ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኦሮሚያ ክልል ሽርካ ወረዳ "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" እና "ኢመደበኛ ታጣቂዎች" 48 ሰዎችን መግደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ
በኦሮሚያ ክልል ሽርካ ወረዳ "በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" እና "ኢመደበኛ ታጣቂዎች" በተፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች 48 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። ኮሚሽኑ፣ መንግሥት በአካባቢው ስለተፈጸመው ጥቃት "ፈጣን ገለልተኛ እና ውጤታማ ምርመራ" እንዲያደርግ ጠይቋል።
ኢሰመኮ፣ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በአዲሱ የኦሮሚያ ክልል አወቃቀር በምሥራቅ ዞን ሥር በሚገኘው ሽርካ ወረዳ ቢርቦና ጮሌ ቀበሌ የተፈጸመውን ጥቃት "ያስከተለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን" በተመለከተ ምርመራ ማከናወኑን ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 24/2019 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ጥቃቱን የተመለከተው ምርመራ የተደረገ፣ በአካባቢው በአካል ተገኝቶ መረጃ በማሰባሰብ፣ በመስክ ምልከታ እና "የዲጂታል የምርመራ" እንደሆነ ኮሚሽኑ አስታውቋል። የኮሚሽኑ መርማሪዎች በስፍራው ተገኝተው ተጎጂዎች፣ የዐይን እማኞች እና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጨምሮ የተለያዩ ሰዎችን እንዳነጋገሩ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ኢሰመኮ፣ ጥቅምት 14 ዕለት ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂ ያደረገው በክልሉ የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" ነው። በዕለቱ ታጣቂ ቡድኑ ንጋት 12፡30 ላይ ወደ ቦርቦና ጮሌ ቀበሌ "በአራት አቅጣጫ በመግባት" ጥቃት ማድረሱን ኮሚሽኑ ገልጿል።
የኢሰመኮ መግለጫ እንደሚያስረዳው በታጣቂ ቡድኑ ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት ከተገደሉት 41 ሰዎች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት "በቀበሌ ደረጃ የተደራጁ ጸጥታ አካላት" ናቸው።
መግለጫው፥ "[ታጣቂ ቡድኑ] በፈጸመው ጥቃት 23 በቀበሌ ደረጃ የተደራጁ ጸጥታ አካላት፥ 5 የሚሊሻ አባላት እንዲሁም 13 ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለማረጋገጥ ተችሏል" ብሏል። "በተጨማሪም በኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በተፈጸመ ጥቃት በ20 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል" በሰዎች ላይ የደረሰውን ተጨማሪ ጉዳት አስፍሯል።
ቢቢሲ ከዚህ ቀደም ያነጋራቸው የዐይን እማኞች፣ የተጎጂዎች ቤተሰቦች እና የአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ በዕለቱ የተገደሉት "46 ሰዎች" መሆናቸውን ገልጸው ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ባወጣችው መግለጫ በሽርካ ወረዳ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ብዛት 46 እንደሆነ አስታውቃለች። አጎራባች በሆነው መርቲ ወረዳ በደረሰ ጥቃት 14 ሰዎች መገደላቸውን የገለጸችው ቤተ ክርስቲያኗ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ በድምሩ 60 ምዕመኖቿ መሞታቸውን አመልክታለች።
በዚህ ጥቃት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች "የክርስትና እምነት ተከታዮች" መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከ40 በላይ ሰዎች ከሞቱበት ከዚህ ጥቃት በኋላ በዚያው ዕለት "የእስልምና እምነት ተከታይ" የሆኑ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ሁለት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተነግረው ነበር።
ኢሰመኮ ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ "በአካባቢው በታጠቁ ኢመደበኛ በሆኑ ታጣቂ ግለሰቦች ሰባት ሲቪል ሰዎች የተገደሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል" ሲል በቀበሌው በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራ በቀበሌው "በአካባቢው ግለሰቦች ኢመደበኛ በሆነ መንገድ ታጥቀው በስፋት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን" እንዳረጋጠ በመግለጫው ጠቅሷል።
እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት፣ "21 መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል" እንዲሁም "247 ቤተሰቦች ከአካባቢው" ተፈናቅለዋል።
የኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ ስለጥቃቱ በሰጠው መግለጫ ለነዋሪዎች ግድያ ተጠያቂ ያደረገው "ሸኔ" ሲል የገለጸውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነው። በተጨማሪም በአካባቢው "የፋኖ" አባላት እንደሚንቀሳቀሱ የክልሉ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ተገግረዋል።
ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ 73 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የገለጹት ኃይሉ፣ የተያዙት ተጠርጣሪዎች "የፋኖ እና ሸኔ" አባላት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጥቃቱን ፈጽሟል በሚል የተከሰሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ውንጀላውን በተመለከተ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም። ይሁን እንጂ ቡድኑ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለኅልውና የተባለው ጥምረት ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 17 ቀን ባወጣው መግለጫ፣ ቀድሞው አርሲ ዞን የሚታየው ጥቃት "በአገዛዙ ቀጥተኛ ድጋፍ እና ባለቤትነት የሚፈጸም ነው" ሲል መንግሥትን ከስሷል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በመግለጫው፣ በዞኑ "በአሰኮ፣ በአንቆሎ ዋቤ፣ በጉና እና በመርቲ ወረዳዎች በተደጋጋሚ ጥቃቶች መድረሳቸውን አስታውሷል። ኮሚሽኑ፣ "መንግሥት ጥቃቶቹን ለመከላከል፣ የሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ እና ጥቃት ፈጻሚዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ" ማሳሰቡን ገልጿል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ "በነዋሪዎች ላይ የደረሱት ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶች፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል እጅግ አሳሳቢ" መሆናቸውን ገልጸዋል። "መንግሥት በጥቃቱ የተጎዱና ተመሳሳይ የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አከባቢዎች ሁሉ በቂና ውጤታማ የሆነ ጥበቃ ሊያደርግ" እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
"ለሚከሰቱ ስጋቶች ፈጣን ምላሽ በመስጠት የነዋሪዎች የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና፣ ንብረት የመጠበቅ ኃላፊነቱን" መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ኮሚሽነር ብርሃኑ አክለውም፣ መንግሥት አሁን ለተፈጸመው ጥቃት "ፈጣን ገለልተኛ እና ውጤታማ ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ" እንደሚገባ መናገራቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም "ለሟቾች ቤተሰቦች እና ለተገጂዎች አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያደርግ" እንዲሁም "የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ" የሚያስችሉ "አፋጣኝ እርምጃዎችን" ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምሥራቅ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እና ጊዜያት የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመከተ የሚያደርገውን ሥልታዊ ምርመራ እያጠናቀቀ መሆኑን የገለጸው ኢሰመኮ፣ ሪፖርቱን ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።