ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ፊት ለፊት ለመነጋገር ለፑቲን ግልፅ ደብዳቤ ፃፉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጦርነቱን ለመቋጨት ባለመ አዲስ እርምጃቸው ከፑቲን ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር ጥያቄ አቀረቡ።

መሪው ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፃፉት ይፋዊ ግልፅ ደብዳቤ በአውሮፓ ያለ ጦርነት አሁንም የአሜሪካን ትኩረት እስኪገዛ ድረስ "መጠበቅ ስህተት ነው" በማለት ሰላም ሊመጣ የሚችለው "በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል በሚደረግ የቀጥታ ንግግር" ነው ብለዋል።

ዜሌንሲኪ እንዲደረግ ባሰቡት ንግግር ወቅት ሙሉ ለሙሉ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ፑቲን ይህን ሀሳብ ሐሙስ ዕለት ውድቅ አድርገውታል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት የሁለቱ አገራት መሪዎች ቢገናኙ መልካም እንደሆነ ተናግረዋል።

የደብዳቤው ይዘት እምቢተኝነት እንዲሁም ፌዝ ያለው ሲሆን፤ ዩክሬን በቅርቡ በሩሲያ ግዛቶች ላይ የፈፀመቻቸው ጥቃቶች ላይ ያተኮረ ይመስላል።

ዜሌንስኪ ፑቲንን "ከ26 ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በኋላ እድሜ ጫና እያሳደረብዎ ነው" ብለዋቸዋል።

ከዚህ ባለፈ ደብዳቤው ግብዣንም ያካተተ ነው።

"ዩክሬን ይህን ጦርነት በእኛ እና በእርስዎ መካከል በቀጥታ ንግግር እንዲቋጭ ሀሳብ ታቀርባለች። ለንግግር ጥሪ እያቀረብኩ ነው" በማለት ዜሌንስኪ ፅፈዋል።

የዩክሬኑ መሪ እንዲህ አይነት ጥሪ ሲያቀርቡ አዲስ አይደለም።

እንደወትሮው ሁሉ ምላሽ የሰጠው ክሬምሊን ዜሌንስኪ ፑቲንን ለማግኘት ሞስኮ መምጣት ይችላሉ ብሏል።

በዚህ አዲስ ጥረት ኪየቭ አሜሪካ በኢራን ጦርነት ላይ ሙሉ ለሙሉ ትኩረቷን ማድረጓን በይፋ አመልክታለች።

ዜሌንስኪ "በአውሮፓ ያለ ጦርነት [የአሜሪካ] የትኩረት ማዕከል እስኪሆን ድረስ መጠበቅ ስህተት ይሆናል" ብለዋል።

የደብዳቤውን ይዘት ያልተመለከቱት እና በሴንት ፒተስበርግ ከተማ ለውጭ ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ፑቲን፤ "ከዩክሬን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚገባ ዝግጁ እና ፈቃደኛ" እንደሆኑ ተናግረዋል።

ነገር ግን አንዳንድ ነገሮች መስተካከል አለባቸው ብለዋል።

ትራምፕ በኢራን ጉዳይ ተወጥረዋል ሲሉ የጠቆሙት ፑቲን፤ አውሮፓ ዜሌንስኪ ግዛቶችን እንድታስረክብ ማነጋገር ይችላል ብለዋል።

የፑቲን የረጅም ጊዜ አቋም ሩሲያ አሁን በከፊል የተቆጣጠረቻቸውን አራት ግዛቶች ዩክሬን እንድታስተክብ እና ኔቶን ለመቀላቀል የያዘቸውን ጥረት እንድታቆም ነው።

ዩክሬን ግዛቶችን አሳልፎ መስጠትን ሩሲያ ዳግም ወረራ ለማድረግ ያደፋፍራል በሚል ውድቅ ያደረገች ሲሆን፤ ሞስኮ ክሬሚያን ከጠቀለለች ከስምንት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ2022 ሙሉ ለሙሉ ወረራ አድርጋለች።

ባለፉት ወራት የተኩስ አቁም ስምምነቶች የተቀዛቀዙ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በጄኔቫ፣ አቡ ዳቢ እና ኢስታንቡል የተደረጉ የሰላም ንግግሮች ከሽፈዋል።

1,800 ቃላትን በያዘው ደብዳቤ ዜሌንስኪ "ጦርነቱ አገራችን ላይ ካደረሰው ጫና በኋላ የሩሲያ ወታደሮች እጣ ፈንታ እኛ የዩክሬናዊያን የሚያስጨንቀን አይደለንም። ነገር ግን ዩክሬናዊያን ያሳስቡኛል። ሕዝባችንን እያጣን ነው፤ እናም እያንዳንዱ እጦት ለእኛ ህመም ነው" ብለዋል።

ዜሌንስኪ ሩሲያዊያን በዩክሬን የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶች፣ በነዳጅ እጥረት እና በዋጋ ንረት እንዲሁም በጦርነቱ እየተማረሩ ነውም ብለዋል።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዲሪይ ሲቢህ "ግልፅ ደብዳቤው ጦርነቱን ለማቆም ትልቅ እና ትርጉም ያለው ጥሪ ነው" ብለዋል።