ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አረብ ኤምሬትስ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ሐሰን ከሰሱ
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በአገራቸው ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባች፣ የፌዴራል መንግሥቱን በመቃወም የክልል አስተዳደሮችን እየደገፈች እና የሶማሊያን አንድነት እና ሉዓላዊነት የሚጎዱ ፖሊሲዎችን እየተከተለች ነው ሲሉ ከሰሱ።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለቀረበባት ክስ በፕሬዝዳንቷ አማካሪ በኩል በሰጠችው ምላሽ ፕሬዝዳንቱ ሞሐሙድ የሚመሯት ሶማሊያ የፖለቲካ ሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ እየገባች መሆኗን እና ፕሬዝዳንቱ የግል ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን በማንጸባረቅ ክስ አቅርበዋል በሚል አጣጥላዋለች።
ፕሬዝዳንቱ ለሕዝባቸው ባደረጉት በጠንካራ ቃላት በተሞላ ንግግራቸው፣ ኤምሬትስ የፌዴራል መንግሥቱን ፈቃድ ሳታገኝ ከአገሪቱ ክልሎች ባለሥልጣናት ጋር ስምምነቶችን በመፈራረም ለዓመታት የተገነባውን የዲፕሎማሲ መተማመን አፍርሳለች ብለዋል።
የባሕረ ሰላጤዋን አገር በፖለቲካዊ፣ በወታደራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ጣልቃ ገብነት የከሰሱት ፕሬዝዳንት ሞሐሙድ፣ ይህም የሶማሊያ መንግሥት ከአል ሸባብ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ጋር በሚዋጋበት ወቅት የአገሪቱን የፀጥታ ተቋማትን አዳክሟል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኤምሬትስ በበርበራ፣ በቦሳሶ እና በኪስማዮ ወደቦች ዙሪያ ስምምነቶችን በመፈራረም፣ ወታደራዊ ተቋማትን በማቋቋም እና ከሶማሊያ ብሔራዊ ጦር መዋቅር ውጭ የሚንቀሳቀሱ የፀጥታ ኃይሎችን በመደገፍም ከስሰዋታል።
እንዲሁም ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ከሶማሊያ በመነጠል ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ዕውቅና እንድታገኝ አረብ ኤምሬትስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች መሆኑን አመለክተዋል። ባለፈው ዓመት እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና ስትሰጥ ኤምሬትስ እርምጃውን ለመቃወም ፈቃደኛ አለመሆኗን በማስረጃነት ጠቅሰዋል።
በሶማሊያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል ያለው አለመግባባት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የሶማሊያ መንግሥት ከዩኤኢ ጋር የነበሩትን የደኅንነት፣ የመከላከያ እና የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነቶችን መሰረዙ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ሶማሊያ የኤምሬትስ ወታደራዊ እና የጭነት አውሮፕላኖች በአየር ክልሏ እንዳይበሩ ከልክላለች፤ እነዚህ እርምጃዎችም የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ አስፈላጊ በመሆናቸው የተወሰዱ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል።
ይህንን እርምጃ ተከትሎ የሶማሊላንድ፣ የፑንትላንድ እና የጁባላንድ ባለሥልጣናት ሞቃዲሾ ከአረብ ኤምሬትስ ጋር ያሉ ስምምነቶችን ለመሰረዝ የወሰደችውን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ የራሳቸውን መንገድ እንደሚከተሉ አስታውቀዋል።
ነገር ግን፣ ይህ ውሳኔ ከተላለፈ ከ10 ወራት በኋላም ኤምሬትስ "የሶማሊያን ፀጥታ እና መረጋጋት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ቡድኖች ጋር ሕገ-ወጥ ግንኙነት መቀጠሏን" በመግለጽ ሶማሊያ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደምትወስድ አስጠንቅቀዋል።
ሆኖም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የምታከብር ከሆነ በአገራቱ መካከል ውይይት ሊጀመር እንደሚችል በመግለጽ ግንኙነቱን ለማሻሻል በሩ ክፍት እንደሆነም ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንት ሞሐሙድ በንግግራቸው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከአገራቸው ባሻገር "በሊቢያ እና በየመን ውስጥ ለተፈጠሩ ክፍፍሎች አስተዋጽኦ አድርጋለች" በማለት፣ ተመሳሳይ ፖሊሲዎች "በሱዳን እና በሶማሊያም እየተተገበሩ ነው" ብለዋል።
ኤምሬትስ አንዳንድ የሶማሊያ ክልል አስተዳደሮች የፌዴራል መንግሥቱን እንዲቃወሙ ለማበረታታት ፖለቲካዊ እና የገንዘብ ድጋፍ እየሰጠች ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ለሶማሊላንድ፣ ለፑንትላንድ እና ለጁባላንድ መሪዎች በቀጥታ ላቀረቡት ጥሪ በማቅረብ፣ ሶማሊያውያን የፖለቲካ ልዩነቶችን በመወያየት እንዲፈቱ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ንግግር ያደረጉት በሶማሊያ የፌዴራል መንግሥት እና በአገሪቱ የግዛት አስተዳደሮች መካከል በፖለቲካ ሥልጣን፣ በፀጥታ እና በስትራቴጂካዊ መሠረተ ልማቶች ቁጥጥር ዙሪያ ውዝግብ በተባባሰበት ጊዜ ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ ቦታ ላይ ከምትገኘው ሶማሊያ ጋር የወደቦች ልማት ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ከበርካታ የሶማሊያ ክልሎች ጋር የቅርብ የንግድና የፀጥታ ግንኙነት አላት።
የኤሚሬትስ ፕሬዝዳንት የዲፕሎማሲ አማካሪ የሆኑት አንዋር ጋርጋሽ፣ አገራቸው የሶማሊያን ሉዓላዊነት በመጣስ በሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ የተሰነዘሩ ክሶችን ተቃውመዋል።
አማካሪው በኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ "ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት" በማለት የጠቀሷቸውን ፕሬዝዳንት ሞሐሙድን "የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ከግል የፖለቲካ ፍላጎታቸው በታች" አስቀምጠዋል ብለዋቸዋል።
ጋርጋሽ በሶማሊያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሥልጣን ሽኩቻዎች አገሪቱን ወደ ቀጣናዊ ውዝግቦች እየጎተቱ መሆኑ እንዳሳዘናቸው በመጥቀስ ኤምሬትስ ከሶማሊያ ሕዝብ ጋር ያላትን ግንኙነት "ከጊዜያዊ የፖለቲካ አለመግባባቶች፣ ከግል ስሌቶች እና ከፖለቲካ ፍላጎቶች የበለጠ ጠንካራ እና ጥልቅ ሆነው ይቀጥላል" ብለዋል።