ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኦሮሚያ ችሎት ውስጥ ዳኛና የቀድሞ ባለቤቱን በገደለው ተከሳሽ እና በፍርድ ቤት ጠባቂዎች ላይ ምርመራ ተከፈተ
በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ወልመራ ወረዳ ፍርድ ቤት ክርክር ሲያደርግበት የነበረውን የፍትሐ ብሔር ክስ ውሳኔ በመቃወም አንድ ተከሳሽ ዳኛዋን እና የቀድሞ ባለቤቱን በሽጉጥ ገድሏል።
ድርጊቱ የተፈፀመው ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ግንቦት 23/ 2018 ዓ. ም. አራት ሰዓት አካባቢ ወልመራ ወረዳ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ውስጥ ነው።
ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጌታቸው ጣሰው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቅናው በቀለ የተባለው ተጠርጣሪ በፍርድ ቤቱ በቤተሰብ ጉዳይ ክርክር ሲያደርግ መቆየቱንና ከባለቤቱ ጋር ፍቺ መፈፀማቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ "ከትናንት በስቲያ የነበረው ቀጠሮ የንብረት ክፍፍል አፈፃፀምን ለመመልከት የተያዘ ነበር" ብለዋል።
ክርክሩ አብቅቶ የመጨረሻው ብይን እየተነበበ በነበረበት ወቅትም ተጠርጣሪው በችሎት የተገኙትን የቀድሞ ባለቤቱን ወ/ሮ አልማዝ መኮንን እና ዳኛ ወ/ሮ ወርቄ ፉካንሳ በያዘው ሽጉጥ ተኩሶ እንደገደላቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
"በውሳኔው ደስተኛ ባለመሆኑ ድርጊቱን እንደፈፀመው ይታሰባል" ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ከሆነ የቀድሞ ባለቤቱ በተተኮሰባት ጥይት ወዲያውኑ ሕይወቷ ያለፈ ሲሆን ዳኛዋም ሆስፒታል መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ተጠርጣሪው ራሱ ላይ ከተኮሰና እና በስለት ጉዳት ከፈፀመ በኋላ ለማምለጥ ሲሞክር በቁጥጥር ሥር ውሏል።
በሆለታ ሆስፒታል ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ለተሻለ ሕክምና አዲስ አበባ ወደሚገኘው ጳውሎስ ሆስፒታል ተልኮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ሕክምና እየተደረገለት ይገኛል።
ግለሰቡ በሌሎች ሰዎች ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ ራሱን ለማጥፋት ከመሞከሩ ውጭ እርሱን ለመያዝ ከፀጥታ ኃይል በኩል የተደረገ ተኩስ እንዳልነበር አስረድተዋል።
ተከሳሹ ፍርድ ቤት ችሎት ድረስ እንዴት ሽጉጥ ታጥቆ ሊገባ እንደቻለ ብዙዎች ጥያቄ አንስተዋል። ይህንን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው " ጉዳዩ ምርመራ የሚያስፈልገው ነው" ብለዋል።
"ፍርድ ቤቶች ጠባቂዎች አሏቸው፤ ወደ ፍርድ ቤት የሚገቡ ሰዎች ተፈትሸው ነው የሚገቡት። የችሎት አስከባሪ ፖሊሶችም አሉ፤ እንዲህ ዓይነት ክፍተት መፈፀሙ ያሳዝናል" ሲሉ ለወደፊት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ከአሁኑ ክስተት ጋር በተያያዘ የፍርድ ቤቱ ጠባቂዎች እና ችሎት አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ አክለዋል።
ተከሳሹም ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ፍርድ ቤት ይቀርባል ብለዋል።
አቶ ጌታቸው እንዳሉት ግለሰቡ ሁለት ሚስቶች የነበሩት ሲሆን ከሁለቱም ጋር ፍቺ ፈፅሟል። በፍርድ ቤት ችሎት ውስጥ ከገደላት ሚስቱም ልጆች እንዳሉት አክለዋል።
ግለሰቡ ከሁለቱም ሚስቶቹ ጋር ከንብረት ጋር በተያያዘ ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል።