ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በተደረገ ሦስተኛ ጭማሪ የቤንዚን ዋጋ ከ167 ብር አለፈ
የዓለም የነዳጅ ገበያ እና አቅርቦት ላይ መቃወስ የፈጠረው የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ በተደረገ የዋጋ ጭማሪ የቤንዚን ችርቻሮ ዋጋ በሊትር 25 ብር ጨመረ። ከፍተኛውን ለውጥ ያስተናገደው የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በአንድ ጊዜ የ169 ብር ጭማሪ ተደርጎበታል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከትናንት ሰኞ ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም. ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ የሆነ አዲስ የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ይፋ አድርጓል።
"የዓለም ነዳጅ ዋጋን መነሻ በማድረግ" የተደረገው ይህ የዋጋ ጭማሪ ይፋ የሆነው መጋቢት ላይ ከተደረገው ማሻሻያ አንድ ወር ገደማ በኋላ ነው።
በትናንቱ አዲስ የዋጋ ተመን ከፍተኛ ጭማሪ የተደረገበት የአውሮፕላን ነዳጅ ነው። ዋጋው ከእጥፍ በላይ በመጨመር 319 ብር ከ67 ሳንቲም ገብቷል።
ዋጋው በ157 ብር ያደገው ኬሮሲንም ከፍተኛ ጭማሪ ተደርጎበት 320 ብር ከ66 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል።
ቤንዚን ላይ የተደረገው የ25 ብር ጭማሪ ነው። በዚህም ዋጋው 167 ብር ከ50 ሳንቲም ሆኗል። የ17 ብር ጭማሪ የተደረገበት ነጭ ናፍጣ ደግሞ የአንድ ሊትር ዋጋው 180 ብር ከ46 ሳንቲም ደርሷል።
የአሁኑን ጨምሮ መንግሥት የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ባደረጋቸው ሦስት የዋጋ ጭማዎች የቤንዚን ዋጋ ላይ የተደረገው አጠቃላይ ጭማሪ ከ38 ብር ያልፋል። ነጭ ናፍጣ ደግሞ ዋጋው ከ51 ብር በላይ ጨምሯል።
የአሁኑ ጭማሪ የተደረገው የፌደራል መንግሥት ከኢራን ጦርነት መጀመር በፊት የነበረው የነጭ ናፍጣ ዕለታዊ የአቅርቦት መጠን ወደነበረበት እንዲመለስ መወሰኑን ካስታወቀ ከሳምንት ገደማ በኋላ ነው።
የጦርነቱን መጀመር ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር ውል የገቡ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት "በግዢ ሂደት እና ተገዝቶ በመቅረብ ላይ የነበረ ከ180 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ" ነዳጅን ማቅረብ እንደማይችሉ ማስታወቃቸው ተገልጾ ነበር።
በዚህም ምክንያት የነጭ ናፍጣ ዕለታዊ አቅርቦት በግማሽ ቀንሶ ከነበረበት 9.1 ሚሊዮን ሊትር ወደ 4.5 ሚሊዮን ሊትር ወርዶ ቆይቷል።
የሕዝብ ማመላለሻ እና ጭነት ተሽከርካሪዎች በብዛት የሚጠቀሙት የነጭ ናፍጣ አቅርቦት መቀነስ አገር አቋራጭ እንዲሁም የሸቀጥ ጭነት ጉዞዎች እንዲገደቡ አድርጓል። ይህንን ተከትሎም የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ተስተውሎበታል።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ መንግሥት የነዳጅ "ዲፖዎች መሞላት ስለነበረቸባው"፣ "የዓለም ዋጋ በመናሩ" እና "ቁጠባ መረጋገጥ ስለነበረበት" በግማሽ እንዲቀን ተደርጎ የነበረው የነጭ ናፍጣ አቅርቦት ወደ ነበረበት እንዲመለስ መወሰኑን አስታውቀዋል።
"በኢኮኖሚ ውስጥ የነጭ ናፍጣ አቅርቦት መቀነሱ በሕዝቡ እና በኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ረገድ ላይ የተለያዩ ጫናዎች መከሰታቸው ግልጽ ነው፤ የተለያየ ጉዳት መድረሱም ግልጽ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ግን በድጎማ [ምክንያት] መንግሥት ላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው" ብለዋል።
እንደ የገንዘብ ሚኒስትሩ ገለጻ በጦርነቱ ምክንያት በዓለም ገበያ የነጭ ናፍጣ ዋጋ ላይ የታየው ጭማሪ "ወደ ሕዝብ" አልተላለፈም። በሌሎች የነዳጅ ዓይነቶች ላይ የታየውን ጭማሪ ለመደጎምም ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ ተደርጓል።
"በየወሩ [ሲደረግ] ከነበረው ድጎማ በተጨማሪ፤ በሁሉም የነዳጅ ዓይነቶች ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ድጎማ በተጨማሪ 20 ቢሊዮን [ብር] አዲስ ድጎማ መንግሥት እየተከፈለ ይገኛል" ብለዋል። የአሁኑ ጭማሪ የመንግሥትን አጠቃላይ "የድጎማ ክምችት ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ" ማድረጉን ገልጸዋል።