ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦችን የማጀብ ዘመቻዋን ለጊዜው ልታቆም መሆኑን ተናገሩ
አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ቆመው የሚገኙትን መርከቦች እያጀበች ለማስወጣት የያዘችውን ዕቅድ "ለአጭር ጊዜ" እንደምታቆም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማክሰኞ ምሽት አስታወቁ።
ትራምፕ ሰኞ ዕለት የተጀመረው "ፕሮጀክት ፍሪደም" እንዲቆም የተደረገው ከኢራን ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት "ትልቅ መሻሻል" እያሳየ በመምጣቱ ምክንያት "በጋራ ስምምነት" ከውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ግን አገራቸው ድል ማስመዝገቧን በመጥቀስ ውሳኔው ትራምፕ ለዓለም የነዳጅ ፍሰት ወሳኝ የሆነውን ወሽመጥ ለማስከፈት ያደረጉት ሙከራ "በተደጋጋሚ ሳይሳካ በመቅረቱ"፤ "ማፈግፈጋቸውን" ያሳያል ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ውሳኔያቸውን ያሳወቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በኢራን የተካሄደው የመጀመሪያው የአሜሪካ-እስራኤል ጥቃት 'ኦፕሬሽን ኤፒክ ፉሪ' ዓላማውን ካሳካ በኋላ ማብቃቱን በመግለጻቸው ነው።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ጽሁፍ ውሳኔውን የወሰኑት በአደራዳሪዋ "ፓኪስታን ጥያቄ መሠረት" መሆኑን ተናግረው አሜሪካ የኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው እገዳ ግን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ትራምፕ ይህንን ከመወሰናቸው ቀደም ብሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት እና የአሜሪካ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ዳን ኬን ዘመቻው በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ የንግድ መርከቦችን እንቅስቃሴ ነፃነትን እንደሚያረጋግጥ ተናግረው ነበር።
ማርኮ ሩቢዮ "የሰላምን መንገድ እንመርጣለን። ፕሬዝዳንቱ [ዶናልድ ትራምፕ] የሚመርጡት ስምምነት ነው" ሲሉ ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በሆርሙዝ ወሽመጥ መተላለፊያ አጥተው የቆሙት ነዳጅ እና ኮንቴይነር የጫኑ መርከቦች ቀጥሎ ምን እንደሚገጥማቸው ግልፅ አይደለም።
የትራምፕ አስተዳደር ፕሮጀክት ፍሪደም ኢራን ላይ የኢኮኖሚ ጫና ለማሳደር ከታቀደው የመርከቦች እገዳ "የተናጠል እና የተለየ" ዘመቻ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቶ ተናግሯል።
የቀጣናው ተንታኞች ፕሮጀክት ፍሪደም የተጀመረው ከቀጣናው የሚገኘውን የነዳጅ ፍሰትን ወደነበረበት ለመመለስ በማቀድ በመሆኑ አሁን "ለጊዜው በመቆሙ" ኢራን የመርከቦቹ እንቅስቃሴን ማስተጓጎል የምትቀጥል ከሆነ ውጤታማ መሆኑ አጠራጣሪ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢራናውያን የተቃወሙት ይህ ፕሮጀክት ፍሪደም ዘመቻ በመቆሙ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ ሊያደርጋቸው ይችላል ሲሉ ስፋቸውን ይናገራሉ።
ሩቢዮ ቀድም ሲሉ የሰጡት አስተያየት የመጣው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን እና በአሜሪካ ጦሮች የተፈጸሙ ጥቃቶች የተኩስ አቁሙን አደጋ ላይ ሊጥሉት ይችላል የሚሉ ስጋቶች ከተፈጠሩ በኋላ ነው።
ቴህራን ለሩቢዮ መግለጫ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት ያልሰጠች ሲሆን የኢራን ፓርላማ አፈጉባዔ ሞሐማድ ጋሊባፍ ግን "የነበረውን ማስቀጠል ለአሜሪካ ከባድ መሆኑን እናውቃለን፤ ለእኛ ግን ግጭቱ ገና መጀመሩ ነው" ብለው ነበር።
ባለፈው ወር ከአሜሪካ ጋር በነበረው ንግግር የኢራን ተደራዳሪ የነበሩት ጋሊባፍ " የመርከቦች እንቅስቃሴ እና የኤነርጂ ፍሰቱ ደህንነትን በአሜሪካ እና አጋሮቿ የተኩስ አቁም ጥሰት እና እገዳ አደጋ ላይ ወድቋል። ይሁን እንጂ የእነርሱ የክፋት ድርጊት አይሳካም" ብለው ነበር።
ማክሰኞ አመሻሽ ላይ የዩኬ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት የተረጋገጡ ምንጮችን በመጥቀስ በሆርሙዝ ወሽመጥ ውስጥ የጭነት መርከብ "ምንነቱ ባልታወቀ ተወንጫፊ" መመታቷን አስታውቋል። ተጨማሩ ዝርዝር መረጃዎች ግን ለጊዜው አልተገኙም።
ቀደም ሲል የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ቁልፍ የነዳጅ ወደብ በሆነው ፉጃይራህ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሦስት ሰዎች "መጠነኛ ጉዳት" እንደደረሰባቸው የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረው ነበር።
የኢምሬትስ ትልቁ ወደብ እና የነዳጅ ማከማቻ ስፍራ የሆነው ፉጃይራህ፤ በኢራን ድሮን ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ ከፍተኛ እሳት መከሰቱን ተገልጿል።
ኢራን በጦሩ ቃል አቀባይ በኩል "እንዲህ ዓይነት ድርጊት ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ በግልጽ እናሳውቅ ነበር" ስትል አለመፈጸሟን አስተባብላለች።
አሜሪካ እና እስራኤል በቴህራን ላይ ጦርነት የከፈቱት የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ነው። ቴህራን ጥቃቱን ተከትሎ በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ የዓለም 20 በመቶ የሚሆነው የነዳጅ አቅርቦት የሚመላለስበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታለች።
በሚያዚያ ወር መጀመርያ አካባቢ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረሰ ሲሆን ይህም ቴህራን ዩኤኢን ጨምሮ በባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ የምትፈጽመውን የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶች እንድታቆም አድርጓታል።
ነገር ግን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በወሽመጡ ላይ ማለፍ የቻሉት በጣት የሚቆጠሩ መርከቦች ብቻ ናቸው። አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን አግዳለች።
ሰኞ ዕለት አሜሪካ በወሽመጡ ውስጥ ሰባት የኢራን ፈጣን ጀልባዎች ማጥቃቷን ስትገልጽ ኢራን በበኩሏ በአሜሪካ መርከብ ላይ የማስጠንቀቂያ ተኩስ መክፈቷን አስታውቃለች። ሁለቱም ወገኖች ጥቃት ተፈጽሟል መባሉን አስተባብለዋል።
ሁለት የንግድ መርከቦች ጥቃት እንደተከፈተባቸው የተገለጸ ሲሆን አንዱ በትራምፕ ወሽመጡን የማስከፈት ዕቅድ መሰረት በአሜሪካ እጀባ መውጣት መቻሉ ተገልጿል።
ከዋይት ሐውስ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ፣ ትራምፕ ከቴህራን ጋር ስምምነት መድረስ እንደሚፈልጉ ገልጸው "ኢራን ግን ለመተባበርም ሆነ ለመደራደር አልፈለገችም" ብለዋል። አክለውም "ቀጥሎ ስለሚሆነው ነገር ማንም እርግጠኛ መሆን አይችልም፤ ሁኔታዎች በሌላ አቅጣጫ ሊሄዱ ይችላሉ" ብለዋል።
ሚኒስትሩ አሜሪካ እና እስራኤል በቴህራን ላይ የፈጸሙት ጥቃት "በምጣኔ ሃብታቸው ላይ ለትውልድ የሚቆይ ውድመት" መሆኑን በመግለጽ የአገሪቱ መሪዎች "ራሳቸውን ከመጉዳታቸው በፊት የሚሄዱበትን መንገድ መለስ ብለው መፈተሽ አለባቸው" ብለዋል።
ሄግሴት በሰጡት መግለጫም ከኢራን ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም "አልከሸፈም ሲሉ ተናግረው ነበር።