኑ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ሆኖም ኢራን በዚያን ጊዜ ደካማ ቦታ ላይ ትሆናለች ብለው ያምናሉ።
በቅርብ ቀናት የአሜሪካ ኃይሎች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረገው የመርከብ ዝውውር ሙሉ በሙሉ እንዳይቋረጥ ማድረግ ችለዋል የሚል ግምት አለ፤ ይህም የነዳጅ ዋጋ እንዳይንር ወይም ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳይፈጠር ረድቷል። ነገር ግን ጦርነቱ ሲጀመር የአሜሪካ ዓላማ ይህ አልነበረም።
የእኔ ግምት ኢራን ወደ መፍትሔ ለመድረስ ከፍተኛ ጥያቄ ታቀርባለች፤ ይህ ግን ለትራምፕ አስተዳደር በፖለቲካ ደረጃ ለመቀበል አዳጋች ሊሆን ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ ከስምምነት አስክትደርስ ኢራን ትጠብቃለች
ዶ/ር አኒሴህ ባሲሪ ታብሪዚ፣ ከለንደን ቻተም ሐውስ የመካከለኛ ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ፕሮግራም
በቅርቡ የተፈጸሙት ጥቃቶች ኢራን ስለ ጦርነቱ ያላትን ስሌት በእጅጉ ይቀይራሉ ብዬ አላስብም። ቴህራን በኢኮኖሚዋ ላይ የሚጨመር ጫናን እና ባለፉት ጥቂት ወራት እንዳየናቸው ተቋርጠው የሚቀጥሉ ጥቃቶችን ለመቋቋም እየተዘጋጀች ነው ብዬ አስባለሁ። የእነርሱ ዓላማ ጥቃቶቹ ወደ ሰፊ ግጭት እንዳይሸጋገር የተመጣጠነ ምላሽ መስጠት ይሆናል።
በኢኮኖሚው ረገድ ይህ ሁኔታ ቀድሞውኑ በጦርነቱ የተጎዳውን የኢራን ኢኮኖሚ ያዳክመዋል። ከዚህም በተጨማሪ አገሪቱ መሠረታዊ መዋቅራዊ ችግሮች እንዳለባት ከታኅሣሥ እና ጥር ወራት በኢራን ከተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ማየት ተችሏል።
ሆኖም ይህ ኢኮኖሚያዊ ጫና የኢራንን አቋም በቅርብ ጊዜ ይቀይረዋል የሚል እምነት ከኢራን ወገን እንዳለ አይሰማኝም፤ ይህም የድርድር ጉዳዮችን ጨምሮ ነው።
ይህ ማለት ግን ኢራን ከግጭቱ መውጫ መንገድ አትፈልግም ማለት አይደለም። የምናየው ግን አሜሪካ ወደ የመግባቢያ ሰነዱ እንድትመለስ ወይም ቢያንስ ወደ አንድ ዓይነት ስምምነት እንዲደረስ ትጠብቃለች።
ቴህራን ለአሜሪካ ጫና እጅ ለመስጠት አትፈልግም፤ እንዲሁም በማዕቀቦች ወይም በተጨማሪ ጥቃቶች ምክንያት የራሷን አቋም ለመቀየር ፈቃደኛ አይደለችም።
ወደ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መመለስ
ኒኮላስ ሆፕተን፣ በለንደን የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስስ ኢንስቲትዩት፣ የዓለም አቀፍ ደኅንነት ተመራማሪ እና በኢራን የቀድሞ የብሪታኒያ አምባሳደር
በቅርቡ የታየው የወታደራዊ እርምጃ መጨመር ኢራን እጅ እንድትሰጥ አያደርጋትም፤ ይህ የግጭቱ አዲስ ምዕራፍ ብቻ ነው። ኢኮኖሚያዊ ጫናውም ብዙ ውጤት ያመጣል ብዬ አላስብም፤ ምክንያቱም ከኢራን ጋር የሚነግዱት ቻይና፣ ሩሲያ እና ሌሎች ብዙ አገራት አሜሪካ ብቻዋን የምትጥለውን ማዕቀብ አይደግፉም።
ኢራን አሁንም በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለውን የመርከብ እንቅስቃሴን ማወክ ትችላለች፤ በእርግጥም በዓለም ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆነውን ቦታ በቁጥጥሯ ስር አድርጋ ይመስላል።
ታዲያ የአሜሪካ የመውጫ ስትራቴጂ ምንድን ነው?
በእርግጥ አሜሪካ መንገዱን አስቀድማ አግኝታዋለች። ይህም ትራምፕ በሰኔ ወር በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ላይ የተቀመጠውን ስምምነት ለማስፈጸም ተከታታይና ጽኑ ጥረት ብታደርግ ከግጭቱ የሚያወጣበት መንገድ ይሆንል።
እንዲህ ያለ ስምምነት ለአሜሪካ ድል የሚሆን ውጤት ያስገኛል፤ ምክንያቱም በእስላማዊቷ ሪፐብሊክ ውስጥ ያሉትን አክራሪ ኃይሎች ያዳክማል። በተጨማሪም ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ አትታጠቅም የሚለውን ለሁሉም ያረጋግጣል።
በዚህ የመግባቢያ ሰነድ ውስጥ ወሳኝ የሆነ ነጥብ አለ፤ ይህም በኢራን ላይ የተጣሉትን ሁሉንም የአሜሪካ ማዕቀቦች ማንሳት ነው።
እነዚህ ማዕቀቦች ቢነሱ ከጊዜ በኋላ በኢራን ውስጥ ትልቅ ተፅእኖ ያለውን የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብን ያዳክሙታል። በቀሪው ዓለም እና በኢራን መካከል የሚፈጠረው አዲስ የኢኮኖሚ ትስስር ቀስ በቀስ መሠረታዊ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ለውጦችን ያመጣል። በመጨረሻም እስላማዊ ሥርዓቱ ቢቀጥልም ከአሁኑ በጣም የተለየ ባህሪ ይኖረዋል።
እርግጥ ነው፣ ይህንን ማሳካት ቀላል አይሆንም፤ ምክንያቱም የኢራን አብዮታዊ ዘብ በኢራን ኢኮኖሚ ውስጥ ጥልቅ ተፅእኖ አለው። ሆኖም በቂ ጊዜ ከተሰጠው እና አሜሪካ ከአጋሮቿ ጋር ስትራቴጂያዊ ትዕግሥት ካሳየች ሊሠራ ይችላል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ይህ ዓይነቱ ትዕግሥት በጣም አናሳ ይመስላል።
ለጊዜው ግን ለሁሉም ወገኖች ጎጂ የሆነ፣ ግልጽ ውጤት የሌለው እና ውስብስብ ሁኔታ እንደሚቀጥል አስባለሁ።















