ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ
ሩሲያ በዩክሬን ዋና ዋና ከተሞች ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች እንደተገደሉ እና ብዙዎች እንደቆሰሉ ተገለጸ።
በዲፕሮ ከተማ አምስት ሰዎች ሲገደሉ 25 ሰዎች ተጎድተዋል። ዛሬ ንጋት ላይ በደረሱ ጥቃቶች በመዲናዋ ኪቭ አራት ሰዎች መገደላቸው እና 51 መቁሰላቸውም ተዘግቧል፤ 35 ያህሉ ደግሞ ሆስፒታል ገብተዋል።
የኪቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊሽኮ እንዳሉት ሁለት ግዙፍ የመኖሪያ ሕንጻዎች የተመቱ ሲሆን፤ ሰዎች በፍርስራሽ ሥር ተቀብረው ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ዩክሬን ባለፈው ወር የድሮን ድብደባ በመፈጸሟ በምላሹ “ስልታዊ ጥቃት” ለማድረስ ሞስኮ ስትዝት ቆይታለች።
ሩሲያ በቁጥጥሯ ሥር ባዋለችው የዩክሬን ሉሀንስክ ግዛት በደረሰው የድሮን ጥቃት 21 ሰዎች ተገድለዋል።
የኪቭ ከንቲባ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። “ጠላታችን በባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት እየፈጸመ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
በአብዛኞቹ የዩክሬን ከተሞች የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወሎች እየተሰሙ ነው። በማዕከላዊ ኪቭ ጭስ መታየቱም ተገልጿል።
በሌላ በኩል በሩሲያ ኢልስኪ የነዳጅ ማቀነባበሪያ የደረሰ ጥቃት እሳት ማስነሳቱ ተገልጿል።
ኪቭ ውስጥ የበርካታ ድሮኖች እና ፍንዳታ ድምጽ እየተሰማ ይገኛል። ሞስኮ የፈጸመችው ጥቃት በነዳጅ ማደያ እሳት አቀጣጥሏል።