ሳዑዲ ውስጥ በኢትዮጵያዊያን መካከል ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ ከ100 በላይ ሰዎች መያዛቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Embassy in Riyadh
ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ቀጥታ ሥርጭት ላይ ተፈጽሟል በተባለው ግድያ የተጠረጠረ ግለሰብ እና "አምስት ግብረ አበሮቹ" በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።
ኤምባሲው፣ ይህንን ድርጊት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "ያሠራጩ እና ያራገቡ ከ100 በላይ" ሰዎችን መያዛቸውን ገልጿል።
በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል "የእርስ በርስ ግጭት እና የግድያ ወንጀል" ሲፈጸም እና "በማኅበራዊ ሚዲያ ሲሠራጭ" እንደነበር አስታውሷል። ድርጊቱን "የአገራችንን ባህል እና እሴት የማይወክል አፀያፊ ተግባር" ሲል ጠርቶታል።
ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በሳዑዲ አረቢያ እና የመን ድንበር ላይ የሚገኙ ናቸው የተባሉ ኢትዮጵያውያን፣ በቲክ ቶክ የቀጥታ ሥርጭት ላይ ፈጽመውታል የተባለው ግድያ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ይህንን ተከትሎ ኤምባሲው ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ "አካባቢን መሠረት ያደረገ ጎራ በመፍጠር እርስ በርስ እየተጋጩ" የሚገኙት ኢትዮጵያውያን "በኢመደበኛ መንገድ" ወደ ሳዑዲ አረቢያ የገቡ እና "በበረሃ ገጠራማ አካባቢዎች የመሸጉ" እንደሆኑ አስታውቆ ነበር።
በዛሬው መግለጫውም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሠራጨውን "የግድያ ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ ከአምስት ግብረ አበሮቹ ጋር" በሳዑዲ የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጿል።
"በተጨማሪም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጉዳዩን በማሠራጨት እና በማራገብ ተጠርጣሪ የነበሩ ከ100 በላይ ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር በማዋል ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል" ሲል የተያዙት ሰዎችን ብዛት አመልክቷል።
እንደ ኤምባሲው ገለጻ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት "ከማኅበረሰቡ እና ከሳዑዲ መንግሥት የፀጥታ ተቋማት ጋር በተደረገ ክትትል" እንደሆነ አስታውቋል። ኤምባሲው እና ማኅበረሰቡ ያቀረቧቸው መረጃዎችም ለተጠርጣሪዎቹ መያዝ መነሻ እንደሆኑ ጠቅሷል።
ኤምባሲው "ከሳዑዲ አረቢያ የፀጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ" እየሠራ መሆኑን ገልጿል። "በወንጀል የተሳተፉ ግለሰቦችን በተመለከተ ማንኛውም መረጃ ያለው አካል ለኤምባሲው እንዲያሳውቅም" ጠይቋል።
ኢትዮጵያውያን ዜጎች "ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ከማሠራጨት" እንዲቆጠቡ ያሳሰበው ኤምባሲው፣ "የአገሪቱን ሕግ እና ደንቦች በማክበር የራሳቸውን ሰላም እንዲሁም የማኅበረሰቡን ክብር እና አንድነት እንዲጠበቁ" ጥሪ አቅርቧል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መታየቱ የተገለጸው እና በበርካቶች ዘንድ በአሰቃቂነቱ የተገለጸውን ድርጊት ብዙ ሰዎች ሲያወግዙት እና ፈጻሚዎቹ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።















