አርሰናል ከ20 ዓመታት በኋላ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ደረሰ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አርሰናል በበኩካዮ ሳካ ብቸኛ ጎል አትሌቲኮ ማድሪድን በማሸነፍ ከ20 ዓመታት በኋላ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ደረሰ።

በመጀመሪያው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች አንድ አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ መድፈኞቹ በአጠቃላይ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ነው ለፍጻሜ መብቃት የቻሉት።

ይህ ውጤት አርሰናል ከፕሪሚየር ሊጉ በተጨማሪ ለአውሮፓው ትልቁ ዋንጫ የሚያደርገውን ፉክክር ያጠናከረበት ሆኗል።

የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ አንድ አቻ የተለያዩት ሁለቱ ቡድኖች በመልሱ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ይህ ነው የሚባል ዕድል መፍጠር አልቻሉም ነበር።

44ኛው ደቂቃ ላይ ሊአንድሮ ትሮሳርድ ወደ ጎል የመታውን ኳስ የአትሌቲኮው ግብ ጠባቂ ጃን ኦብላክ ቢመልሰው ኳሱን ሳካ አግኝቶ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

አትሌቲኮ በጁሊያኖ ሲሞኔ በኩል ሁለት ዕድሎችን ማግኘት ቢችልም ዴክላን ራይስ እና ጋብርኤል መከላከል ችለዋል።

ጎይኮሬሽ የቡድኑን መሪነት ማሳደግ የሚያስችል ዕድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ውጤቱን ተከለትሎ አርሰናል ከ2006 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በቅቷል።

ቡድኑ ከባየር ሙኒክ እና ፒኤስጂ አሸናፊ ጋር ግንቦት መጨረሻ ላይ በቡዳፔስት የፍጻሜ ጨዋታውን ያከናውናል።

አርሰናል ዘንድሮ ትኩረት ያደረገው በሊጉ ዋንጫ ላይ በመሆኑ በሻምፒዮንስ ሊግ ያደረገው ያለመሸነፍ ጉዞ ብዙም ትኩረት አልተደረገበትም።

በዚህም ባየር ሙኒክን፣ ኢንተር ሚላንን፣ ስፖርቲንግን እና አትሌቲኮ ማድሪድን (ሁለት ጊዜ) ማሸነፍ ችሏል።

ቡድኑ በጥሩ ብቃት ፉልሃምን ካሸነፈበት አሰላለፍ አንድም ተጫዋች ሳይቀየር ወደ ሜዳ ገብቷል።

አርሰናል ቀጣይ አራት ጨዋታዎችን ካሸነፈ የፕሪሚየር ሊጉን እና የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ያነሳል።

በታገይነቱ የሚታወቀው የዲዬጎ ሲሞኔው አትሌቲኮ ማድሪድ በሁለቱ ዙር አሸንፎ ለፍጻሜ ሳይበቃ ቀርቷል።

የአሰልጣኙ ልጅ ጁሊያኖ ሲሞኔ ያገኛቸውን ሁለት አጋጣሚዎች አለመጠቀሙ ለቡድኑ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኗል።

ቡድኑ አጥቂዎችን ቀይሮ በማስገባት ጎል ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

ቡድኑ በሲሞኔ አሰልጣኝነት ሁለት ጊዜ ለሻምፒዮንስ ሊጉ ፍጻሜ ቢደርስም በተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድ ተሸንፎ ዋንጫውን አሳልፎ ሰጥቷል።