የኢራን ጦርነት ዩክሬንን ያጠናከረው እንዴት ነው? ከሩሲያ ጋር የሚደረግን የተኩስ አቁም ያፋጥን ይሆን?

የንባብ ጊዜ: 8 ደቂቃ

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በመጋቢት ወር ሳዑዲ አረቢያ ያቀኑት አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ ነበር። በርግጥ የእርሳቸው ጉብኝት ያልተጠበቀ ነበር።

በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ የጉብኝታቸው ዓላማ "የሕይወት ጥበቃን ለማጠናከር" እንደሆነ ገልጸዋል።

ዩክሬንን ከሩሲያ የተከፈተባትን ጦርነት እየመከቱ ያሉት ዜሌንስኪ ወደ ባሕረ ሰላጤ የተጓዙት ኪዬቭ በጦርነት ሜዳ ላይ ያካበተችውን የድሮን መከላከል አቅም በይፋ ለማሳየት ነው።

ዩክሬን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በኢራን ሚሳኤሎች እና ድሮኖች ጥቃት ለደረሰባቸው ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኳታር የድሮን ልምድ እና ቴክኖሎጂን ለማካፈል አቅደው ነው ወደ ስፍራው የተጓዙት።

ከዚህ በተጨማሪም ከአገራቱ ጋር ያላቸውን ጥምረት ለማጠናከር እና ከሀብታሞቹ የአሜሪካን አጋሮች ጋር የንግድ እና የመከላከያ ስምምነቶችን በመፈራረም አብሮ ለመሥራት ተስፋ ማድረጋቸውንም በወቅቱ ተናግረዋል።

"[የባህረ ሰላጤ አገራት] ራሳቸውን እንዲከላከሉ መርዳት እንፈልጋለን። ከሌሎች አገሮች ጋር እንዲህ ዓይነት ሽርክና መመስረታችንን እንቀጥላለን" ሲሉ ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

የኃይል ጫና

መጀመሪያ ላይ የኢራን ግጭት ተጽዕኖ ለዩክሬን እጅግ አሉታዊ ይመስል ነበር። የዶናልድ ትራምፕን ትኩረት ከሞስኮ እና ከኪዬቭ የሰላም ጥረቶች ዞር ከማድረጉ ባሻገር በፍጥነት ባዶ የሆነውን የሩሲያ ካዝና በገንዘብ እንደሚሞላ ተሰግቶ ነበር።

የመካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅን የያዙ መርከቦች የሆርሙዝ ወሽመጥ በማቋረጥ ዓለም አቀፍ ደንበኞችን ማግኘት ስለማይችሉ ሞስኮ በከፍተኛ ዋጋ ብዙ ነዳጅ ለተጨማሪ አገሮች መሸጥ ችላለች።

በዓለም ዙሪያ በተከሰተው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ትራምፕ አገራት ከሩሲያ ነዳጅ እንዲገዙ የሰጡትን ፈቃድ አራዝመዋል።

ሩሲያ ገንዘብ ባገኘች ቁጥር ከዩክሬን ጋር የምታደርገውን ጦርነት ታራዝማለች።

ሞስኮ እአአ በየካቲት 2022 ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ኪዬቭ ዓለም አቀፍ ግምቶችን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።

አሁንም ይህንን በድጋሚ አሳይታለች። ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የመጨረሻ እና ተስፋ የተደረገበት የሰላም ድርድር ከመደረጉ በፊት ጠንካራ ቦታ ላይ ሆና ለመገኘት የኢራን ጦርነት ተጽእኖን ወደ ጥቅሟ በመቀየር በብልሃት እየሠራች ነው።

ረቡዕ ዕለት ትራምፕ ከቭላድሚር ፑቲን ጋር "በጣም ጥሩ" ውይይት ካደረጉ በኋላ በዩክሬን ዙሪያ "አንፃራዊ መፍትሔ በፍጥነት" ሊደረስበት እንደሚችል እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"'አንዳንድ ሰዎች' ስምምነት ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ አድርገውታል ብዬ አስባለሁ" ሲሉ አክለዋል።

ትራምፕ ስለፑቲን ተመሳሳይ አዎንታዊ አስተያየት ሲሰጡ እና የዩክሬን መሪን የተኩስ አቁም ስምምነት ባለማድረጋቸው በተዘዋዋሪ ወይም በግልጽ ሲተቹ የመጀመሪያቸው አይደለም።

"መፍትሔው" ግን እስካሁን አልተገኘም።

ዜሌንስኪ በበኩላቸው በተቻላቸው አቅም ዩክሬንን በማጠናከር ላይ ትኩረት አድርገዋል። የሚገኙ ዕድሎችን በሚገባ መጠቀም ከሚታወቁባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ነው።

በሚያዝያ ወር እንደገና የጎበኟት ሳዑዲ አረቢያ፣ ሩሲያ ወደ ዩክሬንን የምትተኩሰው ዓይነት የባሌስቲክ ሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶች ከኢራን ገጥሟታል ብለዋል።

ከሞስኮ በጣም ኃይለኛ መሳሪያዎች አንዱ በኢራን የተሠራውና ዝቅተኛ ዋጋ ያለው የሻህድ-136 የጥቃት ድሮን እና በዚሁ ድሮን ላይ ተመስርቶ የተሠራው ጌራን የተሰኘው ሰው አልባ አውሮፕላን ነው።

ሻህድ ከ80 ሺህ እስከ 130 ሺህ ዶላር ሊወጣ ቢችልም፣ ዜለንስኪ እስከ 10 ሺህ ዶላር ወጪ በሚደረግበት መሣሪያ ሊጠለፍ እንደሚችል ተናግረዋል። ይህም በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከሚያወጡት ባህላዊ የአየር መቃወሚኣ ሚሳዔሎች አንጻር በጣም ርካሽ ነው።

በሩሲያ ድሮን ስጋት ውስጥ የወደቁ በበርካታ የአውሮፓ የኔቶ አባል አገራትም ትኩረት እየሰጡት ነው።

ዩክሬን በሚያዝያ ወር ከአውሮፓ አጋሮቿ ጋር ሁለት የመከላከያ ትብብር ስምምነቶችን ተፈራርማለች።

አንደኛው ከኖርዌይ ጋር 8.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ስምምነት ሲሆን እስከ 2030 ድረስ የሚዘልቅ 28 ቢሊዮን ዶላር የድጋፍ ፓኬጅ አካል ነው።

ሌላኛው ደግሞ ከጀርመን ጋር ሲሆን "የተለያዩ ዓይነት ድሮኖች፣ ሚሳዔሎች፣ ሶፍትዌሮች እና ዘመናዊ የመከላከያ ስርዓቶችን" ያካተተ የ4.7 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ነው።

የባህረ ሰላጤው አገራትን በተመለከተ ዩክሬንን ከሩሲያ ራሷን ለመከላከል የምታደርገውን እገዛ እንደሚደግፉ ዜሌንስኪ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በወቅቱ ዋሽንግተን መሣሪያዎችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እየላከች ስለነበር ዩክሬንን ለመርዳት የሚውል መሣሪያ ለአውሮፓውያን ለመሸጥ የሚያስችል አቅም አልነበራትም። ትራምፕ የሰጡት ምላሽ "ሁልጊዜ ያንን እናደርጋለን። አንዳንድ ጊዜ ከአንዱ ወስደን፣ ለሌላው እንጠቀማለን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

"የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ራሳችንን ለማጠናከር ዐዕድል እንዲሰጡን እንፈልጋለን" ሲሉ ዜሌንስኪ በቅርቡ ለፈረንሳዩ ጋዜጣ ለሞንዴ ተናግረዋል።

"እኛ የሌለን የተወሰኑ የአየር መከላከያ ሚሳዔሎች አሏቸው። በዚህ ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ ነው የምንፈልገው።"

መሠረተ ልማትን ዒላማ ማድረግ

ዩክሬን ከኢራን ግጭት በአገር ውስጥ የምትጠቀመውን ቁልፍ ትምህርት ወስዳለች። ይህም የጠላትን የነዳጅ ኤክስፖርት ተቋማት ማጥቃት የሚያስከትለውን ትልቅ ተጽዕኖ ነው።

የሩሲያ የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች በዩክሬን በተመረቱ የረዥም ርቀት ድሮኖች ቅድሚያ ዒላማ የሚደረጉ ናቸው።

እንደ ዜሌንስኪ ገለጻ ከሆነ ሩሲያ በቅርቡ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ቢኖርም በኢነርጂ ዘርፏ እስከ ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ "ወሳኝ" ኪሳራ እያጋጠማት ነው።

የድፍድፍ ነዳጅ ኤክስፖርት መረጃ እንደሚያሳየው ከዋጋ ጭማሪው ጎን ለጎን አሜሪካ የሩሲያን ነዳጅ በሚገዙ አገሮች ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በማላላቷ የሩሲያ ገቢ በኢራን ጦርነት ሦስተኛ ሳምንት በ2.3 እጥፍ ጨምሯል።

በአራተኛው ሳምንት የዩክሬን ድሮን በኢነርጂ መሠረተ ልማት ላይ ባደረሰው ጥቃት የሩሲያን ገቢ በአንድ ቢሊዮን ዶላር ቀንሷል። ይህም ካለፈው ትርፍ ሁለት ሦስተኛውን ያህል ቀንሷል።

የኢራን ጦርነት ውጤት ለዩክሬን የሰጠው ሌላ ጥቅም ኪዬቭ በሚመጣው ዓመት ወታደራዊ መሣሪያዎችን ለመግዛት እና ለማምረት በአስቸኳይ እንደሚያስፈልጋት የገለጸችውን 90 ቢሊዮን ዩሮ ብድር በመጨረሻም በአውሮፓ ኅብረት መፈቀዱ ነው።

ብድሩ የአውሮፓ ኅብረት አባል በሆነችው ሃንጋሪ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የክሬምሊን ደጋፊ ታግዶ ቆይቷል።

ነገር ግን የሃንጋሪው ቪክቶር ኦርባን ባለፈው ወር በሃንጋሪ ምርጫ ከፍተኛ ሽንፈት ካጋጠማቸው በኋላ ሩሲያ ወዳጃቸውን አጥተዋል።

ኦርባን የዶናልድ ትራምፕ የቅርብ ጓደኛ እና አድናቂ ናቸው። ይህ በምርጫ ጊዜም አልረዳቸውም። መራጮች የኢራን የኃይል ወጪ መጨመሩ እንዳበሳጫቸው ተናግረዋል። የኦርባን መሸነፍ የአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን ብድሩን እንዲለቀቅ አስችሎታል።

ኪዬቭ በዚህ ረገድ ካስመዘገበቻቸው "ድሎች" በተጨማሪም ዩክሬን በየወሩ ከ30 ሺህ በላይ የጠላት ወታደሮችን ያለማቋረጥ እየገደለች እንደሆነ በመናገሯ፣ ዜሌንስኪ ከአሁን በኋላ ከሩሲያ ጋር የሚደረገውን የሰላም ስምምነት ለማጠናቀቀ የተሻለ ዕድል ሊሰጣቸው ይችላል።

በዩክሬን ያለው የጥድፊያ ስሜት ለረዥም ጊዜ ቆይቷል። ሰዎች ተዳክመዋል፤ እየተሰቃዩም ነው። አዲስ ወታደሮችን መመልመል ከባድ ፈተና ሆኖ ከመቆየቱም በላይ በጦር ሜዳ ላይ ያሉት ወደ ቤታቸው ለመመለስ በጣም ጓጉተዋል።

የአክብሮት ማጣት?

ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማምጣት የታለሙ ድርድሮችስ? ከፈረንጆች ገና በፊት በትራምፕ አስተዳደር በጣም በስፋት ይነገሩ ነበር።

ፕሬዚዳንት ሆነው እንደገና ከመመረጣቸው በፊት ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት በ24 ሰዓታት ውስጥ እንደሚያስቆም ደጋግመው ተናግረዋል። እውነታው ግን ከተስፋው ጋር አልተጣጣመም።

ትልቁ ፍንጭ በትራምፕ የተሾሙት የሰላም መልዕክተኞች የልጃቸው ባል ጃሬድ ኩሽነር እና የቀድሞው የሪል እስቴት ባለጸጋ ስቲቭ ዊትኮፍን እንቅስቃሴ የሚመለከት ነው። ወደ ኪየቭ የሚደረገው ጉዞ በተደጋጋሚ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። አሁን ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ ተጠምደዋል።

ዜሌንስኪ የሁለቱን ሰዎች ወደ ኪዬቭ አለማቅናትን "አክብሮት የጎደለው" አድርገው እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል።

የሰላም ውይይቶች "በቴክኒካል" ደረጃ እየተካሄዱ ነው ቢሉም ግን የኢራን ግጭት እስኪጠናቀቅ ድረስ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማይኖር ይጠበቃል። የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት መቼ እንደሚያበቃ ግን አይታወቅም።

ኩሽነር እና ዊትኮፍ ይፋዊ በሆነ መልኩ ኪዬቭን ጎብኝተው እንደማያውቁ ልብ ሊባል ይገባል።

ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም የታለሙ የተኩስ አቁም ውይይቶች እየተጠናከሩ ሲሄዱ ወደ ሩሲያ መዲና አቅንተዋል። ጥር ላይም ሄደው ነበር። ዊትኮፍ ስምንት ጊዜ ሞስኮን ጎብኝተዋል። ቀደም ሲልም በሩሲያ በግል ጉዳዮች ብዙ ንግድ ሰርተዋል። ከፑቲን ጋርም በተለያዩ ጊዜያት ተገናኝተዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ለሩሲያ ምንም ዓይነት አድልዎ እንዳልፈጸመ ገልጿል።

ዩክሬን እና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የታተመውን የአሜሪካ ብሔራዊ የደህንነት ስትራቴጂ (ኤንኤስኤስ) በማየታቸው ግራ ተጋብተዋል።

ሩሲያን የደህንነት ስጋት እንደሆነች በግልጽ አያስቀምጥም። ይህ ግን በዋሽንግተን የአውሮፓ አጋር በሆኑ የኔቶ አባላት ሞስኮ ከምትታይበት ጋር የሚቃረን ነው።

ኤንኤስኤስ በዩክሬን ጦርነትን ማስቆም ያለውን አስፈላጊነት አፅንኦት ቢሰጥም ግን ትኩረቱ ለኪዬቭ ዘላቂ ሰላም መፍጠር ላይ አይደለም።

ይልቁንም የተገለጸው ዓላማ "ስትራቴጂካዊ መረጋጋት" እና አሜሪካ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ሀብቶችን ለማስለቀቅ ከሩሲያ ጋር ሊኖር ስለሚችል አጋርነት ይጠቅሳል።

እነዚህ የትራምፕ አስተዳደር አመለካከቶች ክሬምሊንን የሚያስደስቱ ናቸው። ለዚህም ማሳያው ቃል አቀባዩ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ኤንኤስኤስ ከሞስኮ ራዕይ ጋር "በአብዛኛው የሚጣጣም" መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል።

በትራምፕ የሥልጣን ዘመን በሩሲያ ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ማጣል ወይም ማስቀጠል አልተቻለም። ይህም ክሬምሊን ተፈጻሚ የማይሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን እየዘረዘረች ለኪዬቭ (ወይም ለአውሮፓ ደጋፊዎቿ) ድርድርን ፈታኝ እንድታደርግ አስችሏታል።

ከዚህም በተጨማሪ የአሜሪካ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ለዩክሬን ሙሉ በሙሉ ደርቋል።

በምትኩ አውሮፓውያን ወደ ኪየቭ የጦር መሣሪያዎችን ለመላክ ከአሜሪካ ወደመግዛት ገብተዋል። በኢራን ግጭት ምክንያት ይህም አቅርቦት አሁን አደጋ ላይ ነው።

የሠላም ተስፋዎች

ሩሲያ ወደ ሰላም ድርድር እንድተገባ ለማሳመን የምትችለው ብቸኛ ኃይል አሜሪካ ነች ይባላል።

ፑቲን በቅርቡ ጦርነቱን የማስቆም ምንም ምልክት አላሳዩም። እየሆነ ያለው በተቃራኒው ነው።

ዓለም በኢራን ላይ በተጀመረው ጦርነት ትኩረቱ በመከፋፈሉ ሞስኮ በዩክሬን ሰላማዊ ዜጎች እና በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቷን አጠናክራለች።

ይህ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ወደ ድርድር ጠረጴዛ ከመምጣታቸው በፊት የመጨረሻ ጥቃት ወይም ቀጣይነት ያለው አስፈሪ ቁርጠኝነት ምልክት እንደሆነ አስተያየት እየተሰጠ ነው።

በብራስልስ የአውሮፓ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት አብዛኛዎቹ የኋለኛውን እንደሚሆን ይጠረጥራሉ።

የሩሲያ ኢኮኖሚ በተጣለበት ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች የተነሳ እየታገለ ሊሆን ቢችልም ሳይንበረከክ ጦርነት ውስጥ እየተሳተፈ ነው።

ይህንን ማዘግየት ቀላል አይሆንም። ይህም የአውሮፓ አገሮች በዩክሬን ሰላም ቢፈጠረም ሩሲያ አውሮፓ እና የኔቶ አባላትን ጨምሮ ሌላ አለመረጋጋት በፍጥነት መፍጠር እንደምትፈልግ በማሰብ እንዲጨነቁ አድርጓቸዋል።

ኔዘርላንድስ፣ ጀርመን እና ኔቶ ይህን ምናልባትም ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ከዚህ ውጭም የፑቲን ኩራት እና ምኞት አለ። በእርግጥ እጆቻቸውን አንስተው በዩክሬን መሸነፋቸውን አምነው ይቀበላሉ?

"ሩሲያ ምክንያታዊ መንግሥት ቢኖራት ኖሮ ጦርነቱን ታቆም ነበር" ብለዋል በለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር የምርምር ባልደረባ ሉክ ኩፐር።

የሰላም ደጋፊ ድርጅቶች ጥምረት በሆነው ፒስሬፕ የዩክሬን ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ኩፐር "ኢኮኖሚው ቆሟል ወይም ውድቀት ውስጥ ነው። ሩሲያ በስራ ላይ ሊሆኑ የሚገባውን የሰው ኃይል ወደ ጦርነት እየላከች ነው፤ የግሉ ቢዝነስ በጦርነት ኢኮኖሚ ጫና እየተሰቃየ ነው… ሩሲያ ምን አሳካች? የዩክሬን የተወሰነ ግዛት። በእርግጥ ይህ ለተኩስ አቁም ስምምነት ጠቃሚ ይሆናል። ነገር ግን ፑቲን በእነዚህ ጉዳዮች አይሳቡም። ይህ ሁሉ የአንድ ሰው ውሳኔ ነው" ብለዋል።

የዩክሬን ጥርጣሬ

ኪየቭ አሁንም የአሜሪካን ተሳትፎ እየጠበቀች ቢሆንም በርካታ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ግን በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አላቸው።

የትራምፕ አስተዳደር ሰላምን ለማረጋገጥ የሚፈልጉትን እርምጃ እንደሚወስድ ወይም የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም እንኳ የሚፈለገውን የደህንነት ዋስትናዎችን ስለማሰጠቱ ጥርጣሬ አላቸው።

የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማርክ ካንቺያን "ዩክሬናውያን የሰላም ስምምነት ለመፈራረም የሚያስችል አስተማማኝ የሆነ የደህንነት ዋስትና ማግኘት እንደሚችሉ እና ሩሲያ፣ አሜሪካ እና አውሮፓውያንም እንደሚስማሙ መገመት ከባድ ነው" ብለዋል።

ነገር ግን "ለመሸነፍ ጊዜ የለም" የሚሉት የአውሮፓ መሪዎች፣ ሩሲያ በዩክሬን ድል እንዳገኘች ከተሰማት ለሰፊው አህጉራዊ ደህንነት አደገኛ እንደሚሆን ያምናሉ ሲሉ በሮያል ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የፋይናንስ እና ደህንነት ማዕከል ዳይሬክተር ቶም ኪቲንጄ ተናግረዋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ቢኖርም ትራምፕ ከቴህራን ጋር ስምምነት ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ በቀጠለበት በዚህ ወቅት በማንኛውም ጊዜ በኢራን ላይ ከማተኮር ሊሸሹ እንደሚችሉ ቶም ገልጸዋል።

ከዚያም በፍጥነት ወደ ሩሲያ-ዩክሬን ጥያቄ መመለስ ይችላሉ። አውሮፓውያን አሁን በዩክሬን ውስጥ ከነበረው የበለጠ ወሳኝ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ሲሉም አጥብቀው ይከራከራሉ።

ዩክሬንን ለመርዳት "እስከሚያስፈልግ ድረስ [እንሄዳለን]" የሚለውን ሐረግ በተደጋጋሚ ቢጠቀሙም ተቺዎች የአውሮፓ መሪዎች ለዩክሬን ሰላም በደንብ ከመስራት ይልቅ ጦርነቱን 'እንደሚያስተዳድሩ' ለረጅም ጊዜ ሲከሱ ቆይተዋል።