ሕጻናት በሒሳብ ትምህርት አቀባበላቸው ደካማ እንዲሆኑ የሚያደርገው ሕመም

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ጆሴፍ ናቴምቦ በወባ በሽታ ሲያዝም ሲድንም ገና ጨቅላ ሕፃን ነበር። በወቅቱ የ54 ዓመቷ እናቱ ማሪያ ልጇ ባጋጠመው ነገር ብትደነግጥም ቶሎ በማገገሙ እፎይታ ተሰምቷት፤ ክፉው ነገር እንዳለፈ አመነች።

ነገር ግን ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ፣ የ18 ዓመቱ ኡጋንዳዊ ወጣት ዶክተሮች በልጅነቱ ከያዘው ኢንፌክሽን ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሚያምኑበት የመማር ችግር አጋጠመው።

በተለይ ሒሳብ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ አግኝቶታል፤ ቁጥሮችን "ግራ የሚያጋቡ" ሲል ይገልጻቸዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በትምህርቱ ወደ ኋላ ቀርቷል። እናቱ በትምህርት ቤት የሚያጋጥመው ተግዳሮት የሥራ ተስፋውን ሊገድበው ይችላል በሚል ፍራቻ ስለወደፊት ሕይወቱ ትጨነቃለች።

ጆሴፍ በኡጋንዳ ወባ በሚያስከትለው ዘላቂ የሆነ የነርቭ ዕድገት ጉዳት (Neurobehavioral Development- MIND) ላይ ጥናት ከተደረገባቸው ከ1400 በላይ ልጆች መካከል አንዱ ነው።

በአሜሪካ የሕክምና ማህበር ጆርናል (ጃማ) ላይ የታተመው ይህ አዲስ ጥናት እንደሚያሳየው የጆሴፍ ሁኔታ በተለይም በሒሳብ ደካማ መሆን ያን ያህል ያልተለመደ ላይሆን ይችላል።

ጥናቱ እንደሚያመለክተው ከከባድ በሽታዎች የተረፉ ብዙ ልጆች እንደ ጆሴፍ ዓይነት ተመሳሳይ የመማር ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል።

"ድብቅ ጠባሳ"

ወባ የሚከሰተው በትንኝ በሚተላለፉ ጥገኛ ተውሳኮች ሲሆን እስካሁን ድረስ የወባ በሽታ በዳኑ ሰዎች ላይ ስለሚፈጠር የረዥም ጊዜ የመማር ተጽዕኖ በደንብ አልተጠናም።

ነገር ግን ጥናቱ እንደሚያሳየው ከባድ የወባ በሽታ ያለባቸው ልጆች የመጀመሪያው ኢንፌክሽን ከተከሰተ ከዓመታት በኋላ የትምህርት አቀባበላቸው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል የአንጎል ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል።

በአሜሪካ የኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ የሕፃናት ሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ቻንዲ ጆን፤ ጉዳቱ "የተደበቀ ጠባሳ" እንደሆነ ይናገራሉ።

"ልጁ በመጀመሪያ ሲታይ በጥሩ ሁኔታ ላይ ያለ ሊመስል ይችላል" የሚሉት ዶክተሩ፤ "ነገር ግን ምርመራው በክፍል ውስጥ ብቻ የሚታይ የአንጎል ጉዳት መኖሩን ሊታወቅ ይችላል" ሲሉ አብራርተዋል።

በኡጋንዳ ካምፓላ በሚገኘው የማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ፖል ባንግራና የተመራው ይህ ጥናት ሁለት ዓይነት ከባድ የወባ ሕክምና የተደረገላቸውን ሕጻናትን ተከታትሏል።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ልጆቹን የተከታተሉ ሲሆን ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱት አንዳንዶቹ ከባድ የወባ ኢንፌክሽን ካጋጠማቸው ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የመማር እና የማሰብ ሁኔታቸው ላይ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ የ'ኮግኒቲቭ' ችግር ምልክቶች እንዳሳዩ አረጋግጠዋል።

ነገር ግን የቅርብ ጊዜ ትንታኔ እንደሚያሳየው እነዚህ ተፅዕኖዎች ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ።

በአጠቃላይ 939 ሕፃናት እንደገና ምርመራ ተደርጎላቸዋል። አንዳንዶቹ ከባድ ወባ ካጋጠማቸው ከ15 ዓመታት በኋላ 'የአንጎል ወባ' [cerebral malaria] ወይም በወባ ምክንያት የሚከሰት ከባድ የደም ማነስ (አኒሚያ) እንዳጋጠማቸው ታውቋል።

የአንጎል ወባ (ሴሬብራል ማላሪያ) በጣም አስከፊው የበሽታው ዓይነት ነው። ይህ የሚከሰተው የተበከሉ የደም ሴሎች በአንጎል ውስጥ ባሉ ትናንሽ የደም ሥሮች ውስጥ ሲቀመጡ ሲሆን ይህም የደም ፍሰትን በመገደብ እብጠትን ያስከትላል።

ራስን ወደ መሳት፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ወደ ሞት ሊያመራ ይችላል። ይህ በሽታ እና ከባድ የሆነ የደም ማነስ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናትን ያጠቃል።

ዝቅተኛ የአእምሮ ምጥቀት (IQ)

በምርምሩ ላይ ሕጻናቱ ሒሳብ፣ ንባብ፣ ትኩረት ማድረግ እና አጠቃላይ ማሰብ መቻልን ተፈትነዋል።

በአማካይ በተደጋጋሚ ወባ የታመሙ ሕጻናት ምንም ታምመው ከማያውቁት ጋር ሲወዳደሩ የአይኪው መጠናቸው ከሦስት እሰከ ሰባት እንደሚደርስ ታውቋል።

በፍላደልፊያ የሕጻናት ሆስፒታል የተላላፊ በሽታዎች ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አውድሪ ጆን "ለአንድ ሕጻን የሚሰራውን በትልቁ ላይለውጠው ይችላል" ይላሉ።

ዶ/ር አውድሪ ጆን በጥናቱ ላይ ያልተሳተፉ ሲሆን ከዶ/ር ቻንዲ ጆን ጋርም ምንም ግንኙነት የላቸውም።

"ነገር ግን ይህንን በመቶ እና በሺህዎች ሕጻናት ስትመነዝረው የአእምሮ ማሰላሰል ብቃት ግዙፍ መሆኑን ማየት ይቻላል።"

በትምህርት ላይ የሚኖር ትንሽ ተግዳሮት በወደፊት የሥራ ዕድል ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ግዙፍ ነው። በሰፊው ካየነው ደግሞ በቤተሰብ ደረጃ ለምጣኔ ኃብት ከሚኖር ምርታማነት አንስቶ እንደ አገርም ትልቅ ኪሳራ የሚያደርስ ነው።

"የዓለም ግማሽ ሕጻናት የሚኖሩት ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አገራት ነው። ይህም ማለት የዓለም ግማሽ ሕጻናት ለዚህ አደጋ የተጋለጡ ናቸው ማለት ይሆናል" ሲሉ ያስረዳሉ።

ተመራማሪዎቹ በምርመራቸው ውስጥ የማኅበራዊ ኢኮኖሚ ደረጃን እና ትምህርት ያላቸውን ግንኙነት በሚመለከት ክትትል ሲያደርጉ ልዩነቱ የጤና አገልግሎት ያለው ተደራሽነት መሆኑን አስተውለዋል።

ይህም በውጤቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ያለው ሲሆን በበሽታው ካልተያዙት ይልቅ የተያዙት በሒሳብ ትምሀርት ደካማ መሆናቸውን አረጋግጦላቸዋል።

በርግጥ ማንበብ ላይ ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ አልደረሰም።

ቸኣንዲ ጆን " የሒሳብ ክህሎት ልጆች ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለማለፍ ማጎልበት ያለባቸው ነገር ነው" ይላሉ።

"ስለዚህ [ወባ] ወደ ኮሌጅ ወይም ወደ ሁለተኛ ደረጃ የመግባት ችሎታቸው ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።"

በትምህርት ቤት ያለ ትግል

አራት ልጆች ያሏት ማሪያ፤ ጆሴፍ ከመታመሙ በፊት "እንደማንኛውም ልጅ ጤነኛ ነበር" ትላለች። "ከወንድም እህቶቹ ጋር መጫወት ይወድ ነበር" ስትልም ታስታውሳለች።

እአአ በ2009 ሁለት ዓመት ሲሞላው ጆሴፍ ሃይለኛ ትኩሳት እና ማስመለስ አስቸገረው። ሲመረመር የጭንቅላት ወባ (ሴሬብራል ማላሪያ) መታመሙ ታወቀ።

በወቅቱ ማሪያ ብዙ ጊዜ እንደርሱ የታመሙ ልጆች ሲሞቱ ስለምታይ ላይተርፍ ይችላል ብላ ፈርታ ነበር።

በሆስፒታል ውስጥ ለሳምንታት ከተመላለሰ በኋኃ ጆሴፍ ተሻለው።

ነገር ግን ሰባት ኣመት ሲሞላው የመጀመርያ ደረጃ ተማሪ ሳለ ችግሮች ቀስ እያሉ እየዳሁ መጡ።

"ሒሳብ ምንም ሊገባው አልቻለም" ስትል ማሪያ ታስታውሳለች፤ አክላም "መደመርም ሆነ መቀነስ ሁሉም አስቸገሩት" በማለት የነበረበትን ችግር ታስረዳለች።

ጆሴፍ ከቁጥር ጋር የተያያዙ እንደ ፊዚክስ እና ኬሚስትሪ ያሉ ትምህርቶች የሚያስቸግሩት ለዚያ እንደሆነ ያምናል።

"በትምህርታቸው ጥሩ ከሆኑት ከወንድም እና እህቶቹ ጋር ሲወዳደር እርሱ ደካማ ነው" ትላለች።

ማሪያ በተደጋጋሚ የልጇ የትምህርት አቀባበል ያሳሰባቸው መምህራኖች እየጠሩ አነጋግረዋታል። በቤት ውስጥ የሚረዳው አስጠኚ ብትቀጥርለትም ትኩረቱ እየሸሸው የትምህርት ነገር አልሆን አለው።

"ምንም ተረጋግቶ አይቀመጥም. . . ትኩረቱ ከእርሱ ጋር አይደለም" ትላለች።

የተወሰኑት እህት ወንድሞቹ ዩኒቨርስቲ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን ጆሴፍ ይህ መንገድ እርሱ ሊጓዝበት የሚችለው አለመሆኑን ማሪያ ተረድታለች።

ጆሴፍም ቢሆን ትምህርቱን ሲጨርስ የመኪና መለዋወጫዎችን መሸጥ እንደሚፈልግ ይናገራል።

ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት የጭንቅላት ወባ ወይም ከባድ የሆነ የደም ማነስ (አኒሚያ) ወደ ማሰብ እና ማሰላሰል አለመቻል ሊመራ ይችላል።

ጥናቶች ከፍተኛ የሆነ የወባ ሕመም ለአንጎል ጉዳት ስለማጋለጡ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን አልቻሉም። ከዚያ ይልቅ በበሽታው እና ለረዥም ጊዜ በሚቆዩ ከማሰብ እና ከመማር ጋር በተያያዙ ችግሮች መካከል ያለውን ግንኙነት መረዳት ችለዋል።

ቀጣዩ ምዕራፍ የሚሆነው 'ኤምአርአይ' ተጠቅሞ አንጎልን በመመልከት ኢንፌክሽኑ የአእምሮ ክፍሎችን እንዴት እንደጎዳ መመርመር ነው።

ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች ከባድ የሆነ የወባ ሕመም ለጡንቻ አለመታዘዝ፣ በእይታ እና በአካል መታዘዝ መካከል ያለው ግንኙነት ያለመቀናጀት ችግሮችን እንደሚያስከትል ደርሰውበታል።

በተጨማሪም ከመንቀትቀጥ፣ ከዕይታ መጥፋት፣ ከባህሪ ችግሮች እና ከትኩረት ማጣት ሃይፐርአክቲቪቲ ዲስኦርደር (ADHD) ጋርም ይያያዛል።

ዓለም አቀፍ ችግር

እአአ በ2024 በመላው ዓለም በወባ 282 ሚሊዮን ሰዎች የታመሙ ሲሆን 610,000 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። ይህ ደግሞ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ598,000 ጭማሪ ያሳየ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

በአፍሪካ በርካቶቹ በበሽታው ተይዘው የሞቱት ሕጻናት ናቸው።

ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ በወባ ተይዘው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በሽታውን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ እንቅፋቶች ተፈጥረዋል።

47 አገራት ከወባ ነጻ መሆናቸው ቢታወጅም ኢትዮጵያን ጨምሮ በማዳጋስካር፣ አፍጋኒስታን እና የመን ደግሞ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።

የዓለም ጤና ድርጅት ለበሽታው መጨመር የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ ምክንያት መሆኑን ያስቀምጣል።

የከባቢ አየር መሞቅ የወባ ትንኝ ምቹ የመራቢያ ስፍራ እንዲኖራት በማድረግ ከዚህ ቀደም ወዳልተጠቁ አካባቢዎች እንድትስፋፋ አግዟታል ይላሉ።

በሽታውን ለመከላከል ይደረግ የነበረው ዓለም አቀፍ ድጋፍ መቋረጥ፣ ከዚህ ቀደም ወባን ይገድሉ የነበሩ መድሃኒቶችን የሚቋቋም ዝርያ መፈጠር የዓለም ጤና ድርጅት ከጠቀሳቸው ምክንያቶች መካከል ናቸው።

ባለሙያዎች የወባ ወደ አዳዳሲ አካባቢዎች መስፋፋት የመከላከል አቅም ያላዳበሩ ሕዝቦች ከባድ ለሆነ በሽታ እንዲጋለጡ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ቻንዲ ጆን "በደቡብ ምሥራቅ እስያ የተወሰኑ አካባቢዎች፣ በታዳጊዎች እና ወጣቶች ዘንድ ከባድ የሆነ የወባ ሕመምን ተመልክተናል" ብለዋል።

"ተመሳሳይ የሆነ የመከላከል አቅም አላዳበሩም።"

ቀጥሎ ምን ይሆናል?

ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሕጻናትን ከባድ ከሆኑ የወባ በሽታዎች ለመከላከል አርቲኤስ (RTS) እና ኤስ (S) የተባሉ ሁለት የወባ ክትባቶች ተዘጋጅተዋል።

እስከ የአውሮፓውያኑ ኅዳር 2025 ድረስ 40 ሚሊዮን ክትባቶች በ24 የአፍሪካ አገራት መሰጠታቸውን ዩኒሴፍ አስታውቋል።

አውድሪ ጆን "እነዚህ አዳዲስ የመከላከያ ሕክምናዎች መኖራቸው እና የልጆችን ሕይወት እያዳንን መሆናችን የሚያስደንቅ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ነገር ግን በቂ አይደለም፤ እዚያ ማቆም አንችልም። የያዙትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን በመጠበቅ እና በማከም ረገድ የተሻለ ነገር ማድረግ አለብን" ብለዋል።