ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ከ2026 መጨረሻ አንስቶ ለእስራኤል ድጋፍ ማድረግ እንደምታቆም ትራምፕ ተናገሩ
ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ስምምነት የፈጸሙት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ ከአውሮፓውያኑ 2026 መጨረሻ አንስቶ ለእስራኤል የገንዘብ ድጋፍ መስጠት እንደምታቆም አስታወቁ።
አሜሪካ በየዓመቱ ለእስራኤል የምታቀርበውን የአራት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንድታቆም ስምምነት ላይ የተደረሰው "ከወራት በፊት" መሆኑን ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ከፎክስ ኒውስ ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለመጠይቅ ተናግረዋል።
ትራምፕ፣ "በዚህ ዓመት መጨረሻ ለእስራኤል ክፍያ እንደማንፈጽም ተስማምተናል" ብለዋል። "አሁን፣ እስራኤል ድጋፍ ከፈለገች እናግዛታለን" ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት ስለ የትኛውን ፈንድ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ይሁን እንጂ በየዓመቱ ለእስራኤል 3.8 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ እንዲሰጥ የሚያደርገው የመግባቢያ ስምምነት በአውሮፓውያኑ 2028 መጨረሻ ያበቃል።
ቢቢሲ ማብራሪያ ለማግኘት ለዋይት ሐውስ ጥያቄ አቅርቧል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።
ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ከእንግዲህ እስራኤል የአሜሪካን የገንዘብ ድጋፍ አትፈልግም ብለዋል።
"ለእስራኤል ክፍያ መፈጸምን በተመለከተ፣ እኔ እና ቢቢ ኔታንያሁ ለእስራኤል በዓመት አራት ቢሊዮን ዶላር የሚሰጥበትን አሰራር ለማቆም ከወራት በፊት ስምምነት ፈጽመናል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ ዴሞክራቶች ለአሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ ሪፐብሊካኖችን ለማጥቃት "በመወያያ አጀንዳነት" ተጠቅመውታል ሲሉ ከስሰዋል።
አስፈላጊ ሲሆን እስራኤል ከአሜሪካ የጦር መሣሪያዎችን መግዛት እንደምትችልም ትራምፕ ጠቁመዋል። የእስራኤልን ጦር ለመደገፍ ምን አይነት አዲስ የግዢ ወይም የኢንቨስትመንት ስምምነት ምን እንደሚደረስ ግልጽ አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ግንቦት ላይ አሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ እስራኤል በየዓመቱ ከአሜሪካ የምታገኘው 3.8 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ቀስ በቀስ በመቀነስ "ወደ ዜሮ ማውረድ" እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።
"አሁን እንጀምረውና በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ እናጠናቅቀው፤ ነገር ግን አሁን መጀመር እፈልጋለሁ። ቀጣዩን ኮንግረስ መጠበቅ አልፈልግም" ብለው ነበር።
እስራኤል ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ትልቋ የአሜሪካ የውጭ እርዳታ ተቀባይ አገር ናት።
የአሜሪካ ኮንግረስ ባለፈው ዓመት ያወጣው ሪፖርት፣ ለእስራኤል ወጪ የተደረገውን ገንዘብ መጠን 174 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ያስረዳል። ይህ ቁጥር የተቀመጠው የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ ሳይደረግ ነው።
የአሜሪካና የእስራኤል ግንኙነት አሁንም ድረስ በሪፐብሊካን እና ዴሞክራት ፓርቲዎች ድጋፍ የሚሰጠው ቢሆንም፣ በመስከረም 2016 ዓ.ም. የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ በዴሞክራቶች ዘንድ ያለው ድጋፍ እየቀነሰ መጥቷል።
ሐምሌ ላይ የሪፐብሊካኑ የሕግ አውጪ ቶማስ ማሲ ለእስራኤል የሚሰጠው የ3.3 ቢሊዮን ዶላር የደኀንነት ድጋፍ እንዲቀንስ የቅበው ረቂቅ ሕግ ድምፅ እንዲሰጥበት ምክር ቤቱን አስገድደው ነበር።
የምክር ቤቱ አባላት ከሆኑ 103 ዴሞክራቶች ድጋፍም ያገኙ ሲሆን ማሻሻያውን የደገፉ ብቸኛው ሪፐብሊካንም ራሳቸው ቶማስ ማሲ ነበሩ። ይሁን እንጂ ውሳኔው በ314 ለ 104 ድምፅ ውድቅ ተደርጓል።
ከአሜሪካ መራጮች መካከል 48 በመቶው አሜሪካ ለእስራኤልን የበዛ ድጋፍ ታደርጋለች ብለው እንደሚያምኑ ኩዊኒፒአክ ዩኒቨርሲቲ መስከረም ላይ ያደረገው የሕዝብ አስተያየት ጥናት አሳይቷል። ይህ ቁጥር በአውሮፓውያኑ በ2017 ከነበረበት 16 በመቶ ከፍ ያለ ነው።
ይህንን ምልከታ የሚጋሩ በዴሞክራቶች ብዛት 67 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ በዚህ ሃሳብ የሚስማሙ ሪፐብሊካኖች ቁጥር 17 በመቶ ነው።