አሜሪካ "ስልታዊ የሳይበር ጥቃት ተፈጽሞባታል" መባሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አስተባበሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው ሳምንት በአገሪቷ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ የአገልግሎት መቋረጥ ማጋጠሙን ተከትሎ አገሪቷ "በስልታዊ የመረጃ መረብ ጥቃት ሥር ናት" በሚል የተነሱ ስጋቶችን አስተባበሉ።

ሩቢዮ ይህን ያሉት በመላ አሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ከተሰረዙ እና የባንክ፣ የአፕል እንዲሁም የማይክሮሶፍት አገልግሎቶች ላይ መስተጓጎል ካጋጠመ በኋላ ነው።

ይህ "ከስልታዊ ጥቃት ወይም ከሆነ ሴራ ጋር ሊገናኝ ይችላል የሚል ስጋት በዜጎች ላይ ሊፈጥር እንደሚችል እንደሚረዱ የገለጹት ሩቢዮ፣ " ይህንን የሚያመልክት ግን ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ሩቢዮ "ስልታዊ ጥቃት እንዳልተፈፀመ" ያረጋገጡ ሲሆን ያጋጠሙት ክስተቶቹ አንዳቸው ከሌላቸው ጋር የሚገናኙ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

የመረጃ መረብ ደኅንነት ባለሙያዎችም የሳይበር ጥቃት ካጋጠመው የአገልግሎት መቋረጥ ጋር ግንኙነት እንደሌለው አስረድተዋል።

ባለሙያዎቹ በአገሪቷ ያጋጠሙት አብዛኞቹ የአገልግሎት መቋረጦች ከአሮጌ መሠረተ ልማቶች ጥገና እና ማሻሻያ ጋራ በተያያዘ የተከሰቱ እንደሚመስሉ ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት የማይክሮሶፍት አገልግሎት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ በአሜሪካ በርካታ በረራዎች ለሰዓታት እንዲቋረጡ እንዲሁም የብሔራዊ የደኅንነት ተቋማት እና በርካታ የአሜሪካ ባንኮች አገልግሎት ላይ መስተጓጎል እንዲፈጠር አድርጓል።

ሁሉም የአገልግሎት መቋረጥ ያጋጠማቸው ተቋማት ክስተቱ ከሳይበር ጥቃት ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ ክስተቱን በተመለከተ አስተያያት የሰጡትም የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ዳይሬክተር ጄይ ክላይተን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከሰጡ ከሰዓታት በኋላ ነው።

ዳይሬክተሩ ለፎክስ ኒውስ በተናገሩበት ወቅት የአገልግሎቶቹ መቋረጥ የሳይበር ጥቃት ውጤት እንዳልሆነ አስረድተዋል። "በርካታ ተቋማት የግንኙነት ሥርዓታቸውን እየቀየሩ እና እያዘመኑ ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህም የአገልግሎት መቋረጥ አስከትሏል ብለዋል።

ክስተቱ የትራምፕን አስተዳደር ያሳስበው እንደሆነ የተጠየቁት ሩቢዮም፣ የሕዝቡን ስጋት እንደሚረዱ ጠቅሰው፣ ይህን ለማስወገድ ወሳኙ ነገር መንግሥት የሚያውቀውን ነገር ለሕዝብ ማሳወቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም ያሉ ማስረጃዎች "ክስተቶቹ ከሳይበር ወንጀል ጋር እንደሚገናኙ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም" ብለዋል።

ከሐሙስ ዕለት ጀምሮ በመላ አገሪቱ የማይክሮሶፍት አገልግሎት ከተቋረጠ በኋላ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች መስተጓጎል አጋጥሟቸዋል።

በማግስቱም የፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር በመላ አገሪቱ በረራዎች መሰረዛቸውን አስታውቋል።

ሰኞ ዕለትም የዩናይትድ ኤርላይንስ ቴክኖሎጂ ብልሽት ካጋጣመው በኋላ ወደ 150 የሚጠጉ በረራዎች እንዲዘገዩ ያደረገ ሲሆን፤ ጄፒሞርጋን ቼዝ ሶፍትዌር ላይ ያጋጠመው ችግርም የተወሰኑ የባንክ አገልግሎቶች ላይ አክል ፈጥሯል።

የአፕል ተጠቃሚዎችም ማክሰኞ ዕለት አይክላውድ እና አፕል ፔይን ላይ በተፈጠረው የአገልግሎት መቋረጥ ተፅዕኖ ደርሶባቸዋል። ኩባንያው የተፈጠረው ችግር ከሳይበር ጥቃት ጋር እንደማይገናኝ እና በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ሥርዓት ከማደስ (አፕዴት ከማድረግ) ጋር እንደሚገናኝ ገልጿል።

የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅነንት ተቋም ለውስጥ ግንኙነት የሚጠቀመው የተለየ ኔትወርክም ሐሙስ እለት ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ነበር።

የሳይበር ደኅንነት ባለሙያዎች ባለፉት አምስት ቀናት በማይክሮሶፍት፣ በአየርመንገድ እና በባንክ አገልግሎቶች መቋረጥ መንስኤዎች ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጻዋል።