የሁቲዎች ግስጋሴ በቀይ ባሕር ላይ የመርከቦችን እንቅስቃሴ ያስተጓጉል ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, EPA
የየመን ሁቲዎች በባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ የሚገኘውን ቁልፍ ደሴት መቆጣጠራቸው ተዘግቧል። ይህም አውሮፓን ከእስያ ጋር የሚያገናኘውን እና በዓለም ወሳኝ የሆነውን የባሕር ትራንስፖርት መስመር አደጋ ውስጥ ከትቶታል።
ባለሥልጣናት እንደሚሉት የየመን መንግሥት ደጋፊ ኃይሎች አርብ ዕለት ከፔሪም ደሴት ለቅቀው ወጥተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ለሳምንት ፈጣን ግስጋሴ ሲያደርጉ የነበሩት በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች የየመንን የቀይ ባሕር ዳርቻ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል።
የዓይን እማኞች እንደሚሉት በባብ ኤል መንደብ ባሕር ዳርቻ ታጣቂዎች እየተሰማሩ ሲሆን፣ በዙሪያውም ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እየተንቀሳቀሱ ነው።
ሁቲዎች ግስጋሴያቸውን ቀጥለው ወደ አፍሪካ ቀንድ አገራቱ ጂቡቲ እና ኤርትራ ቀርበው የሚገኙትን ሃኒሽ የተባሉትን ደሴቶች ሰኞ ዕለት በቁጥጥራቸው ስር አስገብተው በቀይ ባሕር ላይ ያላቸውን ይዞታ አጠናክረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images via Getty
በወሽመጡ ላይ የምትገኘው ቁልፍ የሆነችው ፔሪም ደሴት በቁጥጥር ሥር የዋለችው ሁቲዎች የወደብ ከተማዋን ሞካን ከያዙ ከአንድ ቀን በኋላ እንደሆነ ወታደራዊ ምንጮች ገልጸዋል።
የሞካ ከተማ ነዋሪዎችም የሁቲ ተዋጊዎች ረቡዕ ዕለት ከመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች ጋር እልህ አስጨራሽ ውጊያ ካደረጉ በኋላ ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ተናግረዋል። የተቀሰቀሰው ውጊያም በርካታ ነዋሪዎች ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አድርጓል።
አንድ ግለሰብ ውጊያው የተቀሰቀሰው ያለምንም ማስጠንቀቂያ እንደሆነ ለቢቢሲ አረብኛ አገልግሎት የመካከለኛው ምሥራቅ ፕሮግራም ተናግሯል።
"የተጎዱ ሰዎች ያለምንም እርዳታ በመንገድ ላይ ወድቀው በሚታዩበት አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ በርካታ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አስገድዷል" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ታጣቂዎቹ ከሳምንት በፊት በሳዑዲ በሚደገፉት የመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች ላይ ጥቃት ከከፈቱ አንስቶ በመቶዎች ሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ቢያንስ 46 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስታውቋል። በግጭቱ ምክንያት በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከ1400 ሰዎች በላይ ወሽመጡን አቋርጠው ወደ ጂቡቱ መግባታቸውን የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ኢልያስ ሞሳ ዳዋሌህ ተናግረዋል። ግጭቱ መባባሱም የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
በሳዑዲ መርከቦች ላይ የተሰነዘረው ዛቻ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሁቲዎች በዓለም አቀፍ የባሕር ጉዞ ላይ ስጋት እንደሌለ እና ዒላማ የሚያደርጉት ከሳዑዲ አረቢያ የሚነሱ መርከቦችን ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። ሳዑዲ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲዘጋ ያደረገው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ወዲህ ነዳጅ ወደ ውጪ የምትልከው በዚህ ወሽመጥ ነው።
ሁቲዎች ዓለም አቀፍ መርከቦችን ዒላማ አናደርግም ቢሉም ቡድኑ ቀደም ብሎ በጋዛ ጦርነት ወቅት ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦችን ብቻ እንደሚያጠቁ ገልጸው፤ ነገር ግን ምንም ግንኙነት የሌላቸው በርካታ መርከቦች ላይ ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ የባሕር ትራስፖርት ድርጅቶች ጥርጣሬ ገብቷቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በቴሌግራም ባጋሩት ጽሑፍ ቡድኑ "መጠነ ሰፊ፣ ከፍተኛ ውጤት የሚያስከትል ወታደራዊ ዘመቻ" እንደሚያካሂድ እንደሚያሳውቅ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ባብ ኤል መንደብ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?
ባብ ኤል ማንዳብ ወሽመጥ የሚገኘው ከአረብ የቀይ ባሕር በኩል በየመን እና በአፍሪካ በኩል ደግሞ በጂቡቲ እና በኤርትራ መካከል ነው። ከሕንድ ውቅያኖስ እና ከኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚነሱ መርከቦች ሱዌዝ ቦይ ለመግባት ይህንን ወሽመጥ ማቋረጥ ግድ ይላቸዋል።
36 ኪሎ ሜትር ስፋት እና 115 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው ባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ፣ በአውሮፓውያኑ 1869 አውሮፓ እና እስያን የሚያገናኝ አጭር የባሕር መስመር የፈጠረው የሱዌዝ ቦይ ሲከፈት በዓለም ንግድ ወሳኝ መስመር ሆኗል።
በመሆኑም የቀይ ባሕር ወሽመጥ አሁን ላይ በዓለማችን እንቅስቃሴ ከሚበዛባቸው መስመሮች አንዱ ሆኗል። አንድ አራተኛ የሚሆነው የዓለም መርከቦች የሚያልፉትም በዚሁ ወሽመጥ ነው።
20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን ጦርነት ምክንያት ተዘግቷል። የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ መዘጋትም ተጨማሪ 12 በመቶ የሚሆነው የዓለም የነዳጅ አቅርቦት ያስተጓጉላል።

እንደ የአሜሪካ የኤነርጂ መረጃ አስተዳደር ከሆነ የኢራን ጦርነት ዓለም አቀፍ የባሕር እንቅስቃሴን ሳያስተጓጉል በፊት ከመካከለኛው ምሥራቅ እና እስያ አገራት በቀን ወደ አምስት ሚሊዮን በርሜል የሚጠጋ ነዳጅ ወደ ምዕራባውያን አገራት ይደርስ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ወደ 8 በመቶ የዓለም የተጣራ የተፈጥሮ ጋዝ በወሽመጡ በኩል የሚጓጓዝ ሲሆን፣ ይህም ለዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ወሳኝ እንዲሆን አድርጎታል።
የሆርሙዝ ወሽመጥ ከተዘጋ አንስቶ ቀይ ባሕር ለዓለም ንግድ ወሳኙ መስመር ሆኗል። ሳዑዲ አረቢያ ባብ ኤል መንደብን ነዳጇን ከያንቡ ወደብ ለማጓጓዝ እንደ መሸጋገሪያ መጠቀም ጀምራ ነበር። ሪያድም ከምሥራቃዊ የነዳጅ ማምረቻዋ በነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ በቀን በሚሊዮኖች በርሜል የሚቆጠር ድፍድፍ ነዳጅ ትልካለች።
ከድፍድፍ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ማስተላለፊያነት በተጨማሪም ባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ምሥራቁን እና ምዕራቡን የዓለማችንን ክፍል የሚያገናኝ ዋነኛ የንግድ መስመር አካል ነው። በቀን በርካታ እቃ ጫኝ መርከቦች ይመላለሱበታል።
ወሽመጡ የሚዘጋ ከሆነ በ2021 የፓናማን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለብለበው 'ኤቨር ግሪን' መርከብ ባጋጠማት ችግር የሱዌዝ ቦይን በዘጋችበት ጊዜ የተፈጠረውን ዓይነት ውጤት ሊያስከትል ይችላል።
ይህ ክስተት በዓለም የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ማነቆ ፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እና በነዳጅ እና ሌሎች ፍጆታዎች አቅርቦት ላይ መዘግየት እንዲፈጠር አድርጎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Suez Canal Authority via European Pressphoto Agency
የሁቲዎች ሚና ምንድን ነው?
የመን በአውሮፓውያኑ 2014 ሁቲዎች የሰንዓን መንግሥት ከገረሰሱ በኋላ በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት ክፉኛ ተጎድታለች። በ2015 ደግሞ በሳዑዲ የሚመራው የአረብ አገራት ጥምረት በአገሪቱ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመመለስ ጣልቃ ከገባ በኋላ ደግሞ ግጭቱ ይበልጥ ተባብሷል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ከሆነ በግጭቱ ከ150 ሺህ ሰዎች በላይ የሞቱ ሲሆን፣ በዓለም አስከፊ ከሆኑ የሰብዓዊ ቀውሶች ውስጥ አንዱን አስከትሏል። ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ድጋፍ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
በተመድ አሸማጋይነት በ2022 የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም ሐምሌ ወር ላይ በኢራን የሚደገፈው ሁቲ በሳዑዲ አረቢያ መርከቦች ላይ እገዳ መጣሉን ማስታወቁን እና በሳዑዲ አየር ማረፊያዎች፣ የነዳጅ መሠረተ ልማት እና የነዳጅ ማከማቻዎች ላይ የሚሳዔል እና ድሮን ጥቃቶች መፈፀሙን ተከትሎ ግጭቱ ድጋሚ አገርሽቷል።
ቡድኑ እገዳው ሳዑዲ ሁቲ በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ወደቦችን እና አየር ማረፊያዎችን እንዳይጠቀም በመከልከሏ የአጸፋ እርምጃ እንደሆነ ገልጿል።
በጋዛ ጦርነት ወቅት ሁቲዎች በባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ከ100 በላይ የንግድ መርከቦች ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን ፈፅመዋል። በዚህም ሁለት መርከቦች የሰመጡ ሲሆን አራት መርከበኞች ተገድለዋል።
ኅዳር 2023ም ቡድኑ በቀይ በሕር ላይ ባለቤትነቱ የብሪታኒያ የሆነ እና በጃፓን እየተዳደረ ያለ እቃ ጫኝ መርከብ ለመጥለፍ ሄሊኮፕተር ተጠቅሟል።

የፎቶው ባለመብት, Houthi Military Media via Reuters
ምንም እንኳን ሁቲዎች በወቅቱ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች ዒላማ እንደሚያደርጉ ቢገልጹም ጥቃቱ ማንንም ያልለየ እንደሆነ ተገልጿል። ይህም በርካታ ዓለም አቀፍ ትላልቅ የባሕር ትራንስፖርት እና የነዳጅ ኩባንያዎች በአካባቢው የሚደረግ ጉዞን እንዲያግዱ አድርጓል።
አሜሪካም በታጣቂዎቹ ላይ ጥቃቶችን ፈጽማለች።
አሜሪካ "ሁቲዎች እጅ ሰጥተዋል ስትል፣ ሁቲዎች በበኩላቸው "አሜሪካ ናት ያፈገፈገችው" ብለዋል። ጥቃቶቹም ቀንሰው የነበረ ሲሆን ተንታኞች ጥቃቱ እንደገና ሊጀምር እንደሚችል ስጋት አላቸው።
ሁቲዎች ወሳኝ የሆነው የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥን ከተቆጣጠሩ ኢራን ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር እያደረገች ላለው ጦርነት ጠቀሜታ ሊኖረው ቢችልም በዓለም የነዳጅ አቅርቦት ላይ ግን ሌላ አደጋ ያስከትላል።
ውጥረት ውስጥ ገባው የዓለም የባሕር ትራንስፖርት
ባብ ኤል መንደብ ማለት በአረብኛ ቋንቋ ትርጉሙ "የእንባ በር" ወይም "የሐዘን በር" ማለት ነው። ስሙ የሚያመልክተው ከኃይለኛ የባሕር ወጀብ እና ከማይገመት ነፋስ እስከ የባሕር ላይ ዘረፋ እንዲሁም ግጭቶች ድረስ የሚያናውጠው አደገኛ ስፍራ በመሆኑ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2008 እና በ2012 መካከል ባሉት ዓመታት ውስጥ ባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ እና በዙሪያው ያለው ውሃ በርካታ ጥቃቶችን አስተናግዷል። እነዚህ ክስተቶች ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ እና የባሕር ትራንስፖርት ድርጅቶች በቀጣናው ያለውን ደኅንነት እንዲያጠናክሩ አድርጓል።
ይህ መስመር መዘጋቱም በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ውጥረት ውስጥ ያለውን የነዳጅ ገበያን የባሰ ቀውስ ውስጥ የሚከት ነው።

የፎቶው ባለመብት, West Asia News Agency / Reuters
በባሕረ ሰላጤው ያለው የባሕር ላይ ጉዞ መቋረጥ የዓለም ነዳጅ ዋጋ መተመኛ የሆነው ብሬንት ድፍድፍ ዋጋን በበርሜል ከጦርነቱ በፊት ከነበረው 70 ዶላር ወደ ከ100 ዶላር በላይ አድርሶታል።
በበርካታ የዓለም ፍጆታዎች ንግድ ላይም ከሸማቾች እስከ የግብርና ግብዓቶች ድረስ ተፅዕኖ ፈጥሯል።
በሌላ የባሕር መስመር ላይ ሊያጋጥም የሚችለው አዲሱ መስተጓጎልም የዋጋ ንረትን ይበልጥ የሚያብስ ሲሆን፣ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን የማጣኔ ሃብት ቀውስ ያከፋዋል።















