ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በባድመ የገጠር ቀበሌ በደረሰ የድሮን ጥቃት ቢያንስ 4 ሰዎች መጎዳታቸው ተገለጸ
በትግራይ ክልል፣ ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ ባድመ አቅራቢያ፣ ከባድመ የገጠር ቀበሌዎች አንዱ በሆነችው ቢያራ በተባለች ቀበሌ ሰኞ ኅዳር 7/ 2019 ዓ. ም. በደረሰ የድሮን ጥቃት ቢያንስ 4 ሰዎች መጎዳታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገለፁ።
ይህ ጥቃት ያጋጠመው በባድመ አቅራቢያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ሰሞኑን እያደረገ ባለው ዉጊያ የተነሳ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀላቸው እየተዘገበ ባለበት ወቅት ነው።
በዚህ የድሮን ጥቃት የተጎዱት ሲቪሎች መሆናቸውን የቢቢሲ ምንጮች ገልፀዋል። በሽራሮ ከተማ ወደሚገኘው ማያሚ ሆስፒታል እና ዓዲ ሃገራይ የጤና ተቋም መወሰዳቸውንም አክለዋል።
የማያሚ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም ዶ/ር ሐጎስ ወልደሰማያት ሁለት የድሮን ጥቃት ሰለባዎችን በሆስፒታሉ ተቀብለው ሕክምና እንዳደረጉላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ጥቃት ዐይኗ ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰባት አንዲት የ37 ዓመት ሴት ወደ ሽረ እንዳሥላሴ ስሁል ሆስፒታል መላኳንም አስረድተዋል።
ሁለተኛው የ22 ዓመት የጥቃቱ ሰለባ ቀላል ጉዳት ስለደረሰበት ሕክምና ተሰጥቶት ወደ ቤቱ መመለሱን ተናግረዋል።
"የነገሩን ፍንጣሪ እንደመታቸው ነው። የነበሩት ብዙ ሰዎች ቢሆኑም የተጎዱት አራት ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ነግረውናል" ብለዋል።
ቢቢሲ ክስተቱን በተመለከተ ከመከላከያ ሠራዊት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ኮሎኔል ቢረሳው ሽፈራው አስተያየት ቢጠይቅም ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።
ጥቃቱን ተከትሎ የሰሜን ምዕራብ ኮማንድ ፖስት ትናንት ማክሰኞ ኅዳር 8 ቀን 2019 ዓ. ም. ባስተላለፈው ትዕዛዝ በዞኑ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ "ከአራት ሰዎች በላይ እንዳይሰባሰቡ" ከልክሏል።
በትግራይ ቴሌቪዥን የተላለፈው የኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ፣ እርምጃው የተወሰደው "በዞኑ ሰላም እና ፀጥታ ለማስፈን" በማለም እንደሆነ ገልጿል።
በዚህም ሽረ ከተማን ጨምሮ በዞኑ ውስጥ ከምሽት 12፡00 ሰዓት ጀምሮ የባጃጅ እና የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ ማድረግ ተከልክሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ለ24 ሰዓት እንዲንቀሳቀሱ ከተፈቀደላቸው አምቡላንሶች ውጪ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከተቀመጠው ሰዓት ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ ኮማንድ ፖስቱ እገዳ ጥሏል።
በአካባቢው በመከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ውጊያዎች እየተደረጉ መሆኑንም ቢቢሲ ያነጋጋራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የባድመ ገጠር አካባቢዎች የማኅበራዊ ጉዳይ አስተባባሪ ወ/ሮ ዳናይት አታላይ፤ ሰኞ ዕለት በተፈፀመው የድሮን ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አስቀድመው በአካባቢው ይደረግ በነበረው ዉጊያ ሕይወታቸውን ለማዳን ተፈናቅለው ወደ ሽራሮ የሄዱ ነዋሪዎች ሲሆኑ ቀለብ ለማምጣት በሚል ወደ ቢያራ ቀበሌ በተመለሱበት ወቅት አደጋው እንደደረሰባቸው አብራርተዋል።
"ወደዚያ የሚሄደው የሚመጣውም አንድ መኪና ነው፤ ነጭ ቅጥቅጥ አይሱዙ ነው። የድሮን ጥቃቱ የደረሰው በመኪናው ላይ ነው" ብለዋል።
አንድ ሴት እና ሦስት ወንዶች እንደተጎዱ እንዲሁም የመኪናው ሹፌር እና ረዳት እንደሚገኙበት አክለዋል።
ውጊያው ከተጀመረ ወዲህ ወደ ሽራሮ የተፈናቀሉ ሰዎች 1ሺህ 233 እንደሚደርሱ ወ/ሮ ዳናይት ተናግረዋል።
የተወሰኑት በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የተቀሩት ደግሞ ከማኅበረሰቡ ጋር ተጠግተው እየኖሩ መሆኑንም አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል "በከባድ መሣሪያ የታገዘ" ግጭት ታካሂዶ እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ግጭቱን ተከትሎ ለድንበር በቀረቡ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንም ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል ሽራሮ፣ ዓዲ ሃገራይ እና ቢያራ በተባሉት አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተካሄደው ውጊያ፣ የገጠር አካባቢዎችን ያዳረሰ ነበር።
በውጊያዎቹ እንደ መድፍ ያለ ከባድ መሣሪያ እና ድሮን ጥቅም ላይ መዋላቸውን ሁለት ነዋሪዎች ተናግረዋል።