ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ከዜሌንስኪ ጋር መገናኘቱ "ፋይዳ" እንደሌለው ተናገሩ
የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ከቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር የመገናኘታቸው ጥቅም እንደማይታያቸው ተናገሩ።
ፑቲን ይህን ያሉት የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ የሁለቱን አገራት ጦርነት ለመቋጨት ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲነጋገሩ ከጠየቁ በኋላ ነው።
ዜሌንስኪ ሐሙስ ዕለት ከፑቲን ጋር ቀጥተኛ ድርድር ለማድረግ ለፑቲን ግልጽ ደብዳቤ ልከዋል።
በደብዳቤያቸው ከአራት ዓመት በፊት ሩሲያ በዩክሬን ላይ በጀመረችው ወረራ የተጀመረው ጦርነት የአሜሪካን ትኩረት እስኪገዛ ድረስ "መጠበቅ ስህተት ነው" በማለት ሰላም ሊመጣ የሚችለው "በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል በሚደረግ የቀጥታ ንግግር" ነው ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዚደንት በዚሁ ደብዳቤቸያው ላይ ተኩስ አቁም እንዲደረግም ጠይቀዋል።
ፑቲን ጥያቄውን እንደማይቀበሉ አስታውቀው፤ ከማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት በፊት የሰላም ንግግር መደረግ እንደሚገባ ቀድሞ የነበራቸውን አቋም በድጋሚ ተናግረዋል።
ፑቲን አርብ ዕለት በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደው የሩሲያ ዓመታዊ የምጣኔ ሐብት ፎረም ላይ ዜሌንስኪ ያቀረቡትን ሃሳብ ይቀበሉ እንደሁ ተጠይቀው "ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገሩ ፋይዳው አይታየኝም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ዜሌንስኪ የፑቲንን ምላሽ ከሰሙ በኋላ "ሩሲያ በድጋሚ ጦርነትን መርጣለች" ብለዋል።
በቴሌግራም ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍም "ጦርነቱ እንዲያበቃ አይፈልግም። በዚህ ምላሻቸው ብዙዎች ይናደዳሉ ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።
ለዜሌንስኪ ደብዳቤ ምላሽ የሰጡት ፑቲን በበኩላቸው ሞስኮ ከኪዬቭ የምትፈልጋቸው ነገሮች ባልተሟሉበት የተኩስ አቁም ማድረጉ ዩክሬን እንደገና ራሷን እንድታደራጅ ያደርጋል ሲሉ አቋማቸውን በድጋሜ አሳውቀዋል።
"የጦር ግስጋሴያችንን ለመግታት ዩክሬኖችን ብቻ ነው የሚጠቅመው" ሲሉም አክለዋል።
"ሆኖም ስምምነቶችን እንፈልጋለን፤ ግን ለስድስት ወር አሊያም ለሦስት ወር አይደለም፤ የረዥም ጊዜ ስምምነት ነው የምንፈልገው" ብለዋል።
ባለሙያዎች በሃሳቡ ላይ ከመከሩበት እና ከመፍትሔ ጋር ከመጡ በኋላ መገናኘት እንደሚችሉም ጨምረው ገልጸዋል።
ፑቲን ጦርነቱን የሚያቆሙት የሩሲያ ግቦች ሲሳኩ እንደሆነም አፅንኦት ሰጥተዋል።
"ወታደራዊ እርምጃዎች የሆነ ጊዜ ይቆማሉ፤ እንደዚያ እናስባለን። ያለምንም ጥርጣሬ ለራሳችን ያስቀመጥናቸውን ግቦች ካሳካን በኋላ ይቆማሉ።"
የሩሲያ የረዥም ጊዜ አቋም ዩክሬን ከዶንስክ፣ ሉሃንስክ፣ ኼርሶን እና ዛፖሪዥያ ክልሎች መውጣት እና ኔቶን ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት ማቆም አለባት የሚል ነው።
ኪዬቭ ግን ለሞስኮ የሚቀርብ ማንኛውም ስምምነት ወደፊት እንደገና እንድትወረር እንደሚያበረታታ በመግለጽ ማንኛውንም ግዛት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነችም።
ሩሲያ ሙሉ ወረራ የከፈተችባት የክሬሚያን ባሕረ ገብ መሬት ከተቆጣጠረች ስምንት ዓመታት በኋላ እንደሆነም ጠቅሳለች።
የዜሌንስኪ ደብዳቤ ይዘት ዋይት ሃውስን ጨምሮ በአንዳንድ ወገኖች የሰላም ተስፋን ሰጥቷል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለቱ መሪዎች ቢገናኙ "ጥሩ ነበር" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን አርብ ዕለት በሩሲያ በተያዘው አዞቭ ባሕር "ሕገ ወጥ ጭነት የጫኑ" አምስት መርከቦች ላይ ጥቃት መፈፀሟን አስታውቃለች።
የዩክሬን የድሮን አዛዥ ሮበርት ብሮቭዲ መርከቦቹ የዩክሬንን እህል በመዝረፍ፣ ነዳጅ እና ወታደራዊ ገብዓቶችን በማስተላለፍ ተሳትፈዋል ብለዋል።
የአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሁለት መርከቦች ላይ በተፈፀመው ጥቃት 5 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል። ሆኖም ጥቃቱን ማን እንደፈፀመው አልጠቀሰም። መርከቦቹ ግን የአዘርባጃን አይደሉም ብሏል።
በዩክሬን የሚንቀሳቀስ አንድ ድሮን በሮማኒያ ጥቁር ባሕር ኮንስታንታ ወደብ ላይ ፈንድቷል።
የዩክሬን ኦፕሬተሮች ድሮኑ በሩሲያ የኤሌክትሮኒክስ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ከመስመሩ እንደወጣ ተናግረዋል።
ባለፉት ቀናት ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈፀመችው ተከታታይ ጥቃቶች ቢያንስ 13 ሰዎች ሲገደሉ 70 የሚደርሱ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።