ኦፕንኤአይ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተፈጸሙ ስድስት አስጊ እና ያልተጠበቁ ክንውኖችን ይፋ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኦፕንኤአይ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሎቹ የተፈጸሙ ስድስት አስጊ ወይም ያልተጠበቁ ክንውኖችን ይፋ አደረገ።
የኤአይ ኩባንያው ኦፕንኤአይ ለወደፊት እንዲህ ያሉ ክስተቶችን ይፋ ማድረግ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም ይፋ ካልተደረጉ ክንውኖች መካከል ኤአይ መረጃ መፍጠሩ ወይም መደበቁ ይገኝበታል ተብሏል።
የቻትጂፒቲ ፈጣሪ የሆነው ኦፕንኤአይ ኃላፊ ሳም አልትማን በያዝነው ሳምንት መባቻ "ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ተገቢ ስለሆነ ትክክለኛውን ነገር እንደምናደርግ ዓለም ሊያምን ይገባል። የጉዳዩን አሳሳቢነት እንረዳለን" ብሎ ነበር።
ባለፉት ቀናት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የሚቀርቡ ትችቶች ተጠናክረዋል። ኤአይ ለሰው ልጆች ኅልውና አደጋ ነው የሚለውም እያነጋገረ ይገኛል።
ኦፕንኤአይ የሠራቸው የኤአይ ሞዴሎች ያልተገባ ባሕሪ ያሳዩባቸውን ክስተቶች ይፋ አድርጓል። የተለያዩ ክንውኖች እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ሞዴሎች የሚጠበቅባቸውን ለማከናወን በሚል ያልተገባ ባሕሪ አሳይተዋል።
ከታዩት ያልተገቡ ባሕሪዎች መካከል የተጣለባቸውን ክልከላ ለማለፍ የራሳቸውን ትዕዛዝ መፍጠር፣ ስህተታቸውን መሸፈን እና መረጃ መፍጠር ይገኙበታል።
የኤአይ ሞዴሎች ያልተገባ ድርጊት ሲፈጽሙ ወይም "ከመስመር ሲወጡ" ምርመራ ተደርጎ መረጃው ይፋ የሚደረግበት አዲስ አሠራር ተዘርግቷል።
የኤአይ ሞዴሎች የሚሠሩ ባለሙያዎች እነዚህን ክስተቶች ከገመገሙ በኋላ መረጃው ለሕዝብ ይፋ መሆን ካለበት ውሳኔ እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ኦፕንኤአይ ባወጣው መግለጫ "ከመስመር የወጡ ነገሮችን በመግለጽ ተዓማኒ መሆን እንዳለብን እናምናለን" ብሏል።
የኦፕንኤአይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሎች በራሳቸው ተነሳሽነት 'ሀጊንግ ፌስ' የተባለውን ተቋም ሀክ ማድረጋቸው ሐምሌ ላይ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
የኤአይ ሞዴሎቹ ላይ ቁጥጥር ማድረግ አለመቻሉ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮም ነበር።
የሀጊንገ ፌስ አጋር መሥራች ቶማስ ውልፍ ክስተቱ "አንቂ ደውል ነው" ብሏል።
ከዚያ ወዲህ ኤአይ የጋረጠው የደኅንነት ስጋት አነጋጋሪ ሆኗል። የኤአይ ተመራማሪዎች፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ኃላፊዎች እና ፖለቲከኞችም የውይይቱ አካል ናቸው።
የኦፕንኤአይ ተገዳዳሪ የሆነውን አንትሮፒክ ለቅቆ የወጣው ጄኮብ ኮክሶን ቴክኖሎጂው የሰው ልጆችን ሊያጠፋ እንደሚችል ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።
ኤአይ ለሰው ልጆች ስጋት መሆኑን ባለሙያው መግለጹን ተከትሎ የአንትሮፒክ ሳይንቲስት ኢቫን ሁቢንገር ኤአይ የሰው ልጆችን "በቀጣይ አሥርታት" ሊያጠፋ የሚችልበት ዕድል ከ10% በላይ ነው ብሏል።
የአንትሮፒክ አጋር መሥራች ጃክ ክላርክ ለቢቢሲ እንደገለጸው ኤአይ ከቁጥጥር ከወጣ የሚገታበት 'ኪል ስዊች' ያስፈልጋል።
የኩባንያው ኃላፊ ዳርዮ አሞዲ ኤአይ እየበለጸገበት ያለው ፍጥነት እንዲቀንስ እና የቅርብ ክትትል እንዲደረግበት አሳስቧል።
ኤአይ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር የሚያስገኘውን የገንዘብ ጥቅም የሚጋፋ መሆን እንደሌለበትም አክሏል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኤአይ ላይ የተነሱ የደኅንነት ስጋቶችን "ማጭበርበሪያ" በሚል አጣጥለዋል።















