ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አምስት የአውሮፓ አገራት የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ሊልኩ መሆኑን ይፋ አደረጉ
አምስት የአውሮፓ አገራት የጥገኝነት ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ሊልኩ መሆኑን አስታወቁ።
ጀርመን፣ ዴንማርክ፣ ኦስትሪያ፣ ግሪክ እና ኔዘርላንድስ እአአ በ2027 የሚባረሩ ስደተኞችን መቀበል የሚችሉ ማዕከላትን በሩዋንዳ ይከፍታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኔዘርላንድስ እና የዴንማርክ መንግሥታት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
አገራቱ ተመላሽ ስደተኞችን እንድታስተናግድላቸው ከአፍሪካዊቷ አገር ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ እየሰሩ መሆናቸውን ያስታወቁት መስከረም ወር ላይ ነበር።
ፕሮግራሙ ተግባራዊ የሚሆነው በአገራቱ በሕገ ወጥ መንገድ በሚኖሩ እና እንዲባረሩ በተወሰነባቸው ስደተኞች ላይ መሆኑንም አገራቱ ገልጸዋል። የኔዘርላንድስ መንግሥት ፕሮግራሙ ወደ አገራቸው መመለስ ለማይችሉ ስደተኞች አማራጭ ይሆናል ብሏል።
ስደተኞቹ ከሩዋንዳ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው መኖር ወይም ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚችሉም አገራቱ አስታውቀዋል።
እርምጃው ተግባራዊ የሚሆነው በአገራቱ ለመኖር ያቀረቡት የጥገኝነት ጥያቄ ተቀባይነት ያላገኘ እና በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ስደተኞች ላይ ነው።
የአገራቱ እቅድ ከዚህ ቀደም ዩናይትድ ኪንግደም ጀምራው ከነበረው እና በኋላ ላይ በፍርድ ቤት ከታገደው ፕሮግራም ጋር የሚለያይ ነው።
ዩኬ እአአ በ2024 ስደተኞች ጉዳያቸውን በሦስተኛ አገር ሆነው እንዲከታተሉ ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር ከስምምነት ላይ ደርሳ ነበር።
ሆኖም ስምምነቱ ብዙ ተቃውሞ ካስተናገደ በኋላ የፈረሰ ሲሆን ዩኬም ስምምነቱ በመፍረሱ በሚሊዮን ፓውንድ የሚቆጠር ገንዘብ እንዳትቀጣ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደወሰነላት አይዘነጋም።
አሁን አምስቱ አገራት ይፋ ባደረጉት እቅድ ግን ወደ ሦስተኛ አገር የሚላኩት ስደተኞች በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ውስጥ ለመቆየት የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት ማቅረብ ያልቻሉ ሲሆኑ ጉዳያቸው በሒደት ላይ ያሉ ስደተኞችን አይመለከትም።
አገራቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ የሚመልሱት ያላገቡ ወንዶችን መሆኑንም ገልጸዋል።
የተያዘው እቅድ የሚባረሩ ስደተኞችን ቁጥር ለመጨመር እና ሕገ ወጥ ስደትን ለማስቆም የሚወስዱት ሰፊ እርምጃ አካል ነው ተብሏል።
የአገራቱ እቅድ ይፋ የተደረገው ስደተኞችን የማባረር ሒደት እንዲቀላጠፍ እና አባል አገራት ከአውሮፓ ውጭ የተመላሽ ስደተኞች ማዕከላትን እንዲያቋቁሙ የሚፈቅደው አዲሱ የአውሮፓ ኅብረት የቁጥጥር ደንብ ከጸደቀ በኋላ ነው።
ዩናይትድ ኪንግደም ይህንን ዕቅድ እየተመለከተችው እንደሆነ ገልጻለች።
በአውሮፓ የሚገኙ በርካታ አገራት የሚያካሂዱት ምርጫ እየተቃረበ ሲሆን የፀረ ስደተኞች እንቅስቃሴ እየተስፋፋ ነው።
መንግሥታትም ስደትን መቆጣጠር መቻላቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ጫና እየተደረገባቸው ነው። ተንታኞች እቅዱ የመንግሥታቱን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሆኖም የመብት ተሟጋቾች ስደተኞች ምንም ዓይነት ግንኙነት ወደ ሌላቸው አገር ሲላኩ የመብት ጥሰት ሊያጋጥማቸው ይችላል ሲሉ በእቅዱ ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
በዳኒሽ ሬፊዩጂ ካውንስል የአውሮፓ ኅብረት ዳይሬክተር የሆኑት ሴሊን ሚያስ "ስደተኞቹ የመብት ጥሰት ካጋጠማቸው ምን አማራጭ ይኖራቸዋል? ማንስ ነው ተጠያቂው?" ብለዋል።
ሚያስ ጨምረውም ይህ ኃላፊነት በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ላይ የሚወድቅ ከሆነም በተግባር እንዴት ነው የሰሚራው? ሲሉም ጠይቀዋል።
ሐምሌ ወር ላይ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ተቋም የሆነው 'ዘ ካውንስል ኦፍ ዩሮፕ' የተመላሽ ስደተኞች ማዕከላት የሰብዓዊ መብት አደጋዎችን መደቀኑን ገልጿል።
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በሩዋንዳ ማዕከል የመክፈቱን እቅድ "ቀጣይነትም ሆነ ሰብአዊነት የሌለው" ሲሉ ተችተዋል።
የአምስቱ አገራት መሪዎች በተደጋጋሚ እቅዳቸው የኅብረቱን እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን ያከበረ መሆኑን ገልጸው፤ የፖሊሲው ዋነኛ ዓላማ ስደተኞችን በብዛት ማባረር ሳይሆን ሕገ ወጥ ስደትን መከላከል ነው ብለዋል።
ስደተኞቹ አውሮፓ ለመግባት በሺህዎች የሚቆጠር ዩሮ ለአዘዋዋሪዎች የሚከፍሉት ወደ ሦስተኛ አገር ለመላክ መሆኑን ማወቃቸው አደገኛ ጉዞ እንዳያደርጉ ያስችላል ሲሉም ተከራክረዋል።
ኦስትሪያ እቅዱ የአውሮፓን የጥገኝነት ሥርዓት ለማቃለል እና ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን ለማስቆም ይረዳል ብላለች።
ሩዋንዳ በበኩሏ "ለስደተኞች ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ሕጋዊ እና ክብር ያለው መፍትሔ" ለማቅረብ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች።
ሆኖም ተቺዎች ጥብቅ እርምጃዎች እና ስደተኞችን የማባረር ፕሮግራም ስደትን በዘላቂነት ያስቀራል የሚል እምነት የላቸውም።
አሜሪካም ባለፈው ዓመት እስከ 250 የሚደርሱ ሰዎችን ወደ ሩዋንዳ ለማዛወር በተደረገ ስምምነት መሠረት ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ መላክ ጀምራለች።
ዩኬም እአአ በ2023 ስደተኞችን ወደ ሦስተኛ አገር የመላክ እቅዷ ሕገ ወጥ ተብሎ በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከታገደ በኋላ ፕሮግራሙን ትታለች።
እቅዱ ከተሰረዘ በኋላ ኪጋሊ 63.6 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ጠይቃለች። ሆኖም ከአንድ ወር በፊት ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ዩኬ እንዳትከፍል ወስኖላታል።
በመስከረም ወር ሁለት የአውሮፓ ፓርላማ ሕግ አውጪዎች ዩኬ ልትጠቀምበት የነበሩትን የስደተኛ ማዕከላት እና ሆቴልን ጎብኝተዋል።