ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈርሶ የነበረው የትግራይ ምክር ቤት ተሰብስቦ ደብረጽዮንን ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡን አስታወቀ
በትግራይ ክልል የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ ፈርሶ የነበረው የክልሉ ምክር ቤት ዛሬ ዳግም ተሰብስቦ የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑትን ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡን ትግራይ ቴሌቪዥን ዘገበ።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በተደረሰው የፕሪቶሪያው ስምምነት ፈርሶ የነበረው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት "መንግሥት ስምምነቱን ስላፈረሰው" በሚል ዳግም በይፋ ሥራ መጀመሩን ዛሬ አስታውቋል።
ስድስተኛ መደበኛ ጉባዔውን ሚያዚያ 27/2018 ዓ.ም. ማክሰኞ ዕለት ያካሄደው ምክር ቤቱ፣ ከክልሉ ፕሬዝዳንት በተጨማሪ አፈ ጉባዔ እና ምክትል አፈ ጉባዔዎችንም መምረጡን አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ወ/ሮ ኪሮስ ሐጎስ በአፈ ጉባዔነት እንዲሁም ወ/ሮ ምህረት በርኸን በምክትል አፈ ጉባዔነት መመረጣቸው ተገልጿል።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከስድስት ዓመት በፊት ክልሉ ውስጥ በተደረገ ምርጫ "የተመረጠው የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት ወደ ሥራ" እንዲመለስ መወሰኑን አስታውቆ ነበር።
ህወሓት ይህንን ውሳኔው ያስታወቀው ፌደራል መንግሥት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የተቋቋመውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እየመሩ ያሉት ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደን የሥልጣን ቆይታ በአንድ ዓመት ካራዘመ ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ነው።
በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመው በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና በህወሓት መካከል ባለፉት ሳምንታት ውዝግቦች ሲካሄዱ የቆዩ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ የቀድሞውን ምክር ቤት የመመለስ ፍላጎት የክልሉን ችግር የሚያወሳስብ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ሲቃወሙ ቆይተዋል።
ዛሬ ምክር ቤቱ ከመሰብሰቡ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሌ/ጄነራል ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት የህወሓት መሪዎች እየወሰዱት ባለው እርምጃ ግጭት ሊቀሰቀስ የሚችልበት ዕድል እንዳለ አስጠንቅቀው ነበር።
"አሁን ያለንበት ሁኔታ በሰላምና በጦርነት መካከል ባለች እጅግ ቀጭን መንገድ ላይ ነው። ያልተገፈፈው የጦርነት ደመና ዳግም ሊዘንብ የሚችልበትና በቀላሉ ወደ ጦርነት ተንሸራትተን ልንገባ የምንችልበት አደገኛ ሁኔታ ላይ ነን" ብለዋል።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅናው የተሰረዘበት ህወሓት ከስድስት ዓመት በፊት የተካሄደው እና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ውዝግብ ውስጥ በገባበት ምርጫ የተመሠረተው የክልሉ ምክር ቤት ሕጋዊ ነው በማለት ይከራከራል።
ህወሓት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ምርጫው "የማይጸና" እንዳልተደረገ ይልቁንም "ታግዶ" መቆየቱን ከዚህ በፊት ለቢቢሲ ተናግሯል።
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም በወቅቱ የተመሠረተው የክልሉ መንግሥት "አልፈረሰም፤ ጊዜያዊ አስተዳደር የተመሠረተው በድርድር ነው" ብለዋል።
እስካሁን ድረስ የፌደራል መንግሥቱ ህወሓት የክልሉ ምክር ቤት እንዲመለስ እና ፕሬዝዳንት መሰየሙን በተመለከተ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ያለው ነገር የለም።
ማክሰኞ ሚያዚያ 27/2018 ዓ.ም. የተካሄደው እና ዶ/ር ደብረጽዮን የተመረጡበት የክልሉ ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባ ላለፉት ስድስት ዓመታት "ተቋርጦ የነበረው የትግራይ ክልል መንግሥት ሥራ እንዲጀምር" የቀረበለትን አጀንዳ በሁለት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁ ተገልጿል።
ዶ/ር ደብረጽዮንን ፕሬዝዳንት የተመረጡት በአንድ ተቃውሞ እና በሦስት ድምጸ ተዓቅቦ መሆኑን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
ዶ/ር ደብረፂዮን እስከ ቀጣዩ ጉባኤ በምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ የሚያስፈልጉ ማስተካከያዎችን በማድረግ በሥራ ላይ እንዲቆዩ ምክር ቤቱ በአንድ ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ ማጽደቁ ተገልጿል።
ፈርሶ የነበረው የትግራይ ክልል ምክር ቤት የተመረጠበት ሂደት በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ከፍተኛ ውዝግብን አስነስቶ ለደም አፋሳሹ ጦርነት መቀስቀስ አንዱ ምክንያት እንደነበር ይነገራል።
ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ ክልሉ የራሱን ምርጫ ኮሚሽን አቋቁሞ ያካሄደው ምርጫ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን በመሆኑ "እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈጻሚነት የሌለው ነው" ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወቅቱ በሙሉ ድምጽ ውድቅ እንዳደረገው ይታወሳል።