ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ለ25 ዓመታት ያሰሯቸው የትግል ጓዶቻቸው የት ናቸው? ጥያቄያቸውስ ምን ነበር?

የፎቶው ባለመብት, Petros Tesfagiorgis
ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነች ጀምሮ እየመሯት የሚገኙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የፖለቲካ ለውጦችን እንዲያካሂዱ በይፋ ጥያቄ ያቀረቡት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በቁጥጥር ስር አውለዋል ደብዛቸው ከጠፋ 25 ዓመታት ተቆጥረዋል።
ቡድን 15 (ጂ15) የሚባሉት ባለሥልጣናት በነጻነት ትግሉ እና ከዚያም በኋላም በተለያዩ ከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ላይ የነቡ ሲሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲደረግ በግልጽ ከጠየቁ በኋላ መስከረም 8/1994 ዓ.ም. ለእስር ተዳርገ አስካሁን ያሉበት አይታወቅም።
በነጻነት ትግሉ እና በኤርትራ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ባለስልጣናቱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምርጫ እንዲያካሄዱ፣ አገሪቱም በሕገ መንግሥት እንድትተዳደር የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈው በይፋ አሠራጭተው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ለውጥ እንዲያደርጉ በደብዳቤ ጥያቄ ካቀረቡት 15 ባለሥልጣናት መካከል 11ዱ በኤርትራ የፀጥታ ኃይሎች ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ አራቱ መስፍን ሓጎስ፣ ኣድሓኖም ገብረማርያም፣ ኃይለ መንቀርዮስ እና መሓመድ ብርሃን ሳይያዙ ቀርተው በስደት ላይ ይገኛሉ።
ለእስር የተዳረጉት እነዚህ ባለሥልጣናት ክስ ሳይቀርብባቸው፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ፣ የት እንዳሉ ሳይታወቅ እነሆ 25 ዓመት ሞላቸው።
በእስር ላይ የሚገኙት ባለሥልጣናት ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ምንጮች ከሚወጡ መረጃዎች በስተቀር ምንም ዓይነት አስተማማኝ ነገር የለም።
የኤርትራ መንግሥት ግን ታሳሪዎቹ በድንበር ይገባኛል ምክንያት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ባካሄደበት ጊዜ የአገሪቱን ነፃነት እና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን ፈጽመዋል፣ ከህወሓት መሪዎች ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል በሚል ይፋዊ ያልሆነ "የአገር ክህደት" ክስ ያርብባቸዋል።
የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናቱ በተያዙ ማግስት ባወጣው መግለጫ፣ "በአገሪቱ ሉዓላዊነት፣ ፀጥታ እና ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ ከባድ ወንጀሎችን ለማስቆም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን" ገልጾ ነበር።
ነገር ግን ግለሰቦቹ እስከዛሬ ለፍርድ ሳይቀርቡ፣ ዝርዝር ክሳቸው በይፋ ሳይነገር እና መልስ የመስጠት መብት ሳያገኙ ቆይተው ደብዛቸው ከጠፋ ሩብ ክፍለ ዘመን ሀናቸው።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ያለመደበኛ ክስ እና የችሎት ሂደት ለአስርታት የተፈጸመውን እስር በተደጋጋሚ ያወገዙ ሲሆን፣ ታሳሪዎቹ "የህሊና እስረኞች" መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ከ25 ዓመታት በኋላ አሁንም መልስ ያላገኘው ዋነኛው ጥያቄ ግን "እነዚህ ሰዎች የት ናቸው? ምን ደረሰባቸው? እና ለምን ወደ ፍርድ ቤት አልቀረቡም?" የሚለውን ነው።
ቢቢሲ እነዚህ ባለሥልጣናት የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ ከኤርትራ መንግሥት መረጃ ለማኘት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ ይገኛል።
ጥያቄያቸው ምን ነበር?
በመስከረም 1994 ዓ.ም. የተሠራጨው የ15ቱ ቡድን አባላት ግልጽ ደብዳቤ ዋና ዋና ጥያቄዎች ኤርትራ በሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና ዲሞክራሲያዊ መንገድ ከፖለቲካዊ ቀውሱ እንድትወጣ ጥሪ የሚያቀርብ እንደነበር ያሳያል።
ደብዳቤው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ውይይት እንዲካሄድ፣ የሕግ የበላይነት እና ፍትህ በአገሪቱ እንዲሰፍን እንዲሁም የተሳሰተውን አቅጣጫ ማረምን እና መፍትሄ ለማግኘት ያለመ ነበር።
ከነፃነት በኋላ ሥልጣን ቀስ በቀስ በጥቂቶች እጅ ውስጥ እየገባ መምጣቱ፣ የጋራ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እየቀረ መቅረቱ፣ ተጠያቂነት እና ተቋማዊ አሠራርን እየተዳከሙ መምጣቱ የሚያትተው ደብዳቤ "አገሪቱ በሕገ መንግሥት፣ በሕግ፣ በተቋማት እና በሕዝብ ተሳትፎ መመራት" እንዳለባት ጠይቆ ነበር።
በተጨማሪም የተረቀቀው ኤርትራ ሕገ መንግሥት ተግባራዊ መሆን እንዳለበት እና የመንግሥት ሥልጣን በተለያዩ የሕግ ተቋማት መገደብ እና ቁጥጥር ሊኖርበት እንደሚገባ ይጠይቃል።
በተለይም ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች በአንድ ሰው ወይም በጥቂት ሰዎች ሳይሆን በጋራ ምክክር እና በሕግ ተቋማት እንዲወሰኑ፣ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን እንዲመሰረት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ እንዲጸድቅ እና ምርጫ እንዲካሄድ የሚሉ ቁልፍ ጥያቄዎችም ይገኙበታል።
እንዲሁም በፕሬዝዳንቱ የተቋቋመው ልዩ ፍርድ ቤት እና ልዩ የምርመራ ኮሚቴ እንዲፈርስ፡ የዳኝነት አካላት ከአስፈፃሚው አካል ነጻ እንዲሆኑ፣ የፕሬስ፣ የመናገር እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ዋስትና እንዲያገኝ ጠይቀው ነበር።
በቡድን 15 አባላት በተሠራጨው ግልጽ ደብዳቤ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል የተባለው ተረቅቆ ወደ ተግባር ያልተቀየረው የኤርትራ ሕገ መንግሥት የጥያቄዎቹ ማዕከላዊ ነጥብ ነው። በዚህም አስካሁን በኤርትራ ተቃዋሚ ፓርቲ እና ነጻ መገናኛ ብዙኃን ካለመኖራቸው በተጨማሪ ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነች ጊዜ አንስቶ ምርጫ አድርጋ አታውቅም።
'ቡድን 15' እነማን ናቸው?
1. ማሐሙድ አሕመድ ሸሪፎ፡ በነጻነት ትግል ወቅት የህዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) የፖሊት ቢሮ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ ከነፃነት በኋላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር [እንደ ምክትል ፕሬዝዳንት የሚቈጠር]፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። በተጨማሪም የትጥቅ ትግሉን የመራው ህግሓኤ ወደ ፖለቲካዊ ፓርቲነት ተለውጦ ህዝባዊ ግንባር ዴሞክራሲ እና ለፍትህ (ህግዴፍ) ሲመሠረት መሥራች እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበረ።
2. ኃይለ ወልደትንሳኤ፡ የሕዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ እና የግንባሩ ፖለቲካ ቢሮ፣ ከነጻነት በኋላ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የገንዘብ ሚኒስትር ነበሩ።
3. ጴጥሮስ ሰሎሞን፡ በትጥቅ እንቅስቃሴው ጊዜ የደኅንነት ኃላፊ፤ የሕዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የፖለቲካ ቢሮ አባል እንዲሁም ከነጻነት በኋላ የባሕር ኃብት ሚኒስትር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የመከላከያ ሚኒስትር ነበሩ።
4. ጀነራል ዑቕበ አብርሃ፡ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር እንዲሁም የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል።
5. ባራኺ ገብረሥላሤ፡ የሕዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) እና የህዝባዊ ግንባር ዴሞክራሲ እና ለፍትህ (ህግዴፍ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ ሲሆን ከነጻነት በኋላ የትምህርት፣ የማስታወቂያ እና ባህል ሚኒስትር እንዲሁም በጀርመን የኤርትራ አምባሳደር ነበሩ።
6. ሜጀር ጀነራል ብርሃነ ገብረእግዝአብሄር፡ በነጻነት ትግሉ ወቅት የህዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) የፖለቲካ ቢሮ አባል እና ከነጻነት በኋላ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ የሜጀር ጄነራልነት ማዕረግ የነበራቸው ሲሆን፤ የኤርትራ ተጠባባቂ ሠራዊት ዋና አዛዥ ነበሩ።

7. ብርጋዴር ጀነራል እስጢፋኖስ ስዩም፡ የህግሓኤ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ ከነጻነት በኋላ በሠራዊቱ ውስጥ የብርጋዲዬር ጀነራልነት ማዕረግ የነበራቸው ሲሆን፤ እስከታሰሩበት ጊዜ ድረስ ደግሞ የአገር ውስጥ ገቢ አገልግሎት ኃላፊ ነበሩ።
8. ጀርማኖ ናቲ፡ የህዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፣ እንዲሁም የጋሽ ባርካ ዞን ኣስተዳደር ነበሩ።
9. ሳልሕ እድሪስ ኬክያ ፡ የህዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ የትራንስፖርት እና ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር እንዲሁም የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ።
10. ሓምድ ሕምድ፡ የህዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) እና ህዝባዊ ግንባር ዴሞክራሲ እና ለፍትህ (ህግዴፍ) ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ፖለቲካ ቢሮ አባል፣ ከነጻነት በኋላ በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የመካከለኛው ምሥራቅ ክፍል ኃላፊ እንዲሆም በሱዳን የኤርትራ አምባሳደር ነበሩ።
11. አስቴር ፍስሐጽዮን፡ የህዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና በሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩ።
እነዚህ የቀድሞ የህዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) እና ከፍተኛ የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በእስር ላይ ይገኛሉ።
ከከፍተኛ ባለሥልጣናቱ በተጨማሪም ያቀረቡትን ጥያቄ የሚደግፉ ሌሎች ሰዎች፣ ጋዜጠኞች እና በርካታ የህዝባዊ ግንባር ሓርንት ኤርትራ (ህግሓኤ) አባላት እና ካድሬዎችም በወቅቱ የታሰሩ ሲሆን እነሱም አስካሁን የት እንዳሉ አይታወቅም።
እነዚህ ከመስከረም 1994 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት የኤርትራ ነጻነት ትግል እንቅስቃሴ አባላት እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መጀመሪያ ላይ እምባትካላ በሚባል እስር ቤት ታስረው እንደነበር እና ከጥቂት ወራት በኋላ ግን 'ዒራዒሮ' ወደ ተባለ እጅግ አስከፊ እስርቤት መዛወራቸው ይነገራል።
የለውጥ ጥያቄውን በግልጽ ደብዳቤ ካቀረቡት የቡድን 15 አባላት መካከል አሥራ አንዱ ተይዘው ለሩብ ክፍለ ዘመን ያሉበት ሳይታወቅ ሲቆዩ አራቱ መስፍን ሓጎስ፣ አድሓኖም ገብረማርያም፣ መሐመድ ብርሃን እና ኃይሌ መንቆሪዮስ ደግሞ ለ25 ዓመታት በተለያዩ አገራት በስደት ላይ ይገኛሉ።
የኤርትራ መንግሥት ምን ይላል?
ለውጥ ጠያቂዎቹ የቡድን 15 አባላት ግልጽ ደብዳቤያቸውን ይፋ አድርገው ለእስር ከተዳረጉ ከአንድ ዓመት በላይ በኋላ በጥር ወር 1995 ዓ.ም. የኤርትራ ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ታሳሪዎቹን "ከዳተኞች እና ከፋፋዮች" ሲል ገልጿቸው ነበር።
በተጨማሪም ታሳሪዎቹ "ፕሬዝዳንቱን በኃይል ከሥልጣን ለማስወገድ ሞክረዋል" በማለት የከሰሳቸው ምክር ቤቱ ከዚያ ጊዜ በኋላ መደበኛ ስብሰባውን አድርጐ አያወቅም።
የለውጡ ጥያቄ ዋነኛ ዒላማ የነበሩት እና አገሪቱን በፈላጭ ቆራጭነት ለ35 ዓመታት እየመሩ ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ስለተነሳባቸው ጥያቅም ሆነ ለሩብ ክፍለ ዘመን በእስር ስለሚማቅቁት የትግል አጋሮቻቸው በየትኛውም አጋጣሚ ተናግረው አያውቁም።
ከ17 ዓመታት በፊት አንድ የኳታር የአረብኛ ጋዜጠኛ ስለእነዚህ እስረኞች የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ፤ "ስለጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም፤ ይህ ጉዳይ ቢረሳ ይበጃል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በተመሳሳይም ይኸው ጥያቄ በአልጀዚራ እንግሊዝኛ ጋዜጠኛ ለፕሬዝዳንቱ ቀርቦ "የታሰሩ አልነበሩም፣ የታሰሩ የሉም፤ የተሳሳተ መረጃ ነው" ብለው ፈርጠም ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።















