ዶናልድ ትራምፕ ኢራን መሸነፏን አምና “እጇን መስጠት አለባት” አሉ
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት የኢራን ጦር አቅምን አጣጥለው ቴህራን መሸነፏን አምና “እጇን መስጠት” ነበረባት ግን ያንን ለማድረግ የቴህራን ባለሥልጣናት ትምክህት ይዟቸዋል አሉ።
ትራምፕ በኦቫል ኦቪስ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ የኢራን ጦር ደካማ መሆኑን እና "የመጫወቻ ጠመንጃዎች" ይጠቀማሉ ሲሉ ተሳልቀዋል።
ኢራን በአደባባይ የምትለው ሌላ ቢሆንም በምስጢር ግን ከስምምነት መድረስ ትፈልጋለች ሲሉም ተናግረዋል።
“ጨዋታ ይጫወታሉ። ነገር ግን አንድ ነገር ልንገራችሁ፤ ከስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። ጦሩ ሙሉ በሙሉ ከወደመበት ማን የማይፈልግ አለ” ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ኢራን ምንም አማራጭ የላትም” በማለት የቴህራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር ሲነጋገሩ እና ቴሌቪዥን ላይ ሲቀርቡ የተለያየ ነገር ይናገራሉ ሲሉ ተችዋቸዋል።
“ምንም አማራጭ የላትም፤ ኖሯትም አያውቅም” በማለት የኢራን ጦር መሸነፉን ዳግም ተናግረዋል።
የኢራን ጦር ባሕር ኃይል፣ አየር ኃይል ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ “የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዲኖራቸው አንፈቅድም” ሲሉ አስተየየታቸውን ሰጥተዋል።
አሜሪካ “ኢራንን ክፉኛ ደቁሳታለች” ያሉት ትራምፕ “በጠመንጃ ብቻ ጥቂት ጀልባዎችን መቀነስ ችለናል” ብለዋል።
ሰኞ ዕለት አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የነበሩ የኢራን ጀልባዎችን መምታቷን አስታውቃለች።
ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ በኢራን በመዘጋቱ መውጫ አጥተው የቆዩ መርከቦችን እንደሚያስወጡ የተናገሩት ትራምፕ፤ “ሰባት ትንሽ ጀልባዎችም ወይም እነሱ ‘ፈጣን’ ጀልባ የሚሏቸውን መትተናል። የቀሯቸው እነሱ ብቻ ነበሩ” ብለዋል።
ትራምፕ በኦቫል ኢፊስ በሰጡት መግለጫ ኢራን በጦርነቱ መጀመርያ ወቅት 159 መርከቦች እንደነበሯት ገልጸው “ያሏቸው እያንዳንዱ መርከብ ከባሕር ወለል በታች ነው የሚገኙት’ ሲሉ ተናግረዋል።
በባሕር ኃይላቸው ምንም ዓይነት መርከብ የላቸውም ያሉት ትራምፕ ከዚያ ይልቅ ስምንት “ትንሽ ጀልባዎች” ነበሩ እነርሱም “ሁሉም ወድመዋል” ብለዋል።
አክለውም “ከእኛ ታላቅ ባሕር ኃይል ጋር ለመገዳደር ትንንሽ ጀልባ እየፈለጉ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ኢራን የተኩስ አቁሙን ጣሰች የሚባለው ምን ስታደርግ ነው ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ “ስለምነግራችሁ ታውቁታላችሁ” በማለት መልሰዋል።
“በጣም አስፈላጊው ነገር ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና እንደሌለባቸው ያውቃሉ” ብለዋል።
ኢራን መሸነፏን አምና “እጇን መስጠት አለባት” ያሉት ትራምፕ “ይህ መደበኛ ውጊያ ቢሆን ኖሮ ይሄኔ አቁመውት ነበር” ብለዋል።
አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚንቀሳቀሱ መርከቦች ማገዷን በተመለከተም ሲናገሩ አንድም መርከብ ማለፍ እንዳልቻለ አብራርተዋል።
አንድ መርከብ ለማለፍ ሲሞክር ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው በኋላ የአሜሪካ ጦር “በአንድ ተኩስ ሞተሩን መትቶታል” ብለዋል።
ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ከጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ጋር “ትልልቅ ስምምነቶችን” እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ቻይና በሚጓዙበት ወቅት ከፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋርም መልካም ንግግር ይኖራል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ትራምፕ አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ ጣለችው እገዳ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ቴህራን “ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች” ብለዋል።
“ጨዋታ ይጫወታሉ። የምነግራችሁ ነገር ግን ከስምምነት መድረስ ይፈልጋሉ” ብለዋል።