የትዳር አጋር ለማግኘት አጭበርባሪዎች እጅ ላይ የወደቁት ላጤዎች

ፊቷን ያዞረች ሴት ሙሽራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቻይና ባለው ያለተመጣጠነ የፆታ ጥምርታ ምክንያት የሴቶች ተፈላጊነት ከፍተኛ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

የሕዝቧን ቁጥር ለመመጠን ስትል ለበርካታ ዓመታት "የአንድ ልጅ" ፖሊሲ ስታራምድ የቆየችው ቻይና አሁን ደግሞ ሌሎች ማኅበራዊ ቀውሶች እያጋጠሟት ነው።

ፖሊሲው ቻይናውያን ጥንዶች አንድ ልጅ ብቻ ሳይሆን ወንድ እንዲወልዱ ያበረታታ ስለነበር አሁን ላይ የሴቶች ቁጥር ከወንዶች ጋር አልመጣጠን ብሏል።

በቻይና የወንዶች ቁጥር ከሴቶቹ በ30 ሚሊዮን ይልቃል። በዚህ ምክንያት ላጤ ቻይናውያን ውሃ አጣጭ ለማግኘት ዋጋ እየከፈሉ ነው። በግል ጥረታቸው ተስፋ የቆረጡትም የትዳር አጋር አፋላጊ ድርጅቶችን አማራጭ እያደረጉ ነው።

የ37 ዓመቱ ዋንግ ዡዋንግ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው። ዋንግ የእነዚህን ድርጅቶች ማስታወቂያ እስከሚያይ ድረስ ሚስት አገኛለሁ የሚለው ተስፋው ተሟጦ ነበር።

እነዚህ የትዳር አገናኞች ለማይሰምር የፍቅር ግንኙነት ዓመታትን ማባከን እንደሌለበት እና እነርሱ "ከአንዲት ጨዋ እና ታማኝ ሴት" ጋር እንደሚያስተዋውቁት ቃል እንደገቡለት ዋንግ ይናገራል።

"የግዌጆው አካባቢ ሴቶች ቁጥብ ናቸው፤ ለትዳር ይሆናሉ" ብለውም ሰብከውታል።

"ጥሩ የቤት አስተዳዳሪ፣ ባለሙያ እና ቤተሰቦቻቸው ድሃ ስለሆኑ ከታጋባችሁ በኋላ ተረጋግተው ካንተ ጋር ሕይወታቸውን መምራት ነው የሚፈልጉት" ሲሉም እንደነገሩት ያስረዳል።

ውሃ አጣጩንም ለማግኘት ተስፋ በማድረግ በደቡባዊ ምዕራቧ ግዌጆው ግዛት ውስጥ ወደምትገኘው ግዌያንግ ከተማ አቀና።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እዚያም ከእርሱ ፍላጎት ጋር አብራ የምትሄድ የምትመስል ሴት ተዋወቀ።

ከዚች ሴት ጋር ከመጋባታቸው በፊት የተገናኙት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ሲሆን፤ ነገሮች የተለወጡትም ብዙም ሳይቆይ ነበር።

"መላው ቤተሰቤ ችግር ውስጥ ተዘፈቀ" ይላል ዋንግ እጆቹ እየተንቀጠቀጡ።

ያገባት ሚስቱ የነገረችው ሁሉ ውሸት መሆኑን ካወቀ ከአንድ ዓመት በላይ ቢሆንም አሁንም ከደረሰበት ጉዳት አላገገመም።

ይህቺ ሴት አስተናጋጅ የነበረች ሲሆን፣ ከሦስት ጊዜ በላይ ትዳር መሥርታለች። የሦስት ልጆችም እናት ናት። ከዚህም በተጨማሪ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ በሽታ የነበረባት እና ዕዳ ውስጥ የተዘፈቀች ነበረች። ትክክለኛ ዕድሜዋንም ዋሽታዋለች።

አሁን ላይ ፍቺ ለመፈፀም እየታገለ ነው። የተወሰነ የቆጠበውን ገንዘቡን መልሶ እስከሚያገኝ ድረስም ወደ ቀድሞ ሕይወቱ መመለስ ከብዶታል።

ገንዘቡን ከብዙ ትዳር ፈላጊዎች ጋር ከተዋወቀ በኋላ በሰዓታት ውስጥ ለኤጀንሲው እንደከፈለ ይናገራል።

"ወላጆቼ ባደረኩት ነገር ይወቅሱኛል፤ እንቅልፍ የለኝም፤ ጭንቀት ውስጥ ነው ያለሁት፤ በሥራ ላይ ማተኮር አልችልም" ብሏል።

የዋንግ ታሪክ በቻይና ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ የቆየውን እጅግ በጣም ውስብስብ የሆነውን የሥነ ሕዝብ ቀውስ ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ለአስርተ ዓመታት ጥንዶች አንድ ልጅ ብቻ እንዲወልዱ ደንግጎ የቆየ ሲሆን በአውሮፓውያኑ ጥር 2016 ይህንን ሕግ አሻሽሎታል።

ሕጉ ከመሻሻሉ በፊት ጥንዶች አንድ ልጅ ያውም ወንድ እንዲወልዱ የሚፈቅደው ሕግ፣ የሴቶችን ቁጥር እንዲቀንስ እና የፆታ ጥምርታ እንዳይመጣጠን አድርጎታል።

አሁን በቻይና የወንዶች ቁጥር ከሴቶቹ በ30 ሚሊዮን ይበልጣል። ይህም የአውትራሊያ ጠቅላላ ሕዝብን ያህላል።

ይህም እንደ ዋንግ ያሉ በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ እና በአነስተኛ ከተማ የሚኖሩ ወንዶች ጥቂት አማራጭ ብቻ እንዲኖራቸው አድርጓል።

በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶችም ፈላጊያቸው ብዙ እንደሆነ ስለሚያውቁ መራጭ ናቸው።

"እኔ ባለሁበት ከተማ ከወንዶች የሚጠበቀው ከፍተኛ ነው፤ መኪና፣ ቤት ሊኖርህ ይገባል። ቤተሰቦችህም የሆነ ቢዝነስ እንዲኖራቸው ይጠበቃል" ይላል ዋንግ።

በርካታ የወንድ ቤተሰቦችም ለረዥም ጊዜ በቆየው የቻይና ባህል መሠረት ለሙሽራዋ ከፍተኛ ጥሎሽ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። ይህም የወንዶች ቁጥር ከሴቶች በሚበልጥበት የቻይና ክፍሎች ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።

ለዚህም የትዳር አጋር አፋላጊ ተቋማት ፈጣን መፍትሄዎችን እያቀረቡ ነው።

እነዚህ ተቋማት ለቻይና አዲስ ናቸው። ሆኖም አብዛኞቹ ዕድሜያቸው እየጨመረ ያለ እና አጋር ለማግኘት እየታገሉ ያሉ ተጋላጭ ወንዶችን የሚያሳድዱ ይመስላሉ።

በቅርቡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘርፉ ፈጣን ዕድገት እንዳሳየ፤ ነገር ግን "ሕገ ወጥ ድርጊቶችን እና ቀውስ" እየፈጠረ እንደሆነ ዘግቧል።

እንዲህ ዓይነቱ ማጭበርበር በቻይና ውስጥ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፤ የቻይና ባለሥልጣናትን ትኩረት መሳብ ችሏል።

ፓስፖርታቸውን የሚያሳዩ ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሁን ላይ ይህ የትዳር ገበያ በቤይጂንግ ዕይታ ውስጥ ገብቷል

ዐቃቤ ሕጎች ከጥር 2024 እስከ መጋቢት 2025 ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከዘርፉ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች የ1546 ግለሰቦችን ጉዳይ ተመልክተዋል።

ጉዳዩ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት በመፍጠሩም በዚህ ወር አራት የተለያዩ ተቋማት በጋራ ሆነው የትዳር አጋር አፋላጊ ዘርፍ ላይ አገር አቀፍ ዘመቻ ከፍተዋል።

በአንድ ክስተት ላይ እነዚህ ኤጀንሲዎች አስተናጋጆችን በመጠቀም ከ128 ተጎጂዎች ከ371 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ አጭበርብረዋል።

በቤይጂንግ የሕግ ድርጅት ያላቸው ፋን ቢነግሄ "መንግሥት እነዚህ ተቋማት ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት" ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዋንግ በተቋሙ ላይ እምነት ያሳደረው የውሃ አጣጩን የኋላ ታሪክ እንደሚያጠናለት እና ተጎጂ ከሆነ የሚከፍለውን ገንዘብ እንደሚመልስ ከሳወቀው በኋላ ነበር።

በዚህ እምነት ላይ ተመሥርቶ ክፍያ ከፈፀመ በኋላም ነበር ከሴቶቹ ጋር መተዋወቅ የጀመረው።

በጥቂት ቀናት ውስጥም በተለያዩ ጊዜያት ከሰባት ሴቶች ጋር ተዋውቋል። ሴቶቹ ከየት እንደመጡ፣ ከዚህ በፊት አግብተው ያውቁ እንደሆነ እና ልጆች እንዳላቸውም ጠይቋቸዋል።

ስምንተኛዋ ሴት ግን ልቡን አሸንፋዋለች። ከዚህ በፊት ያላገባች፣ ልጆች የሌሏት እና ከእርሱ በዕድሜ የምታንስ ሴት እንዳገኘም ተስፋ አድርጎ ነበር።

"ቀለል ያለ ልብስ ነበር የለበሰችው። ታማኝ እና ዝምተኛ ትመስል ነበር" ብሏል ዋንግ። ከእርሷ ጋር አራት ወይም አምስት ጊዜ ተገኛኝተው ለአስር ደቂቃዎች ያህል አውርተዋል።

ስልክ እንዳይለዋወጡ ወይም በግል መልዕክቶች ዝርዝር ግላዊ መረጃዎችን እንዳይለዋወጡ ጥብቅ ገደብ ተጥሎበት ነበር። በዚህ ሒደት ከሁለት እና ከሦስት ቀናት በኋላ ትክክለኛ ሴት እንደሆነች ወስኖ ጥሎሽ ለመክፈልም ተስማምቷል።

"ከ300 ሺህ ዩዋን [ከ44 ሺህ ዶላር] በላይ አውጥቻለሁ" ሲል የከፈለበትን መረጃ አሳይቷል።

"የሰርጉ እና ሌሎች ወጪዎች ሲጨመሩ፤ በአጠቃላይ ከ400 ሺህ እስከ 500 ሺህ ዩዋን (የቻይና ገንዘብ) አውጥቻለሁ" ብሏል።

ዋንግ እና የቀድሞ ሚስቱ ጋብቻ ከፈፀሙ በኋላ የተነሱት ፎቶ። ሙሽራዋ ፊቷ እንዳይታይ የተደረገ ሲሆን የአበባ እቅፍ ይዛለች።
የምስሉ መግለጫ, ዋንግ ከቀድሞ ሚስቱ ጋር ጋብቻ ከፈፀሙ በኋላ የተነሱት ፎቶ

ወደ ትዳር በገባ በወራት ውስጥ ግን ባለቤቱ ብድር እንደወሰደች በመግለፅ አበዳሪ ነን ከሚሉ አካላት በተደጋጋሚ ስልክ ይደወልለት ጀመር።

ዋንግ መጠራጠር ያዘ። የደበቀችው አንዳች ነገር እንዳለ ለማወቅ ስልኳን ሲፈትሽ የቀደመ ሕይወቷን፣ የልደት ካርዷን፣ የቀደመ የጋብቻ ሁኔታዋን የተመለከተ መረጃ ማግኘት እንደቻለ ይናገራል።

ስለጉዳዩ ሲጠይቃትም ፍቺ እንደምትፈልግ እና የከፈለውን ጥሎሽ ሽራፊ ገንዘብ እንደማትከፍል እንደነገረችው ይገልጻል።

ወደ አጣማሪው ተቋም ቢያመራም ከሥፍራው አልነበረም።

ቢቢሲም በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጥ አካል ማግኘት አልቻለም። አንድ ሌላ ኤጀንሲ ኃላፊ ግን በቢሮው ውስጥ ለማነጋገር ፈቃደኛ ከሆኑ በኋላ የሥራ ባልደረባቸው አካባቢውን እንዲለቁ ነግረዋቸዋል።

 ዋንግ ሙሽራውን ያገኛት እንዲህ ዓይነት ክፍል ውስጥ ነበር
የምስሉ መግለጫ, ዋንግ ሙሽራውን ያገኛት እንዲህ ዓይነት ክፍል ውስጥ ነበር

ዋንግ አሁን ላይ ሌሎች ወንዶች ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥማቸው በማኅበራዊ ሚዲያ የቪዲዮ መልዕክቶችን በማጋራት ጊዜውን እያሳለፈ ነው።

የተከራየው ጠባብ አፓርትመንትም ኤጀንሲዎቹን በሚፈልጉ ወይም ከሳምንታት ትዳር በኋላ ጥላቸው ከሄደችው ሚስታቸው ገንዘባቸውን ለማስመለስ በሚሞክሩ ወንዶች ተሞልቷል።

የጂያንግዥ ነዋሪ የሆኑት የ59 ዓመቱ ዡ ሩሊን ለልጃቸው ሚስት ለመፈለግ ለኤጀንሲዎች ወደ 500 ሺህ ዩዋን እንደከፈሉ ተናግረዋል።

ልጃቸው በአካል ከማይተዋወቃት ሴት ጋር ካወራ ከሰባት ቀናት በኋላ ነበር ጋብቻውን የፈፀመው።

ከተጋቡ በኋላ ግን "አይፎን ስልክ እንዲገዛላት እና ለቢዝነሷ 200 ሺህ የሚጠጋ ዩዋን እንዲልክላት ጠይቀዋለች። ለጌጣ ጌጥ እና ለሰርግ ልብስ 120 ሺህ ዩዋን መጠየቋንም" ተናግረዋል።

"የምፈልገው አብራን እንድትኖር ስለነበር፤ ቤት ስትፈለግ ቤት ገዝቸላቸዋለሁ። በምትለው ጉዳይ ሁሉ እስማማ ነበር" ብለዋል።

ሆኖም ከሁለት ሳምንት ላነሰ ጊዜ ከኖረች በኋላ ጥላቸው እንደሄደች ይናገራሉ። ከዚያ ግን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውላ ፍቺ ፈፅመዋል።

የትዳር አጋር አፈላላጊው ድርጅት ባለቤቶችም በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ ታስረዋል። ሆኖም አሁንም ከደረሰባቸው ጉዳት አላገገሙም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ መደበኛ በሆነ መልኩ የደንበኞቻቸውን የኋላ ታሪክ እንደማያጠኑ አምነዋል። ሴቶቹን የሚያገናኟቸው በአካባቢው ያሉ ሌሎች ትዳር አፈላላጊዎች ናቸው።

እነዚህ አፈላላጊዎች ከተመሳሳይ መንደር ስለሚመጡ የሴቶቹን የቤተሰብ ሁኔታ ያውቃሉ። ብዙ ጊዜም ወንዶቹን ትዳር ፈላጊዎችም ያውቋቸዋል።

ለዚህ አገልግሎት ምን ያህል እንደሚያስከፍሉ የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ "ምሥጢር ነው" በማለት ለመናገር ፈቃደኛ ባይሆኑም ከሁለቱም ተጋቢዎች የሚገኘው መረጃ ሐሰት ከሆነ ለደንበኞቻቸው ገንዘባቸው እንደሚመልሱ ተናግረዋል።

"ደንበኞቻችን ከሚነግሩን 90 በመቶው እውነት ነው" ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ አንድ መጥፎ አጋጣሚ ሌላውን እንደሚበክል ገልጸዋል።

ግለሰቡ ጨምረውም "ከአካባቢው ፖሊስ ጋር በመደበኛነት እንነጋገራለን፤ ትዳር አፈላላጊው ተቋም በማጭበርበር ወንጀል ወስጥ ተሳትፎ ከተገኘም በሕግ ተጠያቂ ይሆናል" ብለዋል።

ይህ እንደምንም ብለው የቆጠቡትን ገንዘባቸውን ላጡ ሰዎች ትንሽ መጽናኛ ሆኗል።

ዋንግ "ተቋሙ ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ያስከፍላል ብሎ እንዳላሰበ እንዲሁም የአካባቢው ትዳር አፋላጊ የልጅቷን የኋላ ታሪክ እንዳጠና እና ድርጅቱ ዋስትና እንደሰጠው" ነገር ግን የውሃ አጣጬ ትሆነኛለች ብሎ ያሰባት ሴት መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን ይናገራል።

እዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ በመግባቱም ራሱን ይወቅሳል። "ለእንዲህ ዓይነት ፈጣን ጋብቻ የሚስማሙት ችግር ያለባቸው ሴቶች ብቻ ናቸው" ይላል።

ገንዘቡን እንዲያስመልሱለትም የግዌጆው ፖሊስን ደጅ እየጠና ነው። ባለሥልጣናት እንዲህ ዓይነት ወንጀሎችን እንዲከላከሉ ለማሳሰብም ቤይጂንግ ድረስ ሄዷል።

የሕግ ባለሙያው ፋን ቢንጌ "እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ክስ ለመመሥረት አስቸጋሪ ነው" ይላሉ።

የቻይና ሕግ እንዲህ ዓይነት የትዳር ማጭበርበርን የተመለከተ የወንጀል ሕግ የለውም። በመሆኑም ክስ ለመመሥረት ተጎጂው የአጋሩ ዓላማ ገንዘብ መውሰድ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎችን ማቅረብ አለበት።

"በያዝኳቸው ጉዳዮች፣ ተጠርጣሪዎች እውነተኛ ፍላጎታቸው ትዳር መሥርተው፣ ጥሩ ሕይወት መኖር እንደነበር፤ ነገር ግን አለመስማማታቸውን፣ ግጭቶች እንደነበሩ እና ግንኙነቱን ለማቋረጥ መወሰናቸውን በመጥቀስ ይከራከራሉ" ይላሉ። "የፍቅር ግንኙነት ጉዳይ ላይ የሚነሱ ክሶች ውድቅ ማድረግ አስቸጋሪ ነው" ሲሉም አክለዋል።

በርካታ የትዳር አጋር አፋላጊዎች ብዙውን ጊዜ የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ ከሰበሰቡ በኋላ ቢሯቸውን ስለሚዘጉ ተጎጂዎች ገንዘባቸውን መልሰው እንዲያገኙ ማድረግም አስቸጋሪ ነው።

ዋንግ የተወሰነ ገንዘቡን ማስመለስ ቢችልም፤ ሁሉም ተጎጂዎች ግን ይህን ማድረግ አልቻሉም።

"በዚህ ሁኔታ ውስጥ ካለፍኩ በኋላ ድጋሚ ትዳር ላማትር እችል እንደሆነ አላውቅም። የምትሆነኝን ሴት ለማግኘት ከብዶኛል፤ አሁን ደግሞ ብዙ ገንዘብ ነው ያወጣሁት። ትዳር ለመመሥረት ማሰብ አልፈልግም" ብሏል።

የዋንግ እና በአፓርታማው ውስጥ ያሉ ወንዶች ሕይወትም ግራ የተጋባ ይመስላል።

"ሁለት ዓመት ወስዶብኛል፤ አሁንም መቼ ልፈታት እንደምችል አላውቅም። ወደ መደበኛ ሕይወቴ መቼ ልመለስ እንደምችልም አላውቅም። ማብቂያ እንደሌለው ነው የሚሰማኝ" ብሏል ዋንግ በሚሟገትባቸው ሕጋዊ ሰነዶቹ ተከቦ።