ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአውስትራሊያ 200ሺህ ዶላር የሚያወጡ በረሮዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ተያዙ
የአውስትራሊያ መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ ከ100 ሺህ በላይ በረሮዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታወቀ።
የእጅ መዳፍ የሚያህል በረሮን ጨምሮ በስፋት የማይገኙ የበረሮ ዝርያዎች በኒው ሳውዝ ዌልስ ድንበር ላይ ሲዘዋወሩ ተይዘዋል።
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ነፍሳት 200 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር እንደሚያወጡ ተገልጿል። ከአውስትራሊያ ሲድኒ 200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ባቱርስት ከተማ የተገኙ የበረሮ ዝርያዎች (hissing cockroaches እና dubia cockroaches) በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ከነበሩት መካከል ይጠቀሳሉ።
እነዚህ የበረሮ ዝርያዎች ወደ አውስትራሊያ ከተወሰዱ በኋላ እንዲራቡ ተደርጎ ይሸጣሉ።
ከዚህ ቀደም በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ሕገ ወጥ የነፍሳት ዝውውሮች አንጻር የአሁኑ ሰፊው መሆኑ ተገልጿል።
እነዚህ ነፍሳት በሽታ ከማሰራጨት በተጨማሪ እጽዋት እና ግብርና ላይ ጫና እንደሚያሳድሩም ተመልክቷል።
ነፍሳቱን ለተሳቢ የቤት እንሰሳት ምግብነት የሚገዙ መኖራቸውን የገለጹት የአውስትራሊያ ባለሥልጣናት፤ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተያዙት በረሮዎች እንደሚገደሉ አስታውቀዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ፣ ኢነርጂ፣ አካባቢ እና ውሃ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ "በስፋት የማይገኙ የበረሮ ዝርያዎችን ማርባት እና በሕገ ወጥ መንገድ መሸጥ እየተለመደ መጥቷል። የቤት እንስሳ ሻጮች እና የቤት እንስሳ የሚያሳድጉ ሰዎች ስለ ጉዳዩ እንዲያውቁ አድርገናል።" ብለዋል።
"እነዚህን የበረሮ ዝርያዎች የሚያራባ ወይም ይዞ የተገኘ ሰው በሕጉ መሠረት ይቀጣል" ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።
ተሳቢ የቤት እንሰሳት የሚያሳድጉ ሰዎች ሌላ ሕጋዊ አማራጭ እንዲጠቀሙም አሳስበዋል።
"Madagascar hissing cockroaches" በመባል የሚታወቀው የበረሮ ዓይነት በዓለም በመጠን ትልቁ እንደሆነ ይነገርለታል። ይሄ የበረሮ ዝርያ በሚያወጣው ዘለግ ያለ ድምጽ ይታወቃል።
እባብ በመያዝ የምትታወቀው ስቴፋኒ ሌሰር ለአውስትራሊያው ኤቢሲ እንደተናገረችው "ሰዎች የሚይዟቸው ትልልቅ ስለሆኑ ነው። በእጅ ይሞላሉ" ብላለች።
በረሮዎቹ ግዙፍ መሆናቸው ለተሳቢ የቤት እንሰሳት ምግብነት ተመራጭ እንዳደረጋቸውም ተናግራለች።